በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የተገናኘቱት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ በፍፁም ቅጣት ምቶች ባስቆጠሯቸው ግቦች አቻ ተለያይተዋል ።7
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ13ኛው ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ ያደረጉ ሲሆን ቸርነት ጉግሳ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ምትክ በአሰላለፉ የተካተተ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው አሰላለፍ በተመሳሳይ አንድ ቅያሪ ብቻ ያደረጉ ሲሆን በሀቢብ ከማል ምትክ ወርቅይታደስ አበበ በጨዋታው ላይ መሰለፍ ችሏል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተካሄደበት ሲሆን በፈረሰኞቹ በኩል ከኋላ ጀምረው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት አዞዎቹ ወደ ፊት ተጠግተው ጫና በመፍጠራቸው ምክንያት ረጃጅም ኳሶችን አልፎ አልፎ ለመጠቀም የተገደዱ ሲሆን በአርባ ምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ የሚያገኟቸውን ኳሶች ወደ ፊት መስመር በመውሰድ የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ጥረቶች ማድረግ ችለው ነበር።
ጨዋታው ለደቂቃዎች ጠነከር ያለ የግብ ሙከራ ሳይስተናገድበት የቆየ ሲሆን 15ኛው ደቂቃ ላይ ግን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ጋቶች ፓኖም በሳጥን ውስጥ በፀጋዬ አበራ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ 18ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር አዞዎቹን መሪ አድርጓል ።ለማጥቃት በቀኝ መስመር በኩል ማለትም አቤል ያለው በሚገኝበት በኩል በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ የነበሩት ፈረሰኞቹ በ20 እና 21ኛው ደቂቃ ላይ በአቤል ያለው እና እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ አማካኝነት ያደረጎቸው የግብ ሙከራዎች በአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ግብ ከመሆን ድነዋል ።
በ28ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ በቀኝ መስመር አቤል ያለው በረጅም የተላከለትን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ለማግኘት በሚጥርበት ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማው ተከላካይ አሸናፊ ፊዳ ጥፋት ተሰርቶበት ፈረሰኞቹ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን የፍፁም ቅጣት ምቱንም እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ በ30ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ክለቡን አቻ ያደረገ ሲሆን ለራሱም በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን የግቦች ብዛት ወደ 9 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ለብቻው መምራት ጀምሯል ።የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ጊዜ አቤል ያለው በቀኝ መስመር በኩል ያገኘውን ኳስ ወርቅይታደስ አበበን በግል ጥረቱ አልፎ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በሳምሶን አሰፋ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሊሆን ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ፊት ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩበት ሲሆን በአርባ ከተማ በኩል ደግሞ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክፍል በማፈግፈግ በፈጣን ሽግግሮች እና ከቆሙ ኳሶች የተወሰኑ የግብ አጋጣሚዎቾን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
አጋማሹ ሲጀመር ተቀይሮ የገባው ሀቢብ ከማል 60ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ በቀጥታ ሞክሮት የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ። በአጋማሹ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሌላው ሊነሳ የሚችለው ነገር ተደጋጋሚ ጥፋቶች መሰራታቸው ሲሆን የአርባ ምነጭ ከተማው ተጫዋች ሙና በቀለም በፍሪምፖንግ ሜንሱ ጭንቅላቱን ተመቶ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አምርቷል ።
ፈረሰኞቹ ምንም እነኳን ወደ ፊት ሄደው ግብ ለማግኘት የተለያዩ አማራጮችን እየፈለጉ የነበረ ቢሆንም ከራሳቸው ሜዳ በረጅም የሚላኩ ኳሶች በተደጋጋሚ በአርባ ምንጭ ተከላካዮች ይመለሱ የነበረ ቢሆንም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ረጃጅም ኳሰችን ሲጠቀሙ ተመልክተናል ። በአጋማሹ በፈረሰኞቹ በኩል የተደረገው የመጀመሪያ አስቆጪ ሙከራ 65ኛው ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ ከቸርነት ጉግሳ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ ለመቀየር ያደረገው ጥረት ኳሱ ለጥቂት ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ።
በፈረሰኞቹ በኩል ያብስራ ተስፋዬን ተክቶ ወደ ሜዳ መግባት ችሎ የነበረው ቸርነት ጉግሳ በሜዳ ላይ ጥቂት ያህል ደቂቃዎችን ብቻ አሳልፎ ጉዳት አጋጥሞት በተገኑ ተሾመ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ።
ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመስመር በሚነሱ እና በአንድ ሁለት ቅበብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ለመግባት ሙከራዎችን አድርገዋል ። 78ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌማን ሀሚድ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሳምሶን አሰፋ ወጥቶ መለሰው እንጂ አጥቂው ኦሮ ኦጎሮ ኳሱን አግኝቶ ለማስቆጠር በጥሩ አቋቋም ላይ ነበር ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም የጋቶች ፓኖም እና ቸርነት ጉግሳ ቅብብል ወደ ሳጥን መዝለቅ ቢችልም በአርባ ምንጭ ከተማ ተከላካዮች ወደ ውጪ ሊወጣ ችሏል ።
በዘንድሮው አመት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ አሳሳቢ ከሆኑት እኛም በጨዋታ ዘገባዎቻችን በተደጋጋሚ ስናነሳው የነበረው የመስመር ዳኞች ከጨዋታ ውጪ ውሳኔ አሰጣጥ ስህተት በዚህ ጨዋታም ታይቷል ። 85ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ ያገኙትን የማዕዘን ምት እዛው በመጀመር በሄኖክ አዱኛ አማካኝነት ወደ ግብ ክልል የተሻገረው ኳስ ኦሮ ኦጎር አግኝቶት ለቸርነት ጉግሳ አቀብሎት ግቡ መቆጠር ቢችልም የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጫ በማለት ሽሮታል ። በውሳኔው የተበሳጩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በዳኛው ውሳኔ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን የሊጉ አስተዳደርም በዳኞች የመዳኘት አቅም እና ብቁነት ላይ በአንክሮ መስራት እንደሚገባው ያሳየ ሁነት ሆኖ አልፏል ። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 28 በማድረስ መሪነቱን ያስቀጠለ ሲሆን አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ ነጥቡን 17 በማድረስ በግብ ክፍያ በመበልጥ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።
በ15ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ከተማን አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ከሰበታ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል ።