በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት እንዲሁም የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ እና በወላይታ ድቻ መካከል ተደርጎ በጦና ንቦቹ የአንድ ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ14ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ያሸነፉት ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታው ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ዮናታን ፍስሀን በበሀይሉ ተሻገር ተክተው ያስገቡ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩልም ሀድያ ሆሳዕናን በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው አሰላለፍ አንድ ቅያሪ ብቻ ያደረጉ ሲሆን ቃልኪዳን ዘላለም ምንይሉ ወንድሙን ተክቶ ገብቷል ።የመጀመሪያው የጨዋታው አጋማሽ ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሁለቱም በኩል ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
በጨዋታው 2ኛ ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም በረጅም የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ። ወላይታ ድቻዎች አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት በመላክ የግብ አማራጮችን ለመፍጠር ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። በወልቂጤ ከተማ በኩል በ6ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ በመቀስ ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ በቀላሉ በግብ ጠባቂው ተይዟል ።ወላይታ ድቻዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ለሳጥኑ በቅርብ ርቀት ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት የፊት አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ አክርሮ ወደ ግብ መቶት በግቡ ቋሚ ተመልሷል ። ወላይታ ድቻዎች ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫ በመውሰድ መጫወት ቢችሉም ወደ ማጥቃቱ የሶስተኛ ክፍል ገብተው የግብ ዕድሎችን ለማድረግ ተቸግረው ነበር ።
የጦና ንቦቹ 37ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚን መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። ቃልኪዳን ዘላለም በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ያገኘውን ኳስ ነፃ ለነበረው እንድሪስ ሰይድ ቢያቀብለውም እንድሪስ የመታው ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቀቀ ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች መሀል ላይ መነጣጠቆች የበዙበት ሲሆን ኳሶች ወደ ግብ ደርሰው የግብ ሙከራዎች በቀላሉ ማድረግ አልቻሉም ነበር ። 62ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ኢላማውን ስቶ ወደ ውጪ የወጣው ኳስ በአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር ።
ከውሀ እረፍት መልስ 73ኛ ደቂቃ ላይ ግን የጦና ንቦቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። እንድሪስ ሰይድ ለያሬድ ዳዊት ለማቀበል የሞከረው ኳስ በረመዳን የሱፍ ሲመለስ ያገኘው ስንታየሁ መንግስቱ ኳሱን አክርሮ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ። ከግቡ በኋላ ወልቂጤ ከተማዎች ጫን ብለው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን በተለይም ከግራ መስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ አማራጮችን ለመፍጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ከወላይታ ድቻ ተከላካዮች ማለፍ ግን አልቻሉም ።
በ84ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ወላይታ ድቻዎች ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር በዚህ አጋጣሚ ተቀይሮ የገባው አበባየሁ አጭሶ በጭንቅላት ገጭቶ ለያሬድ ዳዊት ያቀበለውን ኳስ ያሬድ ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ሰይድ ሀብታሙ አድኖታል ። በመጨረሻም ጨዋታው በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 28 በማድረስ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በበከሉ ወደ በ20 ነጥብ ባለበት የግብ ዕዳ ወደ 9ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።
በ16ኛው ሳምንት ( አዳማ ከተማ ) ወልቂጤ ከተማ አዳማ ከተማን ወላይታ ድቻ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።