በ22ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለተኛ ጨዋታ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 1 – 0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ21ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ደስታ ደሙ ፤ ናትናኤል ዘለቀ እና ሀይደር ሸረፋን በሱሌማይ ሀሚድ ፤ ጋቶች ፓኖም እና አዲስ ግደይ ምትክ ሲያሰልፉ በሳምንቱ ከሲዳማ ቡና አቻ የተለያዩት አዳማ ከተማዎች በተመሳሳይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ሳኩባ ካማራ ፤ ዮናስ ገረመውን እና ዳዋ ሆቴሳን በጀመል ጣሰው ፤ ቶማሰ ስምረቱ እና ጀሚል ያዕቆብ ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምሩ አድርገዋል ።ቅዱስ ጊዮርጊስ ገና በ3ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ቀዳሚ ግባቸውን ያገኙት ። በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ከቆሙ ኳሶች ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አማቻችቶ እያቀበ ያለው ሄኖክ አዱኛ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል በግንባር ሲጨርፈው ነፃ የነበረው የቀድሞ የአዳማ ከተማ ተጫዋች ከነአን ማርክነህ በግንባር በመግጨት ግብ አድርጎታል ።
በጊዜ ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት በቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ላይ በቁጥር በርከት ብለው መቆየት ችለው ነበር ። የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረትም 17ኛ ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ ከምኞት ደበበ የነጠቀውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ለነበረው አቡበከር ወንድሙ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም ኡበበከር ወደ ግብ የመታውን ኳስ ቻርለስ ሉክዋጎ አድኖበታል ።ፈረሰኞቹ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከቀኝ መስመር በኩል በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ጥረቶቻቸው ግን በቂ አልነበሩም ።
አዳማ ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ ፈረሰኞቹ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በቀላሉ ወደ ሳጥን ውስጥ ገብተው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ግን አልቻሉም ነበር ። በዚህም ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች የቅዱስ ጊዮርጊስን መረብ ለማግኘት ሲታትሩ ቆይተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በአዳማ ከተማዎች በተወሰደባቸው ብልጫ ከኳስ ጀርባ በቁጥር በርከት ብለው የሚገኙት የሊጉ መሪዎች ኳስ በእግራቸወን ስር በሚገባበት ጊዜ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በማድረስ ለመጠቀም ሲሞክሩ ነበር ።በ31ኛው ደቂቃ ላይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በረጅም የላከውን አዲስ ተስፋዬ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ አማኑኤል ገብረሚካኤል ማግኘት ችሎ የነበረ ቢሆንም አማኑኤል ኳሱን ከመሞከሩ በፊት ቀድሞ አዲስ ከኋላው ደርሶ ኳሱን ተንሸራቶ በማውጣት የማዕዘን ምት አድርጎታል ።
33ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ በጨዋታው ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ። ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ነፃ የነበረው ደስታ ደሙ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ልኮት የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ሳኩባ ካማራ ለጥቂት መልሶበታል ።
በአዳማ ከተማ በኩል 40ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል ያዕቆብ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ቻርለስ ሉክዋጉ በአግባቡ መቆጣጠር የተሳነውን ኳስ ያገኘው አሜ መሀመድ ግብ ለማድረግ የመታው ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1 – 0 መሪነት ተጠናቋል ።በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ አዳማ ከተማዎች የአቻነቱን ግብ ፍለጋ የሚያደርጉትን ጥረት የቀጠሉ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ መስመር ግን ክፍትቶችን የሚሰጥ አልነበረም ። በፈረሰኞቹ በከል በመጀመሪያው አጋማሽ እንደነበረው በረጃጅም ኳሶች እና በፈጣን ሽግግሮች ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል የመድረስ ፍላጎቶችን አሳይተው ነበር ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራ 55ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በቻርለስ ሉክዋጎ ግብ ከመሆን ድኗል ። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም 62ኛ ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የመታው አስደናቂ ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ።ከሁለተኛው አጋማሽ የውሀ እረፍት መልስ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቀደም ብሎ ከነበረው እንቅስቃሴ በተሻለ ወደ ፊት ለመድረስ የቻሉ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል የተለያዩ ቅያሪዎችን በማድረግ የፈረሰኞቹን የኋላ ክፍል አለፍው ግብ ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል ።
በ80ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዳግም አርአያ ለአማኑኤል ገብረሚካኤል አቀብሎ መልሶ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በሳኩባ ካማራ ተይዞበታል ።
የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ፈረሰኞቹ በቀኝ መስመር በኩል ያገኙትን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ኳሱ ግብ ጠባቂውን ጭምር ካለፈ በኋላ ጀሚል ያዕቆብ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 50 በማድረስ መሪነቱን ሲያጠናክር አዳማ ከተማ በበኩሉ በ26 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 3 ( ረቡዕ ) 10:00 ላይ አዳማ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ረፋድ 4:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ የሚጫወት ይሆናል ።