የ14ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ከሀድያ ሆሳዕና አገናኝቶ ስንታየሁ መንግስቱ በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ የጦና ንቦቹ ሙሉ ሶሰት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል ።ወላይታ ድቻዎች በ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በጅማ አባጅፋር በተረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ፅዮን መርዕድ ፣ መልካሙ ቦጋለ ፣ ያሬድ ዳዊት እና እንድሪስ ሰኢድ ወንድወሰን አሸናፊን ፣ በረከት ወልደዮሀንስን አዲስ ህንፃን እና ቃልኪዳን ዘላለም ተክተው የገቡ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናዎችም ከቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው አሰላለፍ በተመሳሳይ አራት ለውጦችን በማድረግ ኤልያስ አታሮ ፣ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ሐብታሙ ታደሰ እና ፀጋዬ ብርሀኑ በፍሬዘር ካሳ ፣ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ፣ ኢያሱ ታምሩ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች በብዛት ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ፊት ለመድረስ የሞከሩ ሲሆን በዚህም በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ይሆኑ ነበር በአንፃሩ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመድረስ የቻሉ ሲሆን ከሳጥን ውጪ ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ግብ ይሞክሩ ነበር ።
ከነዚህም ውስጥ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ተጠቃሽ ነው ። የወላይታ ድቻ ተከላካዮች ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀላሉ ወደ ሳጥናቸው እንዳይገቡ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ወደ ፊት በመሄድ ደከም ብለው ቆይተው በ44ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርገው ነበር ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ እንድሪስ ሰይድ ከቅጣት ምት ወደ ግብ በቀጥታ የመታውን ኳስ መሳይ አያኖ አድኖበታል ።የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ከግራ መስመር በረጅም የተላከለትን ኳስ ቁመታሙ አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ ዘሎ በግንባር በመግጨት የጦና ንቦቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል ።በሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛውን የጨዋታ ብልጫ ሀድያ ሆሳዕናዎች የወሰዱ ሲሆን ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች ግን በጠንካራው የጦና ንቦቹ መከላከል ምክንያት ፍሬያማ ሊሆንላቸው አልቻለም ። ወላይታ ድቻዎች አጋማሹን በጥብቅ መከላከል የጨረሱ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች የሚነጠቁ ኳሶችን በረጅም ወደ ፊት በመላክ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
አጋማሹ እምብዛም የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ሲሆን በሃድያ ሆሳዕና በኩል 75ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አበባየሁ ከቅጣት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በፅዮን መርዕድ የተመለሰ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሌላው ተቀይሮ የገባው ኡመድ ኡክሪ የወላይታ ድቻውን ተጫዋች አናጋው ባደግን አደገኛ ቀጠና ላይ ቀምቶት ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ የመታው ኳስ በፅዮን መርዕድ ተመልሶበታል ።
በመጨረሻም ወላይታ ድቻ ጨዋታውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችሏል ።ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 25 በማድረስ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ በ17 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።በ15ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ ወልቂጤ ከተማን ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ሲዳማ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል ።
- ማሰታውቂያ -
የ15ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ከመጪው እሁድ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ ተከናውነው የሊጉ የመጀሪያዉ ዙር ከመጠናቀቁ ይሆናል ።