የአዳማ ከተማው ምንተስኖት ከበደ የቀድሞ ክለቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላሳዩት ክብርና ለሰጠው ምላሽ ለተቆጡት አዳማ ከተማዎች ይቅርታ ጠየቀ።
ተጨዋቹ አዳማ ከተማ በባህርዳር ከተማ 3-0 ከተሸነፈበት የአዲስ አበባ ዋንጫ ጨዋታ በኋላ በተለምዶ ዳፍ ትራክ አካባቢ ለተገኙ የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች በጭብጨባና በእጅ ሰላምታ ምላሽ ከሰጠ በኋላ ጥላፎቅ ከሚገኝ አንድ ደጋፊ የተሰጠውን አርማ በመሳም አክብሮቱን መግለጹ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎችን አበሳጭቷል።
በማህበራዊ ድረገጾች ደጋፊዎቹ አስጸያፊ ስድብ በመሳደብ ክለቡ ርምጃ እንዲወስድ የሚቀሰቅስ ተቃውሞ የቀረበበት ተጨዋቹ ያልጠበቀው በመሆኑ መገረሙን ገልጿል።
- ማሰታውቂያ -
“አዳማ ከተማዎች እንድጫወትላቸው ፈልገው አክብረው አስፈርመውኛል ይሄ ለኔ ትልቅ ክብር ነው እነዚህን በፍጹም ላስቀይም አልሻም ይሄን አይነት ባህሪም የለኝም” የሚለው ምንተስኖት” ደጋፊዎች ሰላም ሊሉህ ይፈልጋሉ በሚል በአንድ የጊዮርጊስ አስተባባሪ ሲነገረኝ ባሳዩኝ ያልጠበኩት አክብሮት ስሜታዊ ሆኛለሁ አርማውን የተቀበልኩትም ስለምወድህ ይህን ተቀበለኝ ያለውን ደጋፊ ጥያቄ ላለመግፋት ስል ነበር ሁሉም ድንገት መከወኑ ስሜታዊ አድርጎኛል” ሲል የነበረውን ሂደት ገልጿል።
ተጨዋቹ “ለአዳማ ከተማ ትልቅ ክብር አለኝ እኔ ማሊያ በመሳም ብቻ ፍቅር ይገለጻል ብዬ አላምንም ለተሰለፉባቸው ክለቦች በሙሉ ማሊያ እየሳሙ ፍቅራቸውን ገለጹ የሚለውን አላምንበትም በቀጣይ ሃሙስ አዳማና ጊዮርጊስ ሲጫወቱ ለአዳማ ድል የሚቻለኝን በማድረግ ለአዳማ ከተማ ያለኝን ክብር ለማሳየት ዝግጁ ነኝ በዚህ አጋጣሚ በዚህ ድርጊቴ ቅር ለተሰኙና ለተከፉ በሙሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሏል።