የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ የእራት ግብዣ አካሄደ።
ከሰአታት በፊት በድሬዳዋው ራስ ሆቴል በተካሄደ የእራት ግብዣ ላይ የሊጉ ክለቦች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎችና አመራሮች እንዲሁም ለሁሉም ክለቦች የእንኳን ደህና መጣችሁ የሞቀ አቀባበል ያደረጉት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች፣ የዲ ኤስ ቲቪ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸው ታውቋል።
በምሽቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃግብር ላይ የፕሪሚየር ሊጉ ሼር ኩባንያ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ያደረጉት ረዘም ያለ ንግግር ትኩረት የሳበ ሆኗል።
በከተማው መስተንግዶ የተደመሙት መቶ አለቃ ጭብጨባ ያስከተለውን ንግግር ያደረጉት ለድሬዳዋዎች ነው በመልካም አቀባበልና ዝግጅት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎችን ያመሠገኑት ፕሬዝዳንቱ ” የቀጣይ አመት ፕሪሚየር ሊግን የምንጀምረው መስከረም ላይ ነው ቃል የምገባላችሁ የመጀመርያ አዘጋጅ ከተማ አድርገን ውድድሩን የምንጀምረው ድሬዳዋ ላይ ነው”ሲሉ የሞቀ ጭብጨባ ተከትሏቸዋል። ሊጉ ከዲሲፕሊን አንጻር የተሻለና ጥሩ የሚባል መሆኑን የመሰከሩት መቶ አለቃ ለዚህም ክለቦችና ደጋፊዎቻቸውን አመስግነዋል።
መቶ አለቃ በዚህ ንግግራቸው አዲስ መረጃ እንዳላቸው በመግለጽ የክለባቸው ኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበበከር ናስር ለደቡብ አፍሪካው ማማሎዲ ሰንዳውንስ መፈረሙንና ቀጣዮቹን አራት ወራት ኢትዮጵያ ቡናን አገልግሎ በመጪው የውድድር አመት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊግ የሚጓዝ መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
- ማሰታውቂያ -
በዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስተያየት መበሳጨታቸው የሚያስታውቅባቸው የሊጉ ፕሬዝዳንት መቶአለቃ ፈቃደ እንደተናገሩት “የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ስለተናገረው እኔም ልናገረው ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ አሰልጣኙ ሊጉ ደካማ መሆኑን ተናግሯል። በእኛ በኩል ግን ደካማው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ እንጂ ፕሪሚየር ሊጋችን አይደለም” በማለት ጠንከር ያለ ሂስ ሰንዝረዋል። ” አቡበከር ናስር 29 ግብ ያስቆጠረው የፊት አጥቂ ሆኖ ነው በብሄራዊ ቡድን ግን ቦታውን አላገኘም በአሁኑ ሰአት አቡበከር በዕድሜም ሆነ በችሎታ ከጌታነህ ከበደ ይበልጣል አሰልጣኝ ባንሆንም 50 አመት እግርኳስን ተመልክተናል” በማለት የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ጌታነህን ያስቀደመበት ሂደትን ተችተዋል።
የሊግ ኩባንያው ፕሬዝዳንት “ሊጋችን ጠንካራ እየሆነ ነው አሁን ባለን የሊግ ደረጃ የታንዛኒያና የኬንያን ሊግ እንበልጣለን” ሲሉ በሊጉ ጥንካሬ ላይ እምነቱ እንዳላቸው ተናግረዋል።