በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተጀምረዋል ። በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለቱን መቀመጫቸውን ሀዋሳ ከተማ ላይ ያደረጉትን ሀዋሳ ከተማን እና ሲዳማ ቡናን አገናኝቶ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ የ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከሁተኛ ሳምንት ጨዋታቸው በቋሚ አሰላለፍ ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል 4 ቅያሪዎች የነበሩ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩች ደሞ 1 ቅያሪ ብቻ በማድረግ ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው ጅማሮ ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር 5 ደቂቃ ብቻ ነበር የፈጀባቸው ። ብሩክ በየነ ከወንድማገኝ ሀይሉ ጋር በጥሩ አንድ ሁለት ቅበብል አድርጎ ወደ ግብ ኳስ ይዞ ሄዶ በግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ጥፋት ቢሰራበትም ኳሱን ወድያው ያገኘው ኤፍሬም አሻም ሊያስቆጥረው ችሏል ።
- ማሰታውቂያ -
ግብ ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎችም በተሻለ ወደ ፊት በመሄድ ግብ ለማስቆጠር የጣሩ ሲሆን በተለይም 14ኛ ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን በቅጣት ምት ከሰለሞን ሀብቴ የደረሰውን ኳስ በግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ቢያገኘውም ጀርባውን ለግብ ሰጥቶ የነበረው ተጫዋቹ ኳሱን ከግቡ አናት በላይ መቶት ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በጨዋታው 30ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲዳማ ቡና ያገኙት የማዕዘን ምት ወደ ግብ ሲሻማ የሀዋሳ ከተማው 19 ቁጥር ዮሐንስ ሴጌቦ በእጁ በመንካቱ ሲዳማ ቡናዎች የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። ኳሱን በእጁ የነካው ዮሐንስ በውሳኔው ደስተኛ ባለመሆን የዕለቱ ዳኛ ላይ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ የቢጫ ካርድ ሊመለከት ችሏል ።
የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም አጥቂው ይገዙ ቦጋለ 33ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ የጨዋታው 1 ለ 1 ሆነ ። ጨዋታው በርካታ ጥፋቶች ያስመለከተ የነበረ ሲሆን የዕለቱ የመሀል ዳኛ ባህሩ ተካ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽ በ 1 አቻ ውጤት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና ተጭነው በመጫወት ግቦችን ለማስቆጠር ጥረቶችን ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመውሰድ ግቦችን ለማስቆጠር ሞክረዋል ።
68ኛው ደቂቃ ላይ ከግቡ በረጅም ርቀት ላይ የተመታውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ገዛኸኝ በጭንቅላት በመግጨት ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ወደ ውጪ አውጥቶታል ።
ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ሀዋሳ ከተማ መሪ ሊሆን የሚችልበትን ዕድል ባያገኝም አልተጠቀሙበትም ። በኩነቱ ወንድማገኝ ሀይሉ ፤ ዳንኤት ደርቤ እና ብሩክ በየነ ጥሩ ቅበብል አድርገው ኳሱ ለመድኃኔ ብርሀኔ ቢደርስም ተጫዋቹ ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በ80ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ውጤት የቀየረ ግብ በሀዋሳ ከተማ በኩል ተቆጠረ ። ግብ ጠባቂው ሙንታሪ በረጅም የመታውን ኳስ መድኃኔ ብርሀኔ አግኝቶት ከሲዳማ ቡና ተከላካዮችን ጋር በሚፋለምበት ሰአት የደረሰው ብሩክ በየነ መቶት ግብ አደረገው ።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሀዋሳ ከተማ በኩል ተረጋግተው ኳሱን በመያዝ ጨዋታውን ለማጠናቀቅ የሞከሩ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል 89ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ ካወጣው ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል ።
ጨዋታውም በዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 6 ያሳደገ ሲሆን ሲዳማ ቡና ባለበት 4 ነጥብ የሚቆይ ይሆናል ።