በ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቶ ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ወልቂጤ ከተማዎች በ21ኛው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ ሰይድ ሀብታሙ ፤ ዮናታን ፍስሀ ፤ ሀብታሙ ሸዋለም እና አቡበከር ሳኒን በሮበርት ኦዶንካራ ፤ ተስፋዬ ነጋሽ ፤ አበባው ቡጣቆ እና ዮናስ በርታ ምትክ ሲያሰልፉ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በሳምንቱ በፋሲል ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በቴዎድሮስ ሀሙ እና እንዳለ ከበደ ምትክ ዘሪሁን አንሼቦን እና ፍፁም ጥላሁንን ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ወልቂጤ ከተማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ተረጋግተው ከሜዳቸው ለመውጣት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ዘደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ ግን የተሳካ ጊዜን አላሳለፉም በአንፃሩ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ከወልቂጤ ከተማ በተሻለ የተቃራኒ ሳጥን ጋር የደረሱባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ ቢሆንም የማጥቃት የሶስተኛው ክፍል ላይ የነበራቸው እንቅስቃሴ ደከም ያለ ነበር ።
በ2ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አዲሱ ከቻርለስ ሪባኑ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ገብቶ ለአቤል ነጋሽ ለማቀበል ያደረገው ጥረት በዮናታን ፍስሀ አማካኝነት ከሸፈ እንጂ የመዲናዋ ክለብ ገና በጊዜ ቀዳሚ መሆን የሚችልበት አጋጣሚ ነበር ።
ቀጣዩ የግብ ሙከራ 22 ያሀል ደቂቃዎችን ቆይቶ የታየ ሲሆን ከእጅ ውርወራ የተነሳ ኳስን ሪችሞንድ አዶንጎ ለኤልያስ አቀብሎት ኤልያስ ወደ ግብ የመታው ኳስ በዋሁብ አዳምስ ተደርቦ ወጥቷል ።ከውሀ እረፍት መልስ ወልቂጤ ከተማዎች ቀደም ብሎ ከነበራቸው በአንፃራዊነት በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ክፍትቶችን ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል ሲደርሱ የነበራቸው ቅንጅት ግን የግብ ሙከራዎችን በቀላሉ ለማድረግ የሚያስችላቸው አልነበረም ።
- ማሰታውቂያ -
31ኛ ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አሻማ አዶንጎ በግንባር ገጬቶ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ይዞበታል ።
ወልቂጤ ከተማዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን 40ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉ ሲሆን አብዱልከሪም ወርቁ ከርቀትየመታው ኳስ በዳንኤል ተሾመ ተይዟል ።የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛው ክፍለጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ፍፁም ጥላሁን ለሙሉቀን አዲሱ አቀብሎ መልሶ ከሙሉቀን የደረሰውን ግሩም ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ቢጠበቅሞ ፍፁም ወደ ግብ የመታውን ኳስ ዳግም ንጉሴ ደርሶ አውጥቶታል ።
አዲስ አበባ ከተማዎች ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ አምስተኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ሙሉቀን አዲሱ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ዋሁብ አዳምስ ለማውጣት ሲሞክር ኳሱ ከመረብ ላይ አርፏል ።ከግቡ በኋላ በእንቅስቃሴ ረገድ ቀዝቀዝ ብሎ በቀጠለው ጨዋታ ሰራተኞቹ አሁንም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው ቢጫወቱም ዳንኤል ተሾመን የፈተኑ የግብ ሙከራዎች አልነበሩም ።
በአዲስ አበባ ከተማ በኩል የፊት መስመር አጥቂውን ሪችሞንድ አዶንጎን ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች ወደ ወልቂጤ ከተማ የሜዳ ክፍል ቢጣሉም ተጫዋቹ ጋር በትክክል መድረስ የቻሉ አልነበሩም ።
በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ግን ወልቂጤ ከተማዎች ከሽንፈት የዳኑበትን ግብ አግኝተዋል ።
89ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ጫላ ተሺታ በግንባር ገጭቶ አዲስ አበባ ከተማ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን አቻ አድርጓል ።ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ነጥቡን 29 በማድረስ በ8ኛ ደረጃ ሲቀጥል አዲስ አበባ ከተማም በ22 ነጥብ በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 4 ( ሀሙስ ) 10:00 ላይ ወልቂጤ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም በተከታዩ ቀን 7:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ሀዋሳ ከተማን ያስተናግዳል ።