በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን የረፋድ ጨዋታ መከላከያ ግብ ጠባቂዉ ክሌመንት ቦየ ሳይቀር ግብ አስቆጥሮ ተጋጣሚዉን እና ጠንካራውን ሲዳማ ቡና 5ለ3 በሆነ ዉጤት ሰፊ ዉጤት አሸንፏል።
ሲዳማ ቡና በፋሲል ከነማ ሽንፈትን ካስተናገደበት ጨዋታ የሶስት ተጫዋቾችን ለዉጥ አድርጎ ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ መከላከያ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ከነበረዉ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለዉጥ አድርጎ ወደ ሜዳ ገብቷል።
ረፋድ 4:00 ሰዓት ሲል በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ገና ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ በግብ ሙከራ የታገዘ ነበር በ2ኛዉ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ላይ ግሩም ሀጎስ ያሻገረዉን ኳስ የሲዳማ ተከላካዮች ሊያፀዱት ባለመቻላቸው ምክንያት የመከላከያዉ አማካይ ቢንያም በላይ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሯታል። ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ ደግሞ በግራ መስመር በኩል በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሲዳማ የግብ ክልል የደረሱት መከላከያዎች በዳዊት ማሞ አማካኝነት የተሻገረዉን ኳስ በተመሳሳይ ተሾመ በላቸዉ በጥሩ አቋቋም አግኝቷት ሁለተኛዋን ግብ ለክለቡ መከላከያ አስቆጥሯል።
- ማሰታውቂያ -
ገና በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ግብ አስተናግደዉ ችግር ዉስጥ የገቡ የሚመስሉት ሲዳማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ተመልሰዉ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ዳዊት ተፈራ ከይገዙ ቦጋለ ጋር በጥሩ አጨዋወት መንገድ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ከደረሱ በኋላ ዳዊት ተፈራ ከርቀት ግብ አስቆጥሮ ክለቡን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርጓል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ሲዳማዎች ተደጋጋሚ ወደ መከላከያ የግብ ክልል መድረስ ችለዉ የነበረዉ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ይበልጥኑ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በ41ኛዉ ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ያቀበለዉን ኳስ ተሾመ በላቸዉ ለራሱ ሁለተኛውን እንዲሁም ለክለቡ ሶስተኛዉን ግብ አስቆጥሮ በመከላከያ 3ለ1 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ተጭነዉ ለመጫወት የሞከሩት ሲዳማዎቾ ያሰቡት ተሳክቶላቸው ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ተደጋጋሚ ጫናዎችን በመከላከያ ሲፈጥርባቸው ተስተውሏል። በተለይ በ55ኛዉ ደቂቃ ላይ አጥቂዉ እስራኤል ዕሸቱ ከቢኒያም በላይ የተቀበለውን ኳስ ለአዲሱ አቱላ አቀብሎት አዲሱ ኳሷን ከርቀት ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነታቸውን ወደ 4ለ1 ከፍ ማድረግ ችሏል።
በዚህ የጨዋታ መንገድ ቀጥለዉ የጨዋታውን ቴምፖ አቀዝቅዘዉ ለመጨረስ ያሰቡ የሚመስሉት መከላከያዎቸ በ68ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ተጨማሪ አስደናቂ ግብ ተመልክተንበታል። ግብ ጠባቂዉ ክሌመንት ቦየ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የመታዉ ኳስ በተቃራኒው ተ/ማርያም ሻንቆ ከግቡ ወጥቶ ስለነበር ኳሷን መያዝ ሳይችል ቀርቶ ኳሷ መረብ ላይ አርፋለች። ይህም በጨዋታዉ የታየ አስደናቂ ክስተት ሆኖ አልፏል።
በዚህ መንገድ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ሲዳማ ቡናዎች አከታትለው በ73ኛዉ እና በ ደቂቃ ላይ በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዉ የነበረ ቢሆንም ጨዋታው በመከላከያ 5ለ3 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም መሰረት መከላከያ ነጥቡን 30 አድረሶ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ሲዳማ ቡና በ35 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።