የቀድሞ አሰልጣኙን ካሰናበተ በኋላ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ እየተመራ ወደ ዉጤታማነት መመለስ ችሎ የነበረዉ እና ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ በሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ሽንፈት አስተናግዶ የነበረዉ ሲዳማ ቡና በዘጠነኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ቀን 10:00 ሰዓት ላይ በተደረገዉ ጨዋታ በአማካዩቹ ፍሬዉ ሰለሞን እና ሙሉአለም መስፍን (ዴኮ) ግቦች ታግዞ መቻልን ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ወደ ድል መመለስ ችሏል።
በተጠበቀዉ ልክ ዉጤታማ መሆን ያልቻለዉ እና ካለፉት አራት የሊጉ ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ ያልቻለዉ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን መቻል በስምንተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ብር ከአምናዉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ማጠናቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን ፤ በዛሬዉ ዕለትም በቀደመ ብቃቱ ላይ በማይገኘዉ ሲዳማ ቡና ሽንፈትን አስተናግዷል።
የዛሬዉን የዘጠነኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ዉጤት ተከትሎም ሲዳማ ቡና በ10 ነጥብ በጊዜያዊነት 9ነኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ፤ በተቃራኒው በዛሬው ዕለት ሽንፈት ያስተናገደዉ መቻል በስምንት ነጥብ እና በአምስት የግብ ዕዳ 12ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በቀጣይ በአስረኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብርም በዛሬዉ ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገደዉ መቻል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሲገናኙ ፤ የአሰልጣኝ ስዩም ከበደዉ ሲዳማ ቡናም ከፋሲል ከነማ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።