የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ሐዋሳ ከተማ በጅማ ከተማ በሚገኘው የጅማ ዩንቨርስቲ ሜዳ ላይ ዛሬ ባደረገው የ7ተኛው ሳምንት የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራውን ጠንካራውን ባህር ዳር ከተማን በመስፍን ታፈሰ እና በኤፍሬም አሻሞ ሁለት ግቦች 2-1 ሊያሸንፍ ችሏል። ለተጋጣሚው ደግሞ ምንም እንኳን ሽንፈትን ቢያስተነሠግዱም ሳህለወርቅ ተገኝ ነው አንዷን ግብ ሊያስቆጥር የቻለው።
ከሐዋሳ ከተማ እና ከባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምን ይመስል እንደነበርና ስላገኙት ድል እንደዚሁም ደግሞ ስለ ወቅታዊ አቋማቸው እና ለቡድኑ ጎሎችን በማስቆጠር ስላለበት ሁኔታ ተጨዋቹ ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድር ጓል፤ ተከታተሉት።
ስለ ዛሬው ጨዋታ እና ስለ ድላቸው
“ጨዋታው ደስ የሚል እና ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። በሁለታችንም በኩል የጎል ዕድልንም ስንፈጥር ነበር። ያም ሆኖ ግን እኛ ያገኘነውን ዕድል በመጠቀማችንና እነሱ ደግሞ ሊጠቀሙ ስላልቻሉ አሸንፈናቸዋል። በውጤቱም በጅማ ከተማ ላይ ያገኘነው የመጀመሪያችን ድል ስለሆነ በጣም ተደስተናል”።
ስለ ዛሬ ተጋጣሚያቸው
- ማሰታውቂያ -
“ባህር ዳር ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው። በጨዋታው ብዙ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ሊጠቀሙበት አልቻሉም”።
ወደ አሸናፊነት መንፈሱ ስለመምጣት ሚስጥራቸው
“አንድነታችንና ህብረታችን ነው ለእዛ ያበቃን። ወደ ሜዳ ስንገባም የግድ ግጥሚያዎችን ማሸነፍ አለብን ብለን በቁርጠኝነት ስለምንገባም ፈጣሪ ረድቶን ጥሩ ውጤት እያስመዘገብን ይገኛል”።
ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ከውጤት ማጣታቸው ጋር ተያይዞ ሐዋሳ ሊወርድ ይችላል ስለመባሉ
“ሐዋሳ ከተማ በአዲስ አበባ ባደረገው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የጅማሬ ጨዋታዎች ላይ ውጤቶችን ባጣበት ሰዓት እንዳልከው ስለ እኛ ብዙ ተብሎ እና ወራጅ ሊሆን ይችላልም በሚል ተነግሮ ነበር። ይሄን ስንሰማ ቡድናችንን ስለምናውቅ አንዳች ስጋት በእኛ ውስጥ አልነበረም። ሐዋሳ ሊጉ ሲጀመር ውጤትን ያጣው የአዲስ አበባ አየር ስለከበደው እና ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴም አንፃር የራሳችን የሆኑ ችግሮች ስለነበሩብን እንጂ ለተጋጣሚዎቻችን እጃችንን ሰጥተን አልነበረምና ከእዛ በኋላ ባደረግነው ጨዋታ አቋማችንን እያስተካከልን በመምጣታችንና የአሰልጣኛችንንም ታክቲክ እየተገበርን በመምጣታችን በዛሬው ጨዋታ ደግሞ የጅማ ከተማ አየር ከአዲስ አበባው አየር ጥሩ ለመጫወት የረዳን በመሆኑ እነዚህ ወደ ውጤታማነት እንድንመጣ አድርጎናል”።
ለሐዋሳ ከተማ ጎሎችን ስለ ማስቆጠሩ እና ስለ ቀጣይ ጨዋታዎቻቸው
“አጥቂ እንደመሆኔ ቡድኔ ጎሎችን ከእኔ ይጠብቃል። ያን ስለማውቅም አሁን ላይ በየተሰለፍኩባቸው ጨዋታዎች ላይ ግቦችን ማስቆጠር ጀምሬያለሁ። ይሄ ቀጣይነትም የሚኖረው ነው። ለሐዋሳ ብዙ ጎሎችን የማስቆጠር እልም አለኝ። ይሄን ቡድን ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግብም የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ። በቀጣይ ጨዋታዎቻችንም ቡድናችን አሁን በያዘው የአሸናፊነት መንፈስ በመጓዝ ውጤታማም እንደሚሆን አምናለው”።
ስለ ቡድናቸው ስብስብ
“ወጣት ተጨዋቾች በብዛት አሉን። ልምድ ያላቸውንም ጥቂት ልጆች አካተናል። ሁሉንም እንደየተራው በማስገባት ቡድናችን እየተጠቀመባቸው ይገኛል”።