በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን ከአስተናጋጁ ከተማ ክለብ አዳማ ከተማ አገናኝቶ ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ከእረፍት በፊት በተቆጠሩ ግቦች ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
ወልቂጤ ከተማ በ15ኛው ሳምንት በወላይታ ድቻ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን አበባው ቡጣቆ ፣ በሀይሉ ተሻገር እና ያሬድ ታደሰን ወደ ቋሚ አሰላለፍ በመመለስ ጨዋውን የጀመሩ ሲሆን አዳማ ከተማ ደግሞ በሳምንቱ ከሀዋሳ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ በተመሳሳይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ዮሴፍ ዮሀንስ ፣ ዮናስ ገረመው እና ኡበበከር ወንድሙን ጨዋታውን እንዲጀምሩ አድርገዋል ።
ጨዋታው ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የተካሄደ ነበር ። በተለይም በከተማቸው እና በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ፊት የተጫወቱት አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆነው ወደ ፊት ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት የአዳማ ከተማን የተከላካይ መስመር አልፈው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር ።
በአጋማሹ ኳሶች በፈጣን እንቅስቃሴ ላይ የቆዩ ቢሆንም ግብ ጠባቂዎችን የፈተኑ የግብ ሙከራዎችችን ለማየት ደቂቃዎችን መጠበቅ የግድ ብሎ ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በ26ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሀንስ ኳስ ወደ ኋላ ለመመለስ በሚሞክርበት ጊዜ በበሀይሉ ተሻገር ተጨርፎ ጌታነህ ከበደ ጋር የደረሰውን ኳስ የረጅም አመታት የብሄራዊ ቡድኑ አጥቂ በጥሩ አጨራረስ ወልቂጤ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል ።
በተሻለ ወደ ፊት መድረስ ቢችሉም ቀድመው ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ለተቆጠረባቸው ግብ መልስ ለመስጠት አምሰት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁባቸው ። በ31ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳ ኳስ በወልቂጤ ተከላካይ ሲመለስ ያገኘው አቡበከር ወንድሙ ተረጋግቶ ወደ ግብ ክልል ያሻማውን ኳስ የመሀል ተከላካዩ አዲስ ተስፋዬ በግንባር ገጭቶ በሰይድ ሀብታሙ መረብ ላይ በማሳረፍ አዳማ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል ።
ጨዋታው ውጤተለ ወደ አቻ ከተቀየረ በኋላም በፈጣን እንቅስቃሴ የቀጠለ ነበር ። በ34ኛው ደቂቃ ላይ ቶማስ ስምረቱ ለመቆጣጠር የተቸገረውን ኳስ ያገኘው ጫላ ተሺታ ከግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ወደ ግብ የመታው ኳስ በጀማል ጣሰው ተመልሷል ። ጀማል የመለሰውን ኳስ ለመያዝ ሲሞክር ኳሱን ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጅ በመንካቱ የቢጫ ካርድ ተመልክቷል ።
ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላ ጀማል ጣሰው ከአዲስ ተስፋዬ ወደ ኋላ የተመለሰለትን ኳስ ከግብ ለማራቅ ሲሞክር ኳሱ ተጨርፎ አምልጦት የነበረ ሲሆን ጫላ ኳሱ ላይ ለመድረስ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ቶማስ ስመረቱ ደርሶ አውጥቶታል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ተካሂዶ አንድ ለአንድ ተጠናቋል ።
የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ለአይን ሳቢ የሆን እንቅስቃሴ የታየበት ነበር ። በአጋማሹ በፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራዎች ከተጋጣሚያቸው በልጠው ያሳለፉበት ነበር ።
በ50ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ጎበና ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ዮናስ ገረመው በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም በዕለቱ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያድን የነበረው ሰይድ ሀብታሙ ወደ ውጪ አውጥቶታል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላም አዳማ ከተማዎች ሌላ ጥሩ ሊባል የሚችል የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር ። በአጋጣሚው ከዳዋ ሆቴሳ በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ አሜ መሀመድ ወደ ግብ ሞክሮት ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ወልቂጤ ከተማዎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ፊት በፈጣን ሽግግር ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በቀላሉ የአዳማ ከተማን የተከላካይ መስመር ሰብረው ለመግባት በመቸገራቸው ከሳጥን ውጪ በጌታነህ ከበደ ፣ ጫላ ተሺታ እና አብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት የሞከሯቸው ኳሶች ኢላማቸውን መጠበቅ ሳይቸሉ ወደ ውጪ ወጥተዋል ።
በ67ኛው ደቂቃ ላይም ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ያሻማው ኳስ በዳግም ንጉሴ በግንባር ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው አሜ በቀጥታ ኢላማውን የጠበቀ ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በሰይድ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው አብዲሳ ጀማል ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂው ተይዞበታል ።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች የቀጠሉ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በተቃራኒ አቅጣጫ አብዱልከሪም ወርቁ ከአዲስ ተስፋዬ የነጠቀውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ለአቡበከር ሳኒ አቀብሎት የነበረ ቢሆንም አቡበከር ኳሱን በደንብ መቆጣጠር ባለመቻለለ ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። በመጨረሻም ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 21 ማድረስ ቢችልም በደረጃው ላይ ለውጥ ማድረግ ሳይችል 9ኛ ላይ የሚቆይ ሲሆን አዳማ ከተማ ነጥቡን 22 በማድረስ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል ።
17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማ በመጪው ረቡዕ ቀን 9 ሰዓት ላይ ፋሲል ከተማን የሚገጥም ሲሆን አዳማ ከተማ ደግሞ በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ አርብ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጅማ አባጅፋርን የሚያስተናግድ ይሆናል ።