ወልቂጤ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ልክ እንደ ዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ግብ ሳያስተናግድ ተጠናቋል ።
ከአምስተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ሁለቱም ክለቦች በርካታ ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ አበባው ቡጣቆ አላዛር ዘውዴ ፍፁም ግርማ እና ዮናታን ፍስሀን እንዲሁም በአርባምንጭ ከተማ በኩል ይስሀቅ ተገኝ ፤ ማርቲን ኦኮሮ ፤ ሙና በቀለ እና ሱራፌል ዳንኤል ወደ ቋሚ አሰላለፍ ገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው በሁለቱም በኩል ወደ ፊቴ ሄዶ አጥቅቶ የመጫወት ፍላጎት በሜዳ ላይ የታየበት ነበር ። በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይም አርባ ምንጭ ከተማዎች በተሻለ ወደ ፊት ሄደው ጫና መፍጠር የቻሉበት ጨዋታ አስመልክተውናል ።
- ማሰታውቂያ -
አርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያውን ሙከራ ለማድረግ የወሰደባቸው 2 ደቂቃ ብቻ ነበር ሀቢብ ከቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲልቭያን ግቦሆ ለጥቂት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በወልቂጤ ከተማዎች በኩል በ18ኛ ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የተሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ግብ ተይዟል ። ወልቂጤ ከተማዎች በሂደት በማጥቃቱ የበላይነትን ለመውሰድ ቢሞክሩም የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ግን ቀላል አልሆነላቸውም ። በአርባምንጭ ከተማ በኩል በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ግብ ክልል ይዘዋቸው የሚሄዷቸው ኳሶች እንደ ወልቂጤ ሁሉ በግብ ሙከራ የታጀቡ አልነበሩም ።
36ኛ ደቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ ከቀኝ መስመር አካባቢ ያገኘውን የቅጣት ምት ቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ለጥቂት አውጥቶታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለምንም ግብ ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ በጥሩ ፉክክር የተጀመረ ሲሆን 49ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን ከበላይ ገዛኸኝ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ገብቶ አክርሮ ቢመታውም የግቡ ቋሚ መልሶበታል ። በተወሰነ መልኩ ቀድሞ ከነበረው ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለው ጨዋታ 65ኛ ደቂቃ ላይ አወዛጋቢ ክስተትን አስተናግዷል ። እንዳልካቸው መስፍን በሳጥን ውስጥ ሆኖ በአበባው ቡጣቆ ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የአርባ ምንጭ ከተማ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም የዕለቱ የመሀል ዳኛ በዝምታ አልፈውታል ። በቀሩት የጨዋታው ደቂቃዎች እንደአጀማመሩ መቀጠል ያልቻለው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በሁለቱም በኩል በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ተፈፅሟል ።
ውጤቱን ተከትሎም በእኩል 8 ነጥብ ላይ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች ነጥባቸውን ዘጠኝ ማድረስ ችለዋል ።