በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ7ተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ኤሌትሪክን 2ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በጨዋታ እንቅስቃሴ ረገድ የኢትዮ ኤሌትሪክን የበላይነት በተመለከትንበት የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ በመድን በኩል ያን ያህል ተጠቃሽ የግብ ሙከራን መመልከት አልቻልንም ነበር።
- ማሰታውቂያ -
በተለይ ጨዋታዉ በጀመረ ገና በ7ተኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ ናትናኤል ሰለሞን የመድን ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ያገኘዉን ኳስ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በድጋሚ በ11ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ከግራ መስመር በኩል የተቀበለዉን ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ወደ ግብ በሚሞክርበት ሰዓት የመድን ተከላካዮች ሲመልሱ በአቅራቢያው የነበረዉ ኢብራሂም ከድር በድጋሚ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ አቡበከር ኑሪ ተቆጣጥሯል።
በ27ኛዉ ደቂቃ ላይ ኢብራሂም ከድር ላይ የተሰራዉን ጥፋት ተከትሎ የተገኘዉን ቅጣት ምት የመስመር ተጫዋቹ ሙሴ ከበላ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆኖንም ግብ ጠባቂዉ አቡበከር ኑሪ እንደምንም ኳሷን ወደ ዉጭ አዉጥቷታል።
በእንቅስቃሴም ሆነ በሙከራ ረገድ በብዙ ብልጫ የተወሰደባቸዉ የነበሩት መድኖች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸዉ በፊት ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም በ38ኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል ዮናስ ገረመዉ ወደ ስጥኑ ያሻማዉን ኳስ ኪቲካ ጀማል ወደ በጭንቅላት በመግጨት የሞከራት ኳስ በአጋማሹ ተጠቃሽ የመድን ሙከራ ነበረች።
ከአጋማሹ መልስ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት መድኖች በ57ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ከግራ መስመር በኩል የተሻገረለትን ኳስ አጥኪዉ ሲሞን ፒተር ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም የተጫዋቹ ድክመት ታክሎበት ኳሷ ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በ68ኛዉ ደቂቃ ላይ ሙሴ ከበላ ከሳጥኑ ዉጭ ኳስ አክርሮ ወደ ግብ በመምታት ግብ ለማስቆጠር ቢሞክርም ኳሷ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥታለች። በሁለተኛው አጋማሽ በሙከራ ረገድም ጥሩ የነበሩት መድኖች ነገር ግን እጅግ ለግብ የቀረቡ የግብ ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም ለመጠቀም ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በ74ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን መድኖች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም አጥቂዉ ሲሞን ፒተር ቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ ዘሪሁን በሚመልስበት ሰዓት ኳሷን ያገኛት አሚር ሙድሲር በድጋሚ ወደ ግብ በመላክ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በድጋሚ ከአንድ ደቀቃ በኋላ ደግሞ አጥቂዉ ሲሞን ፒተር ከሳጥን ዉጭ ድንቅ ሙከራን ማድረግ ቢችልም በግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደል ድንቅ ብቃት ኳሷ ዘወደ ዉጭ ወጥታለች።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር የማጥቃት ሀይላቸውን እያጠናከሩ የቀጠሉት መድኖች በግብ አስቆጣሪዉ አሚር አማካኝነት ከርቀት ቀርቀት ድንቅ ሙከራን ማድረግ ችለዉ የነበረ ሲሆን በ82ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻሉበትን ግብ በመስመር ተጫዋቹ ሀቢብ ከማል አማካኝነት የችለዉ ጨዋታቸውንም ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችለዋል።