በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የሊጉን መሪ ቅዲስ ጊዮርጊስን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ ፈረሰኞቹ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው መውጣት ችለዋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ17ኛው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በረቱበት ጨዋታ የነበረውን ምርጥ 11 ሙሉ ለሙሉ ሲጠቀሙ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከሲዳማ ቡና ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በመሳይ ጳውሎስ ፣ በአቤል አሰበ እና አቤል ከበደ ምትክ ከድር ኸይረዲን ፣ ዳንኤል ሀይሉ እና ጋዲሳ መብራቴን ተክተው ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
በፈጣን እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከፊት በፈጣን ወደ ፊት በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል አልፎ አልፎ በተመሳሳይ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን ቢያደርጉም የፈረሰኞቹን የኋላ ክፍል ለማለፍ ከባድ ሆኖባቸው ነበር ።
ልክ እንደመጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ በ17ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚው ግብ ተቆጥሯል ። ሄኖክ አዱኛ ከርቀት ወደ ግብ ያሻገረው ኳስ ተጨርፎ ያገኘው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባር በመግጨት ፈረሰኞቹን ቀዳሚ አድርጓል ።
- ማሰታውቂያ -
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ከማዕዘን የተነሳ ኳስ በድሬዳዋ ተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ያብስራ ተስፋዬ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ተይዟል ።
ግብ ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች ኳሱኝ ከራሳቸው ሜዳ ጀምሮ እየተቀባበሉ በመውጣት ወደ ማጥቃቱ ሶስተኛ ዞን ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት በተደጋጋሚ ይከሽፍባቸው ነበር ።
በፈረሰኞቹ በኩል ከግቡ በኋላ በሁለቱ መስመሮች በኩል ወደ ሳጥን በመግባት እንዲሁም ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች በሚሻገሩ ኳሶች ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል ። በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይም ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ፍሪምፖንግ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ ተቆጥሯል ። ፈረሰኞቹ ከሳጥኑ የቅርብ ርቀት ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ፍሪምፖንግ ሜንሱ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ማራኪ ግብ አስቆጥሯል ። ይህም ግብ በጨዋታው ላይ ለተጫዋቹ ሁለተኛ ግቡ ሲሆን በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን ግቦች ደግሞ አራት አድርሷል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው የነበረ ሲሆን በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሰው ኳስ በያብስራ ተስፋዬ አቀባይነት በአማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ግብ ቢሞከርም ፍሬው ጌታሁን አድኖታል ። በ63ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ያለው በቀኝ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ለጋቶች ፓኖም ቢቀንስለተም ጋቶች የመታው ኳስ በእንየው ካሳሁን ተደርቦ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በ66ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው የግራ መስመር ተከላካይ መሀመድ አብዱለጢፍ በሀይደር ሸረፉ ላይ በሰራው ጥፋት ሁለተኛ የቢጫ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
በ75ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ለከንአን ማርክነህ ያቀበለው ኳስ ያብስራ ተስፋዬ ጋር ደርሶ አቤል ያለው ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ መቶ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ 3 ለ 0 ከፍ አድርጓል ።
የግብ ሙከራ ማድረግ የተሳናቸው ድሬደዋ ከተማዎች በ85ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው የነበረ ሲሆኖ አቤል አሰበ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሲመለስ በቅርብ የነበረው አብዱራህማን ሙባረክ በድጋሚ ወደ ግብ ቢሞክረውም የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ዳግም አድኖታል ። በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ላይ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ከንአን ማርክነህ ነፃ ሆኖ አግኝቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በአማረ ተመልሶ ግብ ከመሆን ድኗል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 40 በማድረስ መሪነቱን ሲያጠናክር ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ17 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል ።
በ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው ዕህድ ቀን 9 ሰዓት ላይ መከላከያን ሲገጥም ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በማግስቱ በተመሳሳይ ሰዓት ጅማ አባጅፋርን ይገጥማል ።