አቶ ግርማ አወቀ እና ወ/ሮ ሰብለ ደምሴ ከተባሉ ኢትዮጵያዊን ወላጆቿ በአሜሪካ የተወለደችው ናኦሚ ግርማ በ2022 የአሜሪካ ሴቶች ሊግ (National Womens Super League)
በሁለት ዘርፎች የአመቱ ምርጥ ተብላ ተሸልማለች ።
በቀድሞዋ የማንችስተር ዩናይትድ ሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ካሴይ ስቶኒ በሚመራው የሳን ድያጎ ዌቭ በመሀል ተከላካይ ስፍራ የምትጫወተው ናኦሚ ያሸነፈችባቸው ዘርፎች አንደኛው የአመቱ ምርጥ ተከላካይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ Rookie of the Year (በመጀመሪያ የፕሮፌሽናል ተጫዋነት አመታቸው አስገራሚ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾች የሚሸለሙበት) ዘርፎች ነው ።
በአሜሪካ የሴቶች ሱፐር ሊግ ታሪክም በመጀመሪያ አመት ቆይታ በሁለት ዘርፎች በማሸነፍ የመጀመሪያ ተጫዋች ለመሆን ችላለች ።
ናኦሚ ከዚህ ቀደምም በ2020 የአሜሪካ የአመቱ ወጣት ሴት ተጫዋች አሸናፊ መሆን ችላም ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
የ22 አመቷ ተጫዋቾች ለአሜሪካ ከ17 ፤ ከ19 እና ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድኖች ተጫውታ አሳልፋለች ።
ናኦሚ የአሜሪካ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት ጭምር በመምራት የ2020 የኮንካፋ ዋንጫን ያነሳች ሲሆን በ2016ም ከ17 ዓመት በታች ቡድን ጋር የዕድሜ ዕርከን የኮንካፋ ውድድር አሸናፊ ሆናለች ።
ከ2020 ጀምሮ ደግሞ ለዋናው የአሜሪካ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን 8 ያህል ጨዋታዎች ላይ ተሰልፋ በመጫወት አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችታ ማቀበል ችላለች ። በተጨማሪም አሜሪካ የ2022 የኮንካፋ አሸናፊ ስትሆን የቡድኑ አባል ነበረች ።
ተጫዋቿ እያሳየች ባለችው ብቃት በሊጉ ተከታታዮች ዘንድ እና በአሜሪካ የስፖርቱ ሚዲያዎች ከፍተኛ ሙገሳዎችን በማግኘት ላይ ትገኛለች ። በቀጣይም በአለም የሴቶች እግርኳስ ላይ ከላይ የሚቀመጠው የአሜሪካ ሴቶች ብሄራዊ ቡድንን በድንቅ ብቃት ለረጅም አመታት እንደምታገለገል ተስፋቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ ።