በአስረኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ የተገናኙት መቻል እና ኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ጨዋታቸውን አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ሲያጠናቅቁ ጎሎቹንም ናቲ ለኤሌክትሪክ ሲያስቆጥር የመቻልን ግብ ደግሞ አማካዩ ፍፁም አለሙ በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።
ወደ ድሬዳዋ ከተጓዙ በኋላ በጨዋታ ሶስት ነጥብ ማሳካት ተራራ የመዉጣት ያህል የከበዳቸው መቻሎች በአስረኛዉ ሳምንት በሲዳማ ቡና ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት ከተረቱበት ጨዋታ ለማገገም የዛሬዉ የአስር ሰዓት መርሐግብር ወሳኝነቱ የጎላ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በተለይ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለዉ የመቻል የአጥቂ ክፍል አሁንም ጥያቄ ቢነሳበትም ነገር ግን አጠቃላይ እንደ ቡድን በሚጠበቀዉ ልክ መዋሀድ አለመቻሉ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ እንቅፋት ሆኖበታል።
በተመሳሳይ ወደ ድሬዳዋ ካመራ በኋላ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለዉ እና ከቀናት በፊት የቀድሞ አሰልጣኙን ያሰናበተዉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት የአራት ለሁለት ሽንፈት ለማገገም በዛሬዉ ጨዋታ አንዳች ነገር ይሰራሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።
ዉጤቱን ተከትሎም ሁለቱ ክለቦች በአምስተኛው ተከታታይ ጨዋታቸዉ ከድል ጋር መታረቅ ሳይችሉ ሲቀጥሉ በቀጣይ በአስራ አንደኛዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር መቻል ከሀዋሳ ከተማ ጋር ሲገናኝ በተመሳሳይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የሚጫወት ይሆናል።