በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተገናኘቱ የሲዳማ ቡና እና ተመስገን ዳናን በአሰልጣኝነት የሾሙት የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ግብ ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠቋል ።
ሲዳማ ቡና በ13ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተስፋዬ በቀለ ጊት ጋትኩትን ተክተው ሲያስገቡ በወልቂጤ ከተማ በኩል በቅዱስ ጊዮርጊስ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ የገቡ ሲሆን በዮናስ በርታ እና አህመድ ሁሴን ምትክ ተስፋዬ ነጋሽን እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን አሰልፈዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴዎች በሁለቱም በኩል የታዩበት ሲሆን የሚያገኟቸውን ኳሶች በቀጥታ ወደ ግብ ክልል በመውሰድ በሲዳማ ቡናም ሆነ በወልቂጤ ከተማ በኩል ጥረቶች የተደረጉበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
ሲዳማ ቡናዎች ኳስን ከኋላ መስርተው ለመውጣት ሲሞክሩ ወልቂጤ ከተማውች ጫን ብለው በመጫወት በቀላሉ ከሜዳቸው እንዳይወጡ ማገድ የቻሉ ሲሆን እነዚህን ኳሶችም በነጠቁበት ቅፅበት ወደ ሳጥን በመላክ እንዲሁም ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ መሞከር የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 10ኛ ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ረመዳን የሱፍ ከግራ አቅጣጫ ኳሱን አየር ላይ ሳለ በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በተክለማርያም ሻንቆ ተይዟል ።
በሊጉ በተደጋጋሚ ከሚታዩ ክፍትቶች አንዱ የረዳት ዳኞች ከጨዋታ ውጪ ላይ የሚሰጡት ውሳኔ በተደጋጋሚ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በሚያስብል መልኩ ይታዩ ነበር ። በዚህ ጨዋታ ላይም የተስተዋለው ነገር ይህ ጉዳይ በሚመለከትው አካል ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው ነው ። በ23ኛው ደቂቃ ላይ በወልቂጤ ከተማ በኩል ረመዳን የሱፍ በሀይሉ ተሻገር እና ጫላ ተሺታ ያደረጉት ሳቢ ቅብብል በመጨረሻም በበሀይሉ ግሩም አጨራረስ ግብ መሆን ቢችልም የመስመር ዳኛው ፍፁም ስህተት በሆነ መልኩ ከጨዋታ ውጪ ነው በማለት ጎሉን ሽረውታል ።
የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሲዳማ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ። 42ኛ ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከርቀት ላይ ከተገኘ የቅጣት ምት ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻገረው ኳስ ከግቡ የወጣውን ሰይድ ሀብታሙን አልፎ ያገኘው ያኩቡ መሀመድ በግንባር ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ተቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ የወልቂጤ ከተማው ተከላካይ ዋሁብ አዳምስ ከግቡ አፋፍ ላይ አውጥቶታል ።
በሁለተኛው ኢጋማሽ በሁለቱም በኩል የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ በተመሳሳይ የቀጠለ ሲሆን በአንፃራዊነት ከውሀ እረፍት በፊት ወልቂጤ ከተማዎች ከውሀ እረፍቱ በኋላ ደግሞ ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር ።
ምንም እንኳን በሲዳማ ቡናም ሆነ በወልቂጤ ከተማ በኩል በመሀል የሜዳው ክፍል ብልጫውን ወስደው ወደ ፊት ለመሄድ የነበረው የሜዳ ላይ ፉክክር ጠንካራ የነበረ ቢሆንም ወደ ወደ ማጥቃት ሶስተኛው ዞን ሲደርሱ የረባ የግብ ዕድል ለመፍጠር አይናፋር ሆነው ቆይተዋል ።
በወልቂጤ ከተማ በኩል ጌታነህ ከበደ በ55ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ወደ ግብ የሞከረው ጠንከር ያለ ኳስ በተክለማርያም ሻንቆ ከመያዙ ውጪ ሌላ የግብ ሙከራ አልተመለከትንበትም ነበር ። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ጥፋቶች በርከት ብለው የነበረ ሲሆን በዚህም ከሁለቱም በኩል የማስጠንቀቂያ ካርዶች የተመለከቱ ተጫዋቾች ነበሩ ። በመጨረሻም የጨዋታው ውጤት ሲዳማ ቡና 0 ወልቂጤ ከተማ 0 ሆኖ ተፈፅሟል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 19 በማድረስ ደረጃውን ወደ 5 ሲያሻሻል ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በ17 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።
በ14ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና አዲስ አበባ ከተማን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ጅማ አባጅፋርን የሚገጥሙ ይሆናል ።