በ18ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቅድሚያ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና የአዳማ ከነማ ጨዋታ ግብ ሳያስተናንድ በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ወላይታ ድቻ በ17ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጠሰ ብቻ በማድረግ በእንድሪስ ሰይድ አበባየሁ አጪሶን በ ተክተው ሲገቡ በአዳማ ከተማ በኩልም በሳምንቱ ከጅማ አባጅፋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ በዮሴፍ ገረመው ምትክ ታደለ መንገሻን አሰልፈዋል ።በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተጀመረው የወላይታ ድቻ እና የአዳማ ከነማ ጨዋታ ላይ አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ላይ ለመቆየት የቻሉበት ነበር ። ምንም እንኳን ወደ ፊት በመድረስም ሆኖ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው በኳስ ቁጥጥሩም ከወላይታ ድቻ የተሻሉ ሆነው ቢጀምሩም በመከላከል ጥንካሬው የማይታማውን የወላይታ ድቻን የኋላ ክፍል አልፈው ለመግባት እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ።
በወላይታ ድቻ በኩል አልፎ አልፎ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በዚህም 17ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም በረጅም የደረሰውን ኳስ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ ማግኘት ችሎ ግብ ጠባቂውን ጀማል ጣሰውንም ጭምር ማለፍ ቢችልም ጀማል ከወደቀበት ዳግም ተነስቶ ቃልኪዳን ኳሱን ወደ ግብ ለመምታት ያደረገውን ሙከራ ተደርቦ መልሶበታል ።በ21ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከነማዎች ከሳጥን ውጪ በአማኑኤል ጎበና አማካኝነት ያደረጉት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ግብ ከመሆን ድኗል ።
በአንፃራዊነት ከውሀ እረፍት መልስ ጥሩ መንቀሳቀስ ችለው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች 27ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ከተነሳ ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ማግኘት ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ያሬድ ዳዊት ከአበባየሁ አጪሶ የተሰነጠቀለትን ግሩም ኳስ ወደ መሀል ለማሻገር ሲሞክር በቀላሉ ጀማል ጣሰው ይዞበታል ።
ሁለተኛውን አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች ተነቃቅተው የጀመሩት ሲሆን በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ወደ አዳማ ከነማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገዋል ። 51ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ያሻገረው እና ቃልኪዳን ዘላለም በግንባር ገጭቶ የሞከረው ኳስ ለዚህ ተጠቃሽ ነው ።ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ቃልኪዳን ዘላለም በግራ መስመር በኩል ወደ ግብ የቀነሰውን ኳስ ጀማል ወጥቶ ይዞበታል ።
አዳማ ከነማዎች በአጋማሹም ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ ቀዳሚ የግብ ሙከራቸውን በአማኑኤል ጎበና አማካኝነት ያደረጉ ሲሆን ኳሱን ፅዮን መልሶት የማዕዘን ምት ሆኗል ። የማዕዘን ምቱ ሲሻገር ሚሊዮን ሰለሞን ነፃ ሆኖ አግኝቶ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ።
አዳማ ከነማዎች ቀስ በቀስ ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና የወላይታ ድቻን የኋላ ክፍል ለማስከፈት ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ፍሬያማ መሆን አልቻሉም ።
በ65ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የማጥቃት ሀይላቸውን ለማጠናከር ሶስት ቅያሪዎችን በአንድ ጊዜ ማድረግ ቢችሉም ቅያሪዎቹ በሜዳ ላይ የነበራቸው ተፅዕኖ ያን ያህል ነበር ።በወላይታ ድቻ በኩል በ80ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ በያሬድ ዳዊት አማካኝነት ካደረጉት እና በጀማል ጣሰው ከተያዘው ኳስ ውጪ ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ። በመጨረሻም ጨዋታው ግብ ሳይስተናገድበት 0 – 0 ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 33 በማድረስ በ2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥል አዳማ ከነማ በበኩሉ ነጥቡን 24 በማድረስ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል ።
በ19ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ በመጪው ሰኞ አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ አዳማ ከነማ ደግሞ በማግስቱ ቀን 9 ሰዓት ላይ ሀድያ ሆሳዕናን ይገጥማል ።