በዘጠነኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተካሄደው የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በሲዳማ ቡና የ2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ሲዳማ ቡና በስምንተኛው ሳምንት ጨዋታ ከመከላከያ አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ደግፌ አለሙን እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ቀይረው ሲያስገቡ በወላይታ ድቻ በኩልም በተመሳሳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ መልካሙ ቦጋለን እና ስንታየሁ መንግስቱን ጨዋታውን እንዲጀምሩ አድርገዋል ።
ሲዳማ ቡና በተጣለበት ቅጣት ምክንያት ያለምንም ደጋፊ በተደረገው ጨዋታ በጅማሮ ላይ ወላይታ ድቻዎች በፍጥነት ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉበት ሲሆን ቀስ በቀስ ግን ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
18ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ወንድወሰን ተመልሶ ወደ ውጪ ወቷል ። ወደ ውጪ ወቶ የማዕዘን ምት የሆነውን ኳስ መሀሪ መና አሻግሮት ይገዙ ቦጋለ ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ወንድወሰን አሸናፊ መልሶታል ።
ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታወን ተቆጣጥረው በመጫወት በተደጋጋሚ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም እንደፈጠረት ጫና የግብ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም ነበር ። ብልጫ የተወሰደባቸው የጦና ንቦቹ የሚነጥቋቸውን ኳስ በረጅም ወደ ፊት መስመር ቢልኩም በቀላሉ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ሲሳይ ሆነዋል ።
ከውሀ እረፍት በኋላ ጫና ማድረጋቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች 32ኛ ደቂቃ ላይ በመሀሪ መና አማካኝነት ያደረጉት የግብ ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሶባቸዋል ። ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ሲዳማ ቡናዎች ያገኙት የማዕዘን ምት በወላይታ ድቻ ተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ዳዊት ተፈራ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ተከላካዩ ጊት ጋትኩት በጭንቅላቱ ነፃ ለነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ያቀበለው ሲሆን ሀብታሙም ተረገግቶ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን መሪ አደረገ ።
በ42ኛው ደቂቃ ላይ ተክለማርያም ሻንቆ ኳስ በሚይዝበት ወቅት ከሳጥን ውጪ ይዘሀል በሚል የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ የተመለከተ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ ሲዳማ ቡናዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት በቁጥር 3 ለ 1 ሆነው ወደ ወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል በገቡበት ቅፅበት የመሀል ዳኛው አጋማሹ ተጠናቋል በሚል የፊሽካ ድምፅ አሰምተዋል ። ይህም በሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ላይ ቅሬታን የፈጠረ ነበር ።
የሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ምንይሉ ወንድሙን ቀይረው ያስገቡት ወላይታ ድቻዎች አጋማሹ በተጀመረ 20 ሰከንድ እንኳን ሳይሞላው ነበር ግብ ያስተናገዱት ። ከሲዳማ ቡና የሜዳ ክፍል በረጅም የተመታውን ኳስ የጦና ንቦቹ ተከላካዮች ለማውጣት ሲሞክሩ ኳሱ የደረሰው አምበሉ ፍሬው ሰለሞን ኳሱን እየገፋ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ መትቶ በማስቆጠር የሲዳማ ቡናን መሪነት ከፍ አደረገ ። ከግቡ መቆጠር በኋላ ሲዳማ ቡናዎች የበላይነታቸውን በማስቀጠል በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።
51ኛ ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከሀብታሙ ገዛኸኝ የደረሰውን ኳስ በሳጠን ውስጥ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ በተከላካይ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ መስመር በኩል ብቻውን ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ሊመለስበት ችሏል ።
ወላይታ ድቻዎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች በመስመር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች የተሳኩ አልነበሩም ። ነገር ግን በሲዳማ ቡና እየደረሰባቸው የነበረው ከፍተኛ ማጥቃት እንደቀጠለ ነበር ።
በዚህም 63ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቅጣት የሞከረው እና 74ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ ለሲዳማ ቡናዎች ተጨማሪ ግቦችን ሊያስገኙ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የጦና ንቦች ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ሲዳማ ቡና ነጥቡን 11 በማድረስ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወላይታ ድቻ በበኩሉ በ13 ነጥብ በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።