የ19ኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲጀመሩ በቅድሚያ የተደረገው የመሪው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የመከላከያ ጨዋታ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ18ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ የነበረው ምርጥ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆግ በመከላከያ በኩል ደግሞ በሳምንቱ በአዲስ አበባ ከተማ ሲሸነፉ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ቅያሪ በማድረግ ገናናው ረጋሳን እና ልደቱ ጌታቸውን በብሩክ ሰሙ እና አሚን ነስሩ ምትክ አሰልፈዋል ።ጨዋታው አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ እና ኳሶች ወደ ግብ ደርሰው የግብ ሙከራዎችን ለመመልከት ደቂቃዎችን ያስጠበቀ ነበር ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአጋማሹ በተለይም በቀኝ መስመር በኩል አድልተው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። በአንፃሩ በመከላከያ በኩል የኋላ ክፍላቸውን በማጠናከር በመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች የግብ አጋጣሚዎችን ለማግኘት ሙከራዎችን አድርገዋል ።
17ኛው ደቂቃ ላይ ተሾመ በላቸው ምኞት ደበበን በሳጥን ውስጥ በማለፍ የቀነሰውን ኳስ ቢንያም በላይ ማግኘት ሳይችል ሲቀር ከጀርባው የመጣው ግሩም ሀጎስ ወደ ግብ የላከው ኳስ በፈረሰኞቹ የቀኝ መስመር ተከላካይ ሱሌማይ ሀሚድ ተደርቦ ወጥቷል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ በቅዱስ ጉዮርጊስ በኩል የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ተደርጓል ። ያብስራ ተስፋዬ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ ነፃ ለነበረው አቤል ያለው ቀንሶለት የነበረ ሲሆን የአቤል ኳስ ግን በክሌመንት ቦዬ ተመልሷል ። ከዚህ ሙከራ በኋላ ፈረሰኞቹ ይበልጥ ኳሱን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ከመከላከያ የተሻሉ ሆነው ቢታዩም የተጋጣሚያቸውን የኋላ መስመር አልፈው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ግን ተቸግረው ቆይተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ከአቤል ያለው ሙከራ በኋላ ቀጥሎ የታየው ጥሩ የግብ ሙከራ 32ኛው ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ያሻገረው ኳስ በጋቶች ፓኖም ተገጭቶ ኢላማውን ጠብቆ ወደ ግቡ ቢሄድም ክሌመንት ቦዬ አድኖታል ።
ፈረሰኞቹ ወደ ማጥቃቱ ሶስተኛ ክፍል ለመድረስ በመስመር በኩል ወደ ሳጥን መግባት ፤ ከቆሙ ኳሶች በሚፈጠሩ እድሎች እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ግብ ለማግኘት ቢጥሩም በዕለቱ ድንቅ በነበረው ግብ ጠባቂው እና በመከላከያ የተከላካይ ክፍል ተጫዋቾች ጥረት ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል ።
በ40ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ አራት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ፍሪምፖንግ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በድጋሚ በክሌመንት ቦዬ ተመልሶ ዳግም የማዕዘን ምት ሆኗል ።
መከላከያ በአጋማሹ ያደረጉት ብቸኛው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 44ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን በተነሳ ኳስ በምንተስኖት አዳነ አማካኝነት ሲሆን ሙከራወም በቻርለስ ሉክዋጎ በቀላሉ ተይዟል ።በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ 45ኛ ደቂቃ ላዬ ጋቶች ፓኖም ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረው ኳስ በአማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባር ተገጭቶ የነበረ ቢሆንም የግቡ አግዳሚ መልሶታል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሜዳ ላይ የበላይነታቸውን አጠናክረው በማስቀጠል ግብ ለማግኘት የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል ደጋግመው ቢያንኳኩም ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ የዕለቱ ድንቅ ብቃት የሚቀመስ አልነበረም ።
በአጋማሹ የተደረገው ቀዳሚ ሙከራ በአማኑኤል ገብረሚካኤል የተደረገ ሲሆን ተጫዋቹ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ዘቡ ተመልሷል ። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ፈረሰኞቹ ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር ።አማኑኤል ገብረሚካኤል በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ መሬት ለመሬት ለአቤል ያለው ጥሩ ኳስ ቀንሶለት አቤል አስቆጠረው ተብሎ ቢጠበቅም አጥቂው ራሱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ኳሱን ወደ ግብነት መቀየር ሳይችል ቀርቷል ። በ62ኛው ደቂቃ ላይ በሄኖክ አማካኝነት ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የተመታው ኳስ ኢላማውን የጠበቀ ቢሆንም በግቡ ቋሚዎች መሀል የቆመውን 1 ቁጥር ለባሽ ማለፍ የቻለ አልነበረም ።
መከላከያዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው የቅዱስ ጊዮርጊስን የማጥቃት ሂደት በማቋረጥ ተጠምደው አጋማሹን የቀጠሉ ሲሆን አልፎ አልፎም በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለማለፍ የሚያዳርጓቸው ጥረቶች የተሳኩ አልነበሩም ።በ70ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ፍሪምፖንግ ኤድዊን በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግልፅ የግቡን መስመር አልፎ የነበረ ቢሆንም ግቡ ሳይፀድቅ ቀርቷል ። በውሳኔው የተበሳጩት የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች በተለይም በረዳት ዳኛው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።
ከዚህ ሁነት ሁለት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ከቆመ ኳስ የተሻገረን ኳስ ፍሪምፕንግ በድጋሚ አግኝቶ ወደ ግብ ቢልከውም የግቡ አግዳሚ አውጥቶበታል ።
የሊጉ መሪ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም አሸናፊ የሚያደርጋቸውን ግብ ፍለጋ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም አጨራረስ ላይ የነበረው ድክመት እና በጨዋታው ልዩ በነበረው የመከላከያ ግብ ጠባቂ አማካኝነት ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ተቸግረዋል ። በተለይም 5 ያህል ደቂቃዎች ተጨምረው 90+4 ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ በረጅም የመታውን ኳስ አዲስ ግደይ ገጭቶ ከግቡ ትይዩ ነፃ ሆነው ቆመው ከነበሩት ሶስቱ ፈረሰኞች አንዱ የነበረው ምኞት ደበበ ኳሱን አረጋግቶ ወደ ግብ መምታት ቢችልም ጋናዊው ግብ ጠባቂ ኳሱን በድጋሚ በማዳን መረቡን ሳያስደፍር ጨዋታውን ማጠናቀቅ ችሏል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 41 በማድረስ ከወላይታ ድቻ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 9 ከፍ ሲያደርግ መከላከያ በበኩሉ በ20 ነጥብ በነበረበት 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።በ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው ቅዳሜ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡናን ሲገጥም በማግስቱ በተመሳሳይ ሰዓት ላይ ደግሞ መከላከያ ባህርዳር ከተማን ይገጥማል ።