በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ናስር 3 ግቦች ቅ/ጊዮርጊስን 3-2 መርታቱ የሚታወቅ ሲሆን በዕለቱ ፍልሚያም ሽንፈትን ላስተናገደው ቅ/ጊዮርጊስ የቡናው አማካይ ሬድዋን ናስር ወደ ኋላ ለግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ አቀብላለው ብሎ በራሱ ላይና ጋዲሳ መብራቴ ደግሞ ሌላኛዋን ግብ ሊያስቆጥር ችሏል።
ኢትዮጵያ ቡና ቅ/ጊዮርጊስን በረታበት በእዚሁ ጨዋታ ተቀይሮ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ ሬድዋን አበረታች እንቅስቃሴን ካሳዩ የቡድኑ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን ይህን ተጨዋች አጠር ባሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የሀትሪክ ስፖርት ድረ ገፅ ከትናንት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አናግሮት ምላሹን በሚከተለው መልኩ ሰጥቷል።
ቅ/ጊዮርጊስን ስለ ማሸነፋቸው
“የድል ውጤቱ ከትልቅ ቡድን ጋር ከመጫወታችን አንፃር ለእኛ በጣም አስፈላጊያችን ነበር። ጥሩም ስለተጫወትን እነሱን አሸነፍን። ውጤቱም የተለየ የደስታ ስሜትን በሁላችን ውስጥም ፈጠረብን”።
- ማሰታውቂያ -
ይሄን ድል ከሸገር ደርቢው ጨዋታ በፊት ጠብቀውት እንደነበር
“አዎን።ገና ከካምፕ ስንነሳ ጀምሮ ነው ይሄን ጨዋታ ስለማሸነፍ እንጂ ፈፅሞ አቻ ስለመለያየትን ሳናስብ ወደ ሜዳ በመግባት ግጥሚያውን ያደረግነውና ያሸነፍነው። በስተመጨረሻም ቃላችንን ጠብቀን ወደ ካምፓችን በደስታ ተመልሰናል”።
ቅ/ጊዮርጊስን ማሸነፍ ስለቻሉበት ጠንካራ ጎን
“ያሸነፍናቸው እንደ ቡድን ኳስን ተቆጣጥረን ስለተጫወትንና የተዘጋውን በርም ለማስከፈት የተለያዩ ጥረቶችን ስላደረግን ነው። በያዝነው አጨዋወትም የግብ እድሎችን ስለፈጠርንና በጨዋታውም ላይ የበላይ ስለነበርን አሸናፊ ሆነናል፤ ድሉም ይገባናል”።
ስለ ተጋጣሚያቸው ቅ/ጊዮርጊስ
“እንደ እኔ ምልከታ ከሌላው ጊዜ አንፃር እነሱ ጥሩ አልተጫወቱም። ከእዚህ በፊት ግን የሚያስጨንቅ ቡድን ስለነበራቸው ተፅህኖ ይፈጥሩብናል ብለን ጠብቀን ነበር። ያን በእዚህ ጨዋታ ላይ ማድረግ አልቻሉም”።
ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው አሸናፊ የሆነባቸውን 3 ግቦች ስላስቆጠረው ወንድሙ አቡበከር ናስር
“አቡበከር በአሁን ሰዓት በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኝ ተጨዋች እና ለእኔ ደግሞ በጣም የምወደው ወንድሜ ነው። በኳሱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስም እመኝለታለሁ። ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር በነበረን ጨዋታም እኔ በራሴ ላይ ግብ አስቆጥሬ የመራነውን ፍልሚያ አቻ እንድንሆንበት ባደረግኩበት እና በጣምም በተበሳጨሁበት ሰዓት መልሶ መሪ ያደረገችንን ግብ ሲያስቆጥርና በአጠቃላይ ደግሞ ቅ/ጊዮርጊስን እንድናሸንፍ ሀትሪክ ሲሰራም የተመለከትኩበት ሁኔታ ስለነበር በጣም ነበር የተደሰትኩት”።
ከቅ/ጊዮርጊስ በነበራችሁ ጨዋታ ከግብ ጠባቂያችሁ ጋር ሳትግባቡ ቀርታችሁ በራስህ ላይ ግብን አስቆጠርክ። አንዳንዶች ለጨዋታ እዛ ድረስ ከሚለፋ ለራሱ በሚቀርበው ጎል ላይም አገባ ብለውካል…..ቡድናችሁ ላይ ለተቆጠረው ለእዚህ ግብ ስህተቱ የማን ነው?
“እዛ ድረስ ሄዶ ከሚያገባ በሚቀርበው ግብ ላይ አገባ የምትለውን ቀልድ አሁን ስሰማ አባባሏ በጣም ተመችታኛለች። በቡድኔ ቡና ላይ ላስቆጠርኩት ግብ ጥፋቱ ከግብ ጠባቂያችን ጋር ስላልተግባባን እንጂ የእኔ ብቻ አይደለም። የሁለታችንም ስህተት አለበት፤ ዋናው ነገር ይሄ ኳስ ላይ ያጋጥማልና ከእዚህ ትምህርትን ነው ልንወስድበት የሚገባን”።
የኢትዮጵያ ቡናን መለያ ለብሶ ስለመጫወቱ
“በጣም ዕድለኛ ነኝ። በተለይ ደግሞ በታላቁ የደርቢ ጨዋታ ላይ ከዚህ በፊት ብዙ የአገራችን ታዋቂ ተጨዋቾች ተጫውተው ባለፉበት ማሊያ እና በብዙ ደጋፊዎች በሚደገፈው ክለብ ውስጥ ሆኜ ስለተጫወትኩ ፈጣሪዬን ዓላ አመሰግነዋለሁ”።
ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ
“ስለ እሱ ከሰዎች ከሰማዋቸውም ሆነ ራሴም ከተመለከትኳቸው ነገሮች በመነሳት ጥሩ አሰልጣኝ እንደሆነና የተሻለ ነገርንም ለኢትዮጵያ ቡና ሊሰራ እንደሚችል ተገንዝቤያለሁ። እንደ ተጨዋች ስቀርበው ደግሞ እያንዳንዱ ተጨዋች በውስጡ ያለውን አቅም አውጥቶ እንዲጫወት እና በኳሱ ተፅዕኖ ውስጥም እንዲወድቁ በሚሰጠው ጥሩ ስልጠናም የሚያግዝ ስለሆነ እሱን እንድታደንቀውም ያደርግሃል”።
የዘንድሮ እቅዳቸው እና ግባቸው
“ዓላማችን የአሸናፊነት ግባችንን በማስቀጠል የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ነው። ለእዛም እያንዳንዱን ጨዋታዎቻችንን ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የጨዋታ ታክቲክ ታማኝ ሆነን እንቀጥላለን”።
በመጨረሻ….
“በኢትዮጵያ ቡና የተጨዋችነት ዘመን ቆይታዬ ብዙ ታሪካዊ ውጤቶችን ማግኘት እፈልጋለሁ። ለዛ ሁሌም ጠንክሬም እሰራለሁ እና ለሁሉም ነገር ዓላ እንዲረዳኝም አጥብቄ እለምነዋለሁ”።
“