በፕሪምየር ሊጉ አጀማመሩ ጥሩ ያልነበረው እና በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ የመጀመሪያ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታውን ቀን 10 ሰዓት ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረገዉ ሲዳማ ቡና 2ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ጥሩ የሚዳ ላይ እንቅስቃሴ ባስመለከተን የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ገና በጨዋታው መባቻ 8ኛዉ ደቂቃ ላይ የአዳማ ተከላካዮች በቅብብል ወቅት የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ያገኛትን ኳስ አማካዩ ፍሬዉ ሰለሞን መሐል ለመሐል ለአጥቂዉ ይገዙ ቦጋለ አቀብሎት ተጫዋቹ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
የአቻነት ግብ ለማግኘት በቶሎ ወደ ጨዋታዉ ለመግባት ሲጥሩ የነበሩት አዳማዎች በ ደቂቃ ላይ በአማካዩ መስዑድ መሐመድ አማካኝነት ድንቅ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ከቀኝ መሰመር በኩል በጥሩ የጨዋታ ቅብብል የተገኘዉን ኳስ መስዑድ ከሳጥን ዉጭ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ተከላካዮ ጊት ጋት ኮት እንደምን ወደ ዉጭ አዉጥቷታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ በድጋሚ ከግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሐንስ የተሻገረለትን ኳስ የመስመር ተጫዋቹ አሜ መሐመድ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት በግቡ አናት ላይ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒው ቡድን ለተወሰነ ደቂቃም ቢሆን ጫና ተፈጥሮባቸው የነበሩት ሲዳማዎች በ29 ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። በዚህም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ ፍሬዉ ሰለሞን ተጫዋቾችን በግል ብቃቱ ቀንሶ ያቀበለዉን ኳስ ይገዙ ወደ ግብነት በመቀየር ለራሱም ለክለቡም ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት መምራት የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በጥቂቱም ቢሆን ወደ ራሳቸዉ ግብ አፈግፍገዉ ሲጫወቱ በተቃራኒው አዳማ ከተማ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ሲጥሩ ተስተውሏል።
ከዕረፍት መልስ ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱት አዳማዎች በ52ኛዉ ደቂቃ ላይ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ከግራ መስመር በኩል ዊሊያም ሰለሞን ያሻገረለትን ኳስ አሜ መሐመድ በጭንቅላቱ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ እንደምንም ኳሷን አዉጥቷታል።
በ67ኛዉ ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች ምናልባትም መሪነታቸውን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል አግኝተዉ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህም የአዳማ ተከታዮች የቅብብል ስህተትን ተከትሎ የተገኘዉን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ቢቆጣጠርም በቶሎ ወደ ግብ ሞክሮ በረኛዉ ኳሷን ተቆጣጥሮታል።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር ሲዳማ ቡናወች ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገው ሲጫወቱ አዳማ ከተማዎች በተቃራኒው ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የተመለከትን ቢሆንም ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ጨዋታዉ በሲዳማ ቡና 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።