በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ሲሆኑ ከነአን ማርክነህ በ81ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ግብ ፈረሰኞቹ 1 ለ 0 አሸንፈው ወተዋል ።
ቅዱር ጊዮርጊሶች በስምንተኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አስራአንድ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ቸርነት ጉግሳ ወደ ጨዋታው ሲያስገቡ በጅማ አባጅፋር በኩል በሰበታ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ተጫዋቾችን የቀየሩ ሲሆን ተጫዋቾቹም ተስፋዬ መላኩ ፤ ሽመልስ ተገኝ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ናቸው ።
ጨዋታው በውድድር አመቱ ምንም ሽንፈት ባላስተናገደው እና ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ባልቻለው ቡድን መካከል የተደረገ ነበር ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በጣም ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ነበር ። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በተጋጣሚ ሜዳ ላይ በዝተው በመገኘት እና በጅማ አባጅፋር ተከላካዮች ላይ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል አልፎ አለፎ ከሜዳቸው ወተው ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት በፈረሰኞቹ ተከላካዮች በቀላሉ ይነጠቁ ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በተወሰኑ አጋጣሚዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ጅማ አባ ጅፋር የግብ ክልል በማድረስም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ አልነበሩም ። ፈረሰኞቹ በአጋማሹ ያገኙት ጥሩ ዕድል 11ኛ ደቂቃ ላይ ሲሆን ሱሌይማን ሀሚድ ከአቤል ያለው የተቀበለውን ኳስ በሳጥኑ ቀኝ በኩል ሆኖ ወደ ግብ የላከውን ኳስ እስማኣኦሮ ጎሮ ሳይደርስበት ቀርቶ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
ከዚህኛው የግብ ዕድል ውጪ ያን ያህል ለግብ የቀረበና ግብ ጠባቂዎችን ያስጨነቀ የግብ ሙከራ በሁለቱም በኩል ሳይደረግ ነበር የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው ።
የሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴን የተደረገበት ነበር ። በተለይም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ኳሶችን በመላክ ግብ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል ። በኳስ ቁጥጥሩም ቢሆን የበላይነትን ወስደው በመጫወት ላይ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የጅማ አባጅፋርን ተከላካይ መስመር ሰብረው ለመግባት ያደረጓቸው ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ጋር ሳይደርስ በተከላካዮች ይመለስ ነበር ።
በጅማ አባጅፋር በኩል በመልሶ ማጥቃት እና የሚቀሟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ አጥቂ መስመር ተጫዋቾች በመላክ የፈረሰኞቹን ተከላካዮች በተወሰነ መልኩ ለመፈተን ሞክረዋል ።
በ55ኛ ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች በመልሶ ማጥቃት በፍጥነት በመግባት መሀመድ ኑር ናስር ግብ ቢያስቆጥርም ግቡ ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል ። ነገር ግን ለመሀመድኑር ናስር የደረሰው ኳስ በጅማ አባጅፋር ተጫዋች ሳይሆን በቅዱስ ጊዮርጊሱ ያብስራ ተስፋዬ ተነክቶ ነበር ወደ እሱ የደረሰው በዚህም የአባ ጅፋር ተጫዋቾች ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል ።
ያለ ግብ የቀጠለው ጨዋታ 77ኛ ደቂቃ ላይ የስታድየሙ መብራቶች በመጥፋታቸው ምክንያት ለ12 ያህል ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር ።
በ81ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ በቀኝ መስመር ያገኙኝትን የቅጣት ምት ቡልቻ ሹራ ለሀይደር ሸረፋ ያቀበለው ሲሆን ሀይደርም ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ከነአን ማርክነህ በግንባር ገጭቶ አስቆጠረ ። ነገር ግን ግቡ ሲቆጠር የከነአን ማርክነህ አቋቋም አከራካሪ ነበር ።
የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በከፍተኛ ግለት የተካሄዱ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 17 በማደረስ እና ከፋሲል ከተማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ በማጥበብ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ያሉ ሲሆን በዘጠኝ ሳምንታት የሊጉ ጨዋታ ዎች ምንም ማሸነፍ ያልቻሉት እና 1 ነጥብ ብቻ የያዙት ጅማ አባጅፋሮች የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል ።