በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ በቅድሚያ የተደረገው የሊጉ መሪ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ13ኛው ሳምንት ወልቂጤ ከተማን በሰፊ ውጤት ሲያሸንፉ በተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን በሀድያ ሆሳዕና በኩል በሳምንቱ ሰበታ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ሚካኤል ጆርጅን በኤፍሬም ዘካርያስ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍል ጊዜ በአመዛኙ ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በመሀል ክፍል ላይ የበላይነትን ለመውሰድ በሁለቱም በኩል ፍላጎቶች የተስተዋሉበት ነበር ። በቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ወደ ግብ ክልል ደርሰው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጓቸው ጥረቶች በተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሲበላሹ ቆይተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የፈረሰኞቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ በብዛት በቀኝ መስመር በኩል አድልቶ የተከናወነ ሲሆን በዚህም
በ18ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ለእስማኤል ኦሮ ኦጎሮ በአየር ያሻገረለትን ኳስ ሳይደርስበት ቀርቷል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ምኞት ደበበ ኳስ ሸፍኖ ለማስወጣት ሲሞክር ባዬ ገዛኸኝ ነጥቆት የነበረ ቢሆንም ባዬ የቀነሰውን ኳስ የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ሊደርሱበት አልቻሉም ።
ከውሀ እረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ጋቶች ፓኖም ለአቤል ያለው በረጅም ያደረሰውን ኳስ አቤል በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ቢችልም በግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ተመልሷል ። ሀድያ ሆሳዕናዎች የቅዱስ ጊዮርጊሶችን እንቅስቃሴ በመግታት ወደ ፊት ሄደው ጫና ለመፍጠር በአንፃራዊነት የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረቶችን ቢያደርጉም ወደ ሳጥን ገብተው ሙከራዎችን ለማድረግ ግን አልቻሉም ነበር ። ቡድኑ በአጋማሹ ያደረገው ጥሩ ሙከራ 35ኛ ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን የቀድሞው ፈረሰኛ ተስፋዬ አለባቸው ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በቻርለስ ሉክዋጎ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
37ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ በጉዳት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ በሀብታሙ ታደሰ ተቀይሮ ወቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለግብ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን የተጋጣሚያቸውን የመከላከል መስመር ግን ሰብረው ለመግባት ተቸግረው ነበር ። 50ኛ ደቂቃ ላይም ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሊያዝ ችሏል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከኋላ መስርተው ለመውጣት በሚሞክሩበት ጊዜ በተደጋጋሚ እየተነጠቁ የነበረ ቢሆንም ሀድያ ሆሳዕናዎች የሚቀሟቸውን ኳስ በአግባቡ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል ። ፈረሰኞቹ ቀስ በቀስ እንቅሰቃሴያቸውን በማሻሻል ወደ ፊት ለመድረስ የሞከሩ ሲሆን በተለይም ከቀኝ በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ፍሬያማ ግን አልነበሩም ።
65ኛ ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ያሻገረው ኳስ ተቀይሮ የገባው ቸርነት ጉግሳ ጋር ቢደርስም ቸርነት ዕድለን ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በቁጥር በርከት ብለው በመከላከል ላይ የተጠመዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሚፈጠሩ የግብ አማራጮችን ከማምከን ባለፈ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ላይ ኳሶችን በፈጣን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመላክ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገው ነበር ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት በሁለቱም በኩል በጣም ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን ማግኘት የቻሉበት ነበር ። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ከሄኖክ አርፊቹ በረጅም የተላከው ኳስ በሚካኤል ጆርጅ እና ሀብታሙ ታደሰ በኩል አልፎ ለፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ደርሶት የነበረ ቢሆንም ናትናኤል ዘለቀ እና ቻርለሰ ሉክዋጎ ተረባርበው ኳሱን አድነዋል ። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ አላዛር ሽመልስ በሳጥን ውስጥ ለአማኑኤል ገብረሚካኤል የቀነሰለትን ኳስ አማኑኤል ወደ ግብ ሞክሮት በብርሀኑ በቀለ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። በመጨረሻም የጨዋታው ውጤት ቅዱስ ጊዮርጊስ 0 ሀድያ ሆሳዕና 0 ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 27 በማድረስ በደረጃው አናት ላይ ሲቀጠል ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ነጥቡን ወደ 17 ከፍ ማድረግ ቢችልም በደረጃው ላይ ለውጥ ሳያሳይ 10ኛ ላይ ተቀምጧል ።
በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ወላይታ ድቻን የሚገጥሙ ይሆናል ።