የፈረሰኞቹ ቦርድ ከዲሲፕሊን ጋር ተያይዞ በወሰደው ጠንካራ ርምጃ የጸና ይመስላል።
ከባድ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉትና ውላቸው ያለቀው 3ቱ ተጨዋቾች ዳግመኛ የክለቡን ማሊያ አታደርጉም ብሎ በያዘው የጸና አቋም አስቻለሁ ታመነ ወደ ፋሲል ከነማ፣ ጋዲሳ መብራቴ ወደ ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ሙላለም መስፍን/ዴኮ/ ወደ ሲዳማ ቡና ማቅናታቸው ይታወቃል።
ከሶስቱ ውጪ ሰኔ 30/2014 ድረስ ውል ያለው ጌታነህ ከበደ/ሰበሮም/ ውል ቢኖረውም የክለቡን ማሊያ ዳግመኛ እንዳያደርግ ወስኗል። በዚህም በስምምነት ወደፈለገበት እንዲሄድ መወሰኑ ታውቋል። ከዚህም ውጪ ውል ያለው አቤል እንዳለም በስምምነት ክለቡን እንዲለቅ መወሰኑ ታውቋል።
ለመረጃው ወደ አቤል የግል ስልክ በተደጋጋሚ ብደውልም ዝግ በመሆኑ ላገኘው አልቻልኩም። ስለጉዳዩ የተጠየቀው ጌታነህ ከበደ ስለ ክለቡ ውሳኔ ምንም መረጃ እንደሌለው ገልጿል።
- ማሰታውቂያ -
ክለቡ ግን በሰጠው ምላሽ “የቦርዱ ውሳኔን ለተጨዋቾቹ አሳውቀናል ምላሻቸውን እየጠበቅን ነው በስምምነት የሚጠበቅባቸውን ፈጽመው ወደ ፈለጉበት መሄድ ይችላሉ” ሲል አስታውቋል። የሁለቱ ተጨዋቾች ምላሽ ምን ይሆን የሚለው አጓጊ ሆኗል።