ረፋድ ላይ ሲዳማ ቡና ወልቂጤ ከተማን በዳዊት ተፈራ የፍፁም ቅጣት ምት ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ የአመቱ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ሲችሉ ወልቂጤ ከተማዎች በደካማ እንቅስቃሴያቸው ብልጫ እንዲወሰድባቸው ተገደዋል። 10ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ሲዳማዎች አጥቂያቸውን አዲሱ አቱላን በጉዳት አጥተዋል። በሆንም የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ወደ ግብ ለመድረስ ግን አይናፋር ነበሩ ማለት ይቻላል።
- ማሰታውቂያ -
በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ተከላካዩ ጊት ጋትኮች በረጅሙ አሻምቶት ተመስገን በጅሮንድ ሳጥን ውስጥ ሆኖ የሞከራት በሲዳማ ቡና በኩል ጥሩ ከሚባሉ ሙከራ ነበረች።
የ17ኛው ደቂቃ የዳዊት ተፈራ የርቀት ሙከራዎች ብቻ ከሲዳማ በኩል የታዩ ደህና ሙከራዎች ነበሩ። ቶማስ ስምረቱ ሳጥን ውስጥ በእጅ በመንካቱ ምክንያት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ 36ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ወልቂጤ ከተማዎእ አብዱራህማን ሙባረክ በመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ካደረገው ሙከራ ውጪ እዚ ግባ የሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ በሲዳማ ቡና 1-0 እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የነበሩት ወልቂጤ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ተሻሽለው በመቅረብ በንቃት ተጫውተዋል። ሲዳማዎች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የበላይነት ለማስቀጠል በሙሉ አቅም ተጠቅመዋል። ፍሬው ሰለሞን በረጅሙ መቶ የሞከራት በወልቂጤ ከተማ ልትጠቀስ የምትችል አጋጣሚ ነበረች። ጥሩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ቅብብሎቻቸው የተሳኩ ስላልነበሩ ሶስተኛ የማጥቂያ ክልል ላይ ኳሶቻቸው ሲባክኑ ተስተውለዋል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና በሀብታሙ ገዛኸኝ አማካኝ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው እንደምንም አድኖበታል።
ጨዋታው ተጨማሪ ግቦች ሳይሰተናገዱበት በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ወልቂጤ ከተማዎች በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈትን ለማስተናገድ ተገደዋል ።