በ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቅድሚያ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ እዮብ አለማየሁ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ጅማ አባጅፋሮች አሸንፈዋል ።
ወላይታ ድቻ በ13ኛው ሳምንት መከላከያ በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው የገቡ ሲሆን በያሬድ ዳዊት ምትክ ምንይሉ ወንድሙ የመሰለፍ ዕድልን ያገኘ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ በሳምንቱ በሲዳማ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሶሰት ቅያሪዎቸን በማድረግ አላዛር ማርቆስ ፣ አዛህሪ አልመሀዲን እና ዳዊት ፍቃዱን በማሰለፍ ዮሀንስ በዛብህ ፣ በላይ አባይነህ እና ዱላ ሙላቱ በተቀያሪ ወንበር አስቀምጠው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለቱም በኩል በሚደረግ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የሚደርሱበት ነበር ። ጅማ አባጅፋሮች ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ግብ ለመቅረብ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ በረጃጅም እና ፈጣን ኳሶች የጅማ አባጅፋርን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ችለዋል ።
ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን ለማስመልከት ደቃቃዎችን ያስጠበቀው ይህ ጨዋታ 16ኛው ደቂቃ ላይ በወላይታ ድቻ በኩል ጥሩ የግብ ዕድል አሰመልክቶናል ። ከወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል በረጅም የተላከውን ኳስ በስንታየሁ መንግስቱ ተገጭቶ የደረሰው ቃልኪዳን ዘላለም በሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው አላዛር ሽመልስ ተመልሷል ። ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላ ከምንይሉ የደረሰውን ኳስ ለግቡ ትይዩ የነበረው ስንታየሁ መንግስቱ አክርሮ ቢመታውም በድጋሚ በአላዛር ተመልሷል ። በተከታታይ ደቂቃዎች ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን ያመከነው የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ አላዛር ሽመልስ በ22ኛው ደቂቃ ላይም በቃልኪዳን ዘላለም የተሞከረበትን ኳስ በማምከን ቡድኑን ታድጓል ።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት ለማለፍ ሲታትሩ የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች ቀስ በቀስ በጦና ንቦቹ በተፈጠረባቸው ጫና ወደ ኋላ ለመመለስ የተገደዱ ሲሆን በ34ኛው ደቂቃ ላይ ግን የነጠቁትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመውሰድ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል ። በፈጣን የመጣለትን ኳስ በግራ መስመር የነበረው መሀመድኑር ናስር በጥሩ ሁኔታ ለእዮብ አለማየሁ አቀብሎት እዮብ ማስቆጠር ችሏል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በጅማ አባጅፋር መሪነት ተጠናቋል ።
ጅማ አባጅፋሮች የሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ መልኩ መጀመር አልቻሉም ነበር ። ለግቡ መቆጠር አስተዋፅኦ ያበረከተውን የአጥቂ መስመር ተጫዋቻቸውን መሀመድኑር ናስርን በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን መቀጠል ያልቻለ ሲሆን ምስጋናው መላኩ ተክቶት ገብቷል ። በአጋማሹ በመመራት ላይ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው የአቻነቱን ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉበት ቢሆንም ወደ ጅማ አባጅፋር የግብ ክልል የሚደርሱ ኳሶች በቀላሉ በተከላካዮች ይመለሱ ነበር ። በጅማ አባጅፋር በኩልም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል ከመድረሳቸው ውጫ አብዛኛውን ጊዜ በመከላከሉ ላይ አተኩረው ተጫውተዋል ።
ምነም እንኳን የጦና ንቦቹ ወደ ጅማ አባጅፋር የግብ ክልል ከመስመር በሚነሱ እና በረጅም ወደ ሳጥን በሚላኩ ኳሶች ወደ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ነበር ሁለተኛውን አጋማሽ ያጠናቀቁት ። በጅማ አባጅፋር በኩል በ90+2 ላይ በእዮብ አለማየሁ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም እዮብ በግብ ጠባቂው አናት ላይ አሳልፎ የነበረውን ኳስ በረከት ወልደዮሀንስ ደርሶ አውጥቶታል ። በመጨረሻም ጅማ አባጅፋሮች በ1 ለ 0 ውጤት አሸንፈው ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር ነጥቡን 10 በማድረስ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ጉዞ የቀጠለ ሲሆን ወላይታ ድቻ በበኩሉ በ22 ነጥብ ባለበት 4ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ሀድያ ሆሳዕናን ጅማ አባጅፋር ደግሞ ወልቂጤ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።