በይስሀቅ በላይ
ሀትሪክ፡- ጥያቄን የምጀምረው ለመሆኑ
ኃይሌ ተደምረሃል…? በሚለው ነው…?
ኃይሌ፡- …ምን…አልከኝ…
ተደምረሃል…? …ተደምረሃል ነው
ያልከኝ…?
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- …ምነው ኃይሌ ፊትህን
ጨምደድ…፤…ጥያቄዬን ረገጥ
አደረከው…?… እንደውም ተወው…
ተደምረሃል… የሚለውን ጥያቄዬን…
ለጊዜው ላቆየው…ከዚያ… በፊት…ሌላ ግርም
የሚለኝን… ጥያቄ ልጠይቅህ…ፌስቡክ…
ቢዘጋ ደስ ይልሃል…?
ኃይሌ፡- …(በጣም በፈገግታ
ታጅቦ)…ውይ…ውይ…ተው…በእናትህ…
አታስደስተኝ…! (አሁንም ሣቅ)…፤ምን
መሰለህ…በሌላው አለም ፌስቡክ መማማሪያ
ትልቅ የቢዝነስ መሳሪያ ነው፤ በእኛ ሀገር ግን
የምንጠቀመው በተቃራኒው ነው፡፡ ፌስቡክ
ለምን ጥቅም እንደሚውል በደንብ እስክንማር
ጥቅሙን እስከምናውቀው ያዝ ቢደረግ ደስ
ይለኛል እንጂ አይከፋኝም፡፡ ይሄንን የምልህ
ግን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የተጣለሁ
ሰው ሆኜ ወይም ጠቀሜታው ጠፍቶኝ
አሊያም እኔ ላይ በፌስ ቡክ ብዙ ስለተባለም
አይደለም፤እኔን በተመለከተ ስለተባለው ነገር
ብዙም ግድ የለኝም፡፡ በፌስቡክ እየተሠራጨ
ያለው ነገር በጣም ነው
የሚያሰጋኝ፤ በየዩኒቨርሲቲው፣
በየክልሉ፣ በየስታዲየሙ በዘር በጎሳ
ተከፋፍለን እንድንጋጭ በፌስቡክ
የሚሰራጨው የሀሰትና የጥላቻ ወሬ
በጣም ያሰጋኛል፤ ወንድሞቻችንን
እየጨረሰ ነው፡፡ ማይናማር የምትባለው
ሀገር ላይ አሁን የደረሰውን እልቂት
አይተሃል? መነሻው ይህው የፈረደበት
ፌስቡክ ነው፤ በናይጄሪያ 2 ብሔረሰቦች
የተላላቁት በዚሁ በፌስቡክ የውሸት ዜና
ነው፡፡ ለእኔ በፌስቡክ እነ ማርክ ዙከርበርግ
መስራቾቹና ለመልካም ነገር የሚያውሉት
ብቻ ናቸው የተጠቀሙበት፡፡ እኛን በተመለከተ
ግን ፌስቡክ በመከፈቱ መጀመሪያ ገንዘባችንን
በሉት፣ ቀጥሎ ጊዜያችንን አሁን ደግሞ እኛን
ራሳችንን እያባሉን ህይወታችንን እየበሉት
ነው፤ በየቦታው በዚህ በመከረኛ ፌስቡክ
የወንድሞቻችን ህይወት እየጠፉ ሠላማቸው
እየደፈረሰ ነው፤ይሄ እየሆነ አጠቃቀሙ
እስኪገባን ለመልካም ነገር ማዋል እስክንጀምር
አይዘጋ ብልህ ነበር የሚገርምህ፡፡
ሀትሪክ፡-በሀገራችን በበርካታ ታላላቅና
ዝነኛ ሰዎች ሥም የፌስቡክ አካውንት
እየተከፈተ ህዝቡን የማደናበር ነገር ሲሰራ
ይታያል፤ ኃይሌ አንተም በስምህ አካውንት
ተከፍቶ የዚህ ነገር ሰለባ ከሆኑ፣
ከተሰቃዩት አንዱ ነህ ልበል…?
ኃይሌ፡- …
( ሣ ቅ ) …
ወ ይ …
አ ን ተ …
አ ን ድ
አካውንት
ብ ቻ
መ ሠ ለ ህ
እንዴ…በስሜ
የተከፈተው…?
…አራት አምስት
አካውንት ነው በስሜ
የተከፈተው፤ በዚህ
በፌስቡክ ሠላማቸውን
ካጡት በጣም ከተሰቃዩት
ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ በስሜ
የተከፈተውን የፌስቡክ
አካውንት ለማዘጋት፣ህዝቡ
እንዳይታለል፣በሀሰት ዜና
እንዳይደናገር ለመከላከል
ያልረገጥኩት ቦታ
የለም፡፡ በግሌ ካደረኩት
ጥረት በተጨማሪ
ከመረጃና የደህንነት
መረብ ኤጀንሲ (ኢንሣ)
ጋር ሳይቀር ለማዘጋት
ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፤
በዚህም ሳላበቃ አለም
አቀፉ ድረስ ሄጄ በተለይ
በሆላንድ በማናጀሬ በኩል
ደብዳቤ ተፅፎ ለማዘጋት
ፌስቡክ ዋና መ/ቤት
ድረስ ብዙ ርቀት ሄጄለሁ፡
፡ በወቅቱ እነሱ ምንድነው
የመለሱልኝ መልስ
“ለመዝጋት ከመሞከራችን
በፊት አንተ መሆንህን
ለማረጋገጥ ሌላ አዲስ
የፌስቡክ አካወንት ክፈት”
አሉኝ፤ ባሉት መሠረት
አዲስ ከፈትኩ፤ ከዚያ ምን
ቢሆን ጥሩ ነው….?
ሀ ት ሪ ክ ፡ – … ም ን …
ሆ ነ … ተ ገ ላ ገ ል ክ … ? . . .
እፎይ….አልክ?
ኃይሌ፡- …መች…
እንዲህ በዋዛ…
( ሣ ቅ ) … ፤ …
እንደ አዲስ
የ ከ ፈ ት ኩ ት ን
አ ዲ ሱ ን
አካውንቴን ወዲያውኑ ጠለፉት…(በጣም
ሳቅ)…፤…ፌስቡክ የለኝም…! የእኔም
አይደለም ብዬ ብጮህ ማን ይሰማኝ…?…
ብቻ…ለጊዜውም ቢሆን ተጫወቱብኝ…፣
በጣም አሰቃዩኝ፤አሁን ግን ሁሉም
ተዘጋግቷል፤ እኔም ፌስ ቡክ የሚባል
የለኝም፡፡
ሀትሪክ፡- …በተለይ በአንተ ስም
ከተከፈቱት አንደኛው የአንተን ምስጢር
የሚያውቅ፣ የሌላ ነው ለማለት የሚቸግር፣
ብዙዎችን ያሳመነ ነበር፤ ይሄ እንዴት ሊሆን
የቻለ ይመስልሃል…?…በዚህ የተነሣስ
አጠገብህ ያሉትን… እስከመጠርጠርና
እስከመጣላትስ አልደረስክም…?
ኃይሌ፡- …(ሳቅ)…ወይ ጉድ አንተ ማን
ቀረኝ ብለህ ነው…? …እንኳን ሠውን ጥላዬን
ሁሉ ሳይቀር ነው የተጠራጠርኩት፤ችግሩ
ብዙ ነገር አመሰቃቅሎብኝ ስለነበር …
አጠገቤ ያሉትን ሰዎች ሁሉ መጠራጠር
ጀምሬ ነበር ብቻ ሣይሆን እነሱ ሳያውቁ
እስከማሰለል ሁሉ ደርሼ ነበር፡፡ ምክንያቱም
ይሄን የሚያደርገው ሰው በጣም የተረገመ
ሰው ነው፤ የሆነ መንፈስም ይመስለኛል፤
አንዳንዴ ደግሞ ከሚሰራው ስራ በመነሣት
ይሄ ሰው ውስጤ ነው እንዴ ያለው?…
ነው ወይስ የሆነ መከታተያ ዲሽ ነገር እላዬ
ላይ ተክሏል? እስከማለት ሁሉ ደርሻለሁ…
(ሳቅ)… ምክንያቱም ፌስቡክ ላይ የሚለጠፈው
በየዕቱ የማደርጋቸው ነገሮች ናቸው፡፡
አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሠለህ በዓል ነው የሀገር
ልብስ ለብሼ የበዓል ዳቦ እቆርሳለሁ ፎቶው
በየት በኩል እንደወጣ አላውቅም ወዲያውኑ
ፌስቡክ ላይ “ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ
እንኳን አደረሳችሁ” ተብሎ በስሜ ተለጥፏል፡
፡ ይሄንን ሣይ ማመን አልቻልኩም በጣም
ደነገጥኩ ይሄ ነገር እቤቴ ነው እንዴ
ያለው? እስከማለት ሁሉ አደርሶኛል፡፡
ፎቶ፣ቪዲዮ እንዴት እያመጣ እንደሚለጥፍ
አላውቅም፤ቃላቶቹንም በእኔ ልክ አዘጋጅቶ
ነው የሚለጥፏቸው፡፡
ሀትሪክ፡-ግን የአንተ የሆነ ጥብቅ
ምስጢሮችን፣ፎቶዎችን ከየት የሚያገኝ
ይመስልሃል…?
ኃይሌ፡- ይሄ ሰው ከእኔ ጋር በጣም
ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር የእለት
ተዕለት ግንኙነት ያለው ይመስለኛል፤
እነሱ በየዋህነት “ዛሬ ከኃይሌ ጋር ውለን
በዓል አክብረን”ምናምን ሲሉት እሱ ይቺን
እንደቀልድ ይይዝና ፎቶም በተለያየ መንገድ
እየወሰደ የሚለጥፍ ይመስለኛል፡፡ በአጭሩ
ሌላ ስራ ሆኖብኝ ነው የከረምኩት፤ ብዙ ቦታ
አስሮጦኛል፣ አሰቃይቶኛል፡፡
ሀትሪክ፡-በስምህ አካውንት ከፈቶ ሌላ
ሩጫ ያበዛብህን ይህን ሰው ብታገኘው ምን
ታደርገዋለህ…?
ኃይሌ፡- …መቼም… እገለዋለሁ…
ወይም እከሰዋለሁ… የምልህ መስሎህ
ነው…?… (ሣቅ)…በጣም አደንቀዋለሁ…
ከዚያ እመክረዋለሁ እንጂ ምንም
አልለውም፤ምክንያቱም… ይሄ ሰውዬ
ጭንቅላቱን ለተንኮል አዋለው
እንጂ በጣም የሚደነቅ ጭንቅላት
ነው ያለው፡፡ በእርግጥ የእኔን
አስመስሎ አወጣ ህዝቡን አደናበረ
እንጂ አልሰደበኝም፡፡ በዚህ ደረጃ
አዕምሮው ማሰቡ ይገርማል፤ በዚህ ጭንቅላቱ
ማርክ ዙከርበርክ የፌስ ቡክ መስራች ጋር
መቀጠር ያለበት ሰው ነው፡፡ ግን ያለ ባለቤቱ
ፈቃድ የሰውን ሠላም በመንጠቁ ህዝቡን
በማሳሳቱ መሳሳቱን ከመናገርም ከመምከር
ውጪ አደንቀዋለሁ እንጂ አልወቀሰውም፡፡
ሀትሪክ፡- …ኃይሌ ቅድም በይደር ወደ
አቆዩሁት ጥያቄ አሁን ልመለስ…፤…
ለመሆኑ ኃይሌ… ተደምረሃል…?
ኃይሌ፡- …ተደምረሃል… ወይ ነው
ያልከኝ…?…እኔ መደመር ብቻ አይደለም
ተባዝቻለሁ፤ መደመር ማለት ግን ምን
ማለት ነው? መደመር በአፍ ብቻ መሆን
የለበትም፡፡ ቀን ቀን ተደምረህ ማታ ማታ ሌላ
ከሂሳብ ስሌት ውጪ የሆነ ነገር የምትሰራ
ከሆነ የመደመር ትርጉሙን ያጣል፡፡ ለሀገር፣
ለህዝብ የሚጠቅመውን ማድረግ ነው እንጂ
እንደው ዝም ብሎ ተደምሬያለሁ ማለት
ብቻውን ለእኔ ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው፤
አገር ህዝብ ለሚፈልገው ነገር፣ ለሠላሙና
ለአንድነቱ መሰራት ነው ለእኔ የመደመር
ትርጉሙ፡፡
ሀትሪክ፡- …ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር
አብይ አህመድ በሀገሪቱ እያመጡት ያለውን
ለውጥ ኃይሌ እንዴት ነው የሚገልፀው…?
ኃይሌ፡- …የዶክተር አብይ ስራን
በተመለከተ በጣም ጥሩ ስራ እየሠሩ ነው፤
እሳቸው ስለ ፍቅር፣ ስለ ሠላም፣ ስለ
አንድነትና ስለይቅር መባባል ይሰብካሉ፤
በአንዳንድ ቦታዎች ከእሣቸው ሃሣብ፣ ካለው
መነሳሳት ጋር የሚቃረን ነገር ታያለህ፤
አንዳንድ ጊዜ መሪዎች ከአንድ ሚሊዮን
ዛፍ ውስጥ አንዱን ብቻ ነው የሚተክሉት፤
የቀረውን የሚተክለው ህዝብ ነው፡፡ እሣቸው
አንዱን ተክለው አሣይተዋል፤ የቀረው
የእኛ ኃላፊነት በመሆኑ ልናግዛቸው እኛም
በመትከሉ ላይ ልንረባረብ ይገባል፡፡ ጠቅላይ
ሚኒስትሩ መፈቃቀርን፤ አንድነትን ይቅር
ባይነትን ዘረኝነትን ስለመጠየፍ በየንግግራቸው
እየተናገሩ እኛ ሀገርን በመንደር በሠፈር ደረጃ
እያጠበብን፣ ዘር እየቆጠርን እንከርማለን፤
ይሄን ሣይ እኛ ወደ ኋላ ቀርተን እሳቸው
ብቻቸውን ወደፊት ሄደዋል እላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ኃይልዬ አሁን ከአንተ
ጋር በልግፅ ማውራትና አንተን መጠየቅ
የምፈልገው ጥያቄ ላይ ደርሻለሁ…?
ኃይሌ፡- …ኃይል እንደመገረም እያለ…
ግንባሩን ጨምደድ እያደረገ…እንዴ
እስከአሁንስ እየጠየከኝ አይደለም እንዴ…?…
ጠይቀኝ የምትፈልገውን…?
ሀትሪክ፡- …የሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎች
ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው
በተያዙበት ሰሞን ከእነሱ ጋር ይሰራሉ የተባሉ
ድርጅቶች ስም ዝርዝር ሲዘረዘር ከተዘረዘሩት
ውስጥ አንዱ በአንተ ባለቤትነት የሚመራው
ማራቶን ሞተርስ የተባለው ድርጅት ነው፤
እንደ ድፍረት ካልቆጠርክብኝ ኃይሌ የአንተም
ድርጅት እዚህ ውስጥ አለበት…የሚለውን
አረጋግጥልኝ እስቲ…?
ኃይሌ፡-(…በግርምት እያየኝ… በጣም ከት
ብሎ ሳቅ)…ይህቺ… ጥያቄ…ምርመራ ቢጤ
መሆንዋ ነው …?…(ሣቅ)… አንተ ይሄን
ትላላህ… ከዚህ ይልቅ ሌላ የተባለውን… የባሰ
ነገር ልንገርህ…
ሀትሪክ፡-…ምን ተባለ…?
ኃይሌ፡-…(አሁንም ሳቁ አላባራም)…
አንዱ በዚሁ በፈረደበት ፌስቡክ ምን
አለ መሰለህ…? “ሰባተኛው እስር ቤት
ተገኘ፤ የኃይሌ ህንፃ ስር እስር ቤት አለ”
ብሎት አረፈው…(በጣም ባቅ)…አንተ ስለ
ማራቶን ሞተርስ ታወራለህ ከእሱ የባሰም
ይሄ ተብሏል፡፡
ይሄ ከሜቴክ ጋር አብረው የሚሠሩ ድርጅቶች ምናምን የሚባለውን
ነገር እኔም ሰምቻለሁ፤ ከፌስቡክ ላይ
አምጥተውም አሳይተውኛል፡፡ ስራ ከሆነ
ትክክለኛውን መስመር ይዘህ ከሜቴክም
ይሁን ከማንም ጋር ልትሠራ ትችላለህ፤
ከእነ ሜቴክና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር
የኃይሌ ድርጅት ዝርዝሩ ውስጥ ተካቷል
በሚል የተወራውን ወሬ እንደሰማሁ ወደ
ቢሮ መጥቼ ምን የተሠራ ነገር አለ እኔ
የማላውቀው? ብዬ ፋይሎችን ማገላበጥ
ነው የተያያዝኩት፡፡ ሠራተኞቼንም እናንተ
ከሜቴክ ጋር የሠራነው ሥራ አለ እንዴ? ብዬ
ሁሉ እስከመጠየቅ ደርሼ “እንዴ ኃይሌ ምን
ማለትህ ነው የፌስ ቡክ ወሬ አይተህ ነው
እንዴ? ብሎን እንኳን አልተሻሻጥንም” ብለው
መልሰውልኛል፡፡ የሚገርምህ ከየት መጥቶ
ለምን እንደተወራ ለምን ከዚህ ጋር ማያያዝ
እንደተፈለገ ለእኔ ግልፅ አይደለም፤ እንደዚህ
አይነት የሀሰት ወሬ ጦርነት ሲከፈት እኔን
አይጎዳኝም፤ ምክንያቱም ለምጄዋለሁ፡፡ ለ30
አመት እናንተን ጨምሮ ከሀገር ውስጥና
ከውጪ ሚዲያዎች ጋር እገናኛለሁ፤ ብዙ
ተፅፏል፣ ብዙ ተወርቷል፣ ብዙ ተብያለሁ፤
እኔ ለምጄዋለሁ፤ ይሄንን መቋቋም የማይችሉ
ሰዎችን ግን ክፉኛ ነው ምንጎዳቸው።
ለምሣሌ የማራቶን ሞተርስ እንደተባለው
ቢሆን እንኳን ችግር የሚመጣው እኔ ጋር
አይደለም፤በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች አሉ፡
፡ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ኦፌሰር አለ፤ ያልተገባ
ጥቅም አግኝተሃል? ወይም ሥራ ሠርተሃል?
ተብለው የሚጠየቁ በኃላፊነት የተቀመጡ
ሰዎች ከመሆናቸው አንፃር ወሬው ሲወራ
እነዚህ ሰዎች ሊረበሹ ይችላሉ፡፡፤ ሰዎች
ናቸውና ከራሣቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውም
ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ እንዳልኩህ ነው እኔ እንደዚህ
አይነቱን ነገር ለምጄዋለሁ፤ ኖሬበታለሁም፡፡
እንደውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላ የሚያስቅ
ነገር ምን ተባለ መሰለህ…(ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ምን ተባለ…ደሞ…?
ኃይሌ፡- …(አሁንም ያላባራ ረዥም
ሳቅ)… ከዚሁ ከማራቶን ሞተርስ ጋር
በተያያዘ… የኃይሌ ድርጅትና ስም ዝርዝር
ወጥቷል አልተባለም እንዴ…? ታዲያ
ስም ዝርዝሩ ከወጣ እስከ አሁን እንዴት
አልያዙትም? ሲል አንደኛው ምን ብሎ
ቢመልስ ጥሩ ነው… “ምን ይይዙታል…
፤እሱ ታውቀው የለ ሯጭ ነው…ሊይዙት
ሲሉ እየተሽሎከለከ እያመለጣቸው ነው…”
ብሎት እርፍ ብሏል…(በጣም የማያባራ
ሳቅ) …በአጭሩ እኔ ለሀሰተኛ ወሬ የምሸበር
አይደለሁም… ፤ ህዝብ ግን ይጎዳል…
አሁን ሰሞኑንን የተለቀቀውን የአምነስቲ
ኢንተርናሽናልን ዜና ሰምተሃል? የውሸትና
የጥላቻ ዜናን በመልቀቅ ሰዎችን በማጋጨት
ሀገራችን አንደኛ መሆኗን ይገልፃል፡፡ በሌላ
አንደኛ ለመሆን መሽቀዳደም ሲገባን አሁን
በዚህ መጥፎ መንገድ መሪ መሆናችን ነው
የሚያሳዝነው፡
ሀትሪክ፡- ኃይሌ እስቲ አሁን ደግሞ
ወደ አትሌቲክሱ ሰፈር እንመለስ፤ መፈክር
ተይዞብህ ሠላማዊ ሰልፍ የተወጣብህ
የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሆነሃል፤ በዚህ
ደንግጠህ ነው ስልጣን የለቀከው?
ኃይሌ፡- …ወይ መደንገጥ…!ያው
እንግዲህ አንተ እየለፍህ እየደከምክ ባለበት
ሰዓት ብዙኃኑን የማይወክሉ በአትሌቲክስ
ውስጥም ያንን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ ያልሆኑ
ሰዎች በድንገት “በአንተ ደስተኛ አይደለንም”
ሲሉ መልስህ ምንድነው መሆን ያለበት?
የራሳችሁ ጉዳይ ብለህ መቀመጥ ነው? ለእኔ
መልሱ አይደለም ነው፡ ምክንያቱም እኔ ወደ
አትሌቲክሱ የመጣሁት ለሥልጣን ወይም
ለጥቅም ባለመሆኑ ምንም እንኳን ጥቂት
ቢሆኑ፣ ምንም እንኳን አትሌቲክሱ ውስጥ
ምንም ያልሆኑ ቢሆኑ እንኳን ሃሳባቸውን
ማክበርና መቀበል ነው ያለብኝ፤ያደረኩትም
ይሄንኑ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አትሌቶች መፈክር ይዘው
ሰልፍ እስከወጡ ድረስ የሚያደርስ ምን
የአመራር ክፍተት ተፈፅሞ ነው? አንተስ
ለሠላማዊ ሰልፍ ምላሽ መስጠት እንጂ
እስከመልቀቅ የሚያደርስ ውሳኔ መወሰን
ነበረብህ…?
ኃይሌ፡- …አንድ የማረጋግጥልህ ያ
ሰልፍ የአትሌቶቹ ሃሣብ አይደለም፤ ሠልፉም
ሁሉንም አትሌት የሚወክልም አይደለም፡
፡ ደግሞም አሁን የወሰንኩትን ውሳኔ
ባልወስንና ወንበሬን አለቅም ብዬ ሙጭጭ
ብል እናንተስ እንደ ሚዲያ ህዝቡስ ምን
ይላል? አትሌቶቹ መፈክር ይዘው ተበደልን
ብለው ወጡ እኔ ደግሞ ልክ አይደላችሁም
ብዬ ብታገል ሰው በማነው የሚፈርደው?
በእኔ ነው፤ ስለዚህ እኔ በፕሬዝዳንትነት
የምመራው ቤት ትክክል ካልሆነ ልጆቹ በእኔ
ካልተደሰቱ አመሰግናለሁ ብዬ ቦታውን
ከመልቀቅ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ
የለኝም፡፡
ሀትሪክ፡-በአትሌቲክሱ በዚህ ደረጃ
የጠነከረ ተቋውሞ ማቅረብ ያልተለመደ
ነውና እንደ አንድ አለም አቀፍ ታዋቂ
አትሌት፣ እንደ አንድ አትሌቲክሱን
በቅንነት ላግዝ ብሎ እንደመጣ ሰው
እንደዚህ አይነት ያልተለመደ ነገር
ሲከሰትብህ ምን ተሰማህ…?
ኃይሌ፡- ሰው እኮ ነኝ…፤…በጣም
ነው የተሰማኝ ብቻ አይደለም ትልቅ
የሞራል ውድቀት ሁሉ የደረሰብኝ
ያህል በጣም ነው ውስጤ የተጎዳው፤
በጣም ባዶነትም ነው የተሰማኝ፡፡
አትሌቶች ሰልፍ አደረጉ የሚለውን
ዜና ሳይ ማመን አልቻልኩም፤ በጣም
ነው የደነገጥኩት፡፡ ምክንያቱም ቀጥታ
መነጋገር ሲቻል ይሄን ያህል ሰልፍ
የሚያስወጣ ምን ስራ ሠርቼ ነው?
ቁጭ ብሎ መነጋገር ሲቻል እኔ
የፖሊስ ኃይል ወይም የመንግሥት
ባለሥልጣን አይደለሁም መፈክር
ተይዞ ሰልፍ የሚወጣብኝ፤ ብቻ
በተደረገው ነገር ከልብ በጣም አዝኜ
ምን እንዳልኩ ታውቃለህ? ለራሴ
ሳይሆን “አይ ይህቺ ሀገር” የምትል ቃል
ብቻ ነው የተነፈስኩት፡፡ ምክንያቱም እኔ እኮ
ወደ አትሌቲክሱ የመጣሁት ሌላ ጥቅም
ፈልጌ አይደለም፤ ህዝቡ እንደ አይኑ ብሌን
የሚያየውን፣ ለሌላው አለም የገፅታችን
ማሳያ የሆነውን፣ በአለም አደባባይ
አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ
የሚያደርገንን አትሌቲክስ ለማገዝ
ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገር ፈልጌ
አይደለም የመጣሁት፡፡ እንደውም ወደ
አትሌቲክስ በመምጣቴ ሙሉ በሙሉ
ሊባል በሚችል ደረጃ የግል ስራዬን እኮ
ትቼዋለሁ፤ ይሄን በማድረጌ ደግሞ
አልተቆጨሁም፤ ምክንያቱም ፈቅጄ
ስለገባሁ፡፡ የግል ስራዬን በድዬ ጠዋት
ማታ ሳልል ራሴን ለአትሌቲክሱ
መስዋዕት ማድረጌ እንደ ጥፋት
ተቆጥሮ ሰልፍ ማስወጣቱ ውስጤን
ክፉኛ ጎድቶታል፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ ወደ ስልጣን ከመጣህ
በኋላ በአትሌቲክሱ መንደር ሠላም አልነበረም
መሳሪያ እስከመማዘዝ የተደረሰበት አጋጣሚ
ሁሉ እንደነበር ይሠማል በዚህ ላይ ምን
ትላለህ?
ኃይሌ፡- እንዳልከው አሁን ሠላማዊ
ሠልፍ ስለተወጣ ነገሮች ለየላቸው እንጂ
እነዚህ ወገኖች እኮ ላለፉት ሁለት አመታት
ሲያሰቃዩን ነበር፤ ነገር ግን በወቅቱ ትልቁን
ምስል በማየት ለሀገር መስራትን ነው
ያስቀደምነው፡፡ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ
መሞትም ካለብኝ እሞታለሁ፤መድረስ
የሚገባው ቦታ ሣላደርስ ክንዴን አልንተራስም
የሚል ቁጭትን በውስጤ ይዤ ስለመጣሁ
ወደ ኋላ ማለትን አልፈለኩም፡፡ በዚህ ደረጃ
እሞትለታለሁ ብዬ ምዬ ተገዝቼ የቆምኩለት
አትሌቲክስና አትሌት መፈክር ይዞ ሲወጣብህ
ምንድነው የምታደርገው? ዞር ማለት ብቻ
በቃ ይኸው ነው፡፡ ሠላማዊ ሠልፍ የተወጣው
ለሀገር ታስቦ ከሆነ የእኔ ዞር ማለት ለለውጥ
ከረዳ በቃ ምን አደርጋለሁ።
ሀትሪክ፡-በአመራርነት ዘመንህ የአሁኑ
ፈጦ ወጣ እንጂ መሳሪያ እስከመማዘዝ
“እገልሃለሁ” የሚል ዛቻን እስከመሰነዛዘር
የተደረሰበት አጋጣሚም ነበር፤ ለዚህ
ጥያቄዬ መልስ ሳትሰጠኝ…? ሌላው ኃይሌ
ፈተናዎችን ይቋቋም ይጋፈጥ ነበር አሁን
ትከሻው ሳሳ እንዴ የሚሉ አሉና ለዚህ ምን
መልስ አለህ…?
ኃይሌ፡- ይሄ እኮ የትከሻ መሳሳት
ፈተናን የመቋቋም አቅም ማጣት አይደለም፤
ፈተናን በተመለከተ እኮ እንዳልኩህ ሁለት
አመት የቆየነው እኮ በፈተና ውስጥ ሆነን
ነው፡፡ የአሁኑ እኮ እኔ አስፈልግሃለሁ
አገለግልሃለሁ ያልኩት አካል “አል
ፈልግህም” ሲልህ ልትታገለው
ነው? ወይስ ወደህ ሳይሆን በግድህ
ትፈልገኛለህ ብዬ መደረቅ ነው የነበ
ረብኝ? ይሄንን በተመለከተ ሰው
ያልተረዳኝ ነገር አለ፤ ልክ አንተ
በጥያቄህ እንዳነሣኸው “ኃይሌ በጣም
ጠንካራ ነበር፤ እንዴት አሁን ይሄን
የሚቋቋምበት ጥንካሬ አጣ፤ ትከሻው
ሳሳ እንዴ?” ምናምን ይላሉ፤
እውነታው ግን ይሄ አይደለም፡
፡ ምክንያቱም ሰልፉ የወጣብኝ እኮ
አትሌቱ ነው፤ የአትሌቶቹን ማንነት፣
ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ለጊዜው
ተወው፤ እነማንም ይሁኑ ሰልፉ
ከተወጣ በኃላ ቦታው ላይ
ምን ታደርጋለህ? በቃ አ
ታስፈልግም ተብለሃል እኮ፡፡
ሀትሪክ፡- ይህቺን የዛቻዋ
ንና መሳሪያ እስከመማዘዝ
የተደረሰበትን ጥያቄዬን እየዘለልካት
አስቸገርከኝ…?
ኃይሌ፡- …አንተ ምን አይነት ችኮ
ነህ…?…(ሳቅ)…ይሄንን ብናወራው ትርጉም
የለውም፤ በሁለት አመት የፌዴሬሽን
አመራርነት ከጠቀስኩልህ የበለጠ ብዙ
ነገር አስተናግደናል፤ አንተም በጥያቄህ
እዳነሣኸው ማስፈራሪያና ዛቻ ድረስ ተደርሶ
ነበር፡፡ እኔ እንደውም ግለፅ ባለ አማርኛ
ልንገርህ “እገልሃለሁ” እስከመበባልም ተደርሶ
ነበር፡፡ እኔ ግን ይሄ የፕሮፓጋንዳ ጉዳይ
ስለሆነ “እገልሃለሁ” ሲል ገድለኸኝ ሰበብ
እንዳልሆንብህ እያልኩ እያሾፍኩ አንዳንዶቹን
ደግሞ አይ እንግዲህ በቃህ እገልሃለሁ
እያልክ የምታስፈራራበትን እኔም መታጠቅ
አያቅተኝም እየተባባልኩ ነው ያሳለፍኩት፡፡
እንዳልኩህ ይሄ ድርጊቱ የሚደገፍ ባይሆንም
ከስሜት ከብስጭት ያለውን እውነት አምኖ
ካለመቀበል ነው ብለህ ሀገርህን አይተህ
ልታልፈው ትችላለህ፡፡ መፈክር ይዘው ሰልፍ
ወጡ ከተባለ በኋላ ግን መድረቅ ሳይሆን ዞር
ማለት ነው የሚመረጠው፡፡
ሀትሪክ፡- አንተን ልናከብርህ በአለም
ባለህ ተቀባይነት ብዙ ልንጠቀምብህ ሲገባ
በዚህ መልኩ ከስልጣንህ መነሳትህን ብዙዎች
ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል በማለት
ድርጊቱን የሚኮንኑ አሉ…?
ኃይሌ፡- እኔ አንድ የማይገባኝ ነገር አለ
ስራዬን በድዬ ሀገሬ ላገልግል ማለት ኃጢአቱ
ምኑ ላይ ነው? እንደተባለው እኔ ለኢትዮጵያ
አትሌቲክስ ምናልባት የምጠቅም እንጂ የምጎዳ
ሰው ነኝ ብዬ አላስብም፤ በውስጥም በውጪም
በጣም እጠቅማለሁ፡፡ ስለ ራስ ማውራት
እንዳይሆን እንጂ ብዙ ነገር ወደ ኋላ ሄድ ስንል
እኛ እኮ ፕሮግራም እስከማስቀየር የምንደርስ፣
ውጪ ያሉ ትላልቅ ሰዎችን ከፕሬዚዳንት
ጭምር አሳምነን ሃሣብ የምናስለውጥ፣ አንተ
አንተ ተባብለን ተፅዕኖ የምንፈጥር ሰዎች ነን፡
፡ እኔ ወደዚህ ቦታ የመጣሁት በችሎታዬ
ሣይሆን የእግዚአብሔር ሹመት ሆኖ ነው፤
እዚህ ቦታ በመቀመጤ ደግሞ እኔ ሣልሆን
ኢትዮጵያ መጠቀም ነበረባት፤የአትሌቶች
ተቆርቋሪ ነን ባዮች የአትሌቶችም ተወካዮች
ጠዋት ማታ ይሄ አልተሟላም፣ ይሄ ጎደለ
እያሉ በየቦታው ከመለፍለፍ በእኔ መጠቀም
ነበረባቸው፤ ምናልባት ሰው ነኝ ስሰራ
አጥፍቼ ሳላስደስታቸው ቀርቼም ይሆናል፤
ግን እዚህ ደረጃ የሚያደርስ ነገር ግን
እንዳልሰራሁ አውቃለሁ፡፡ እኔ ፍፁም ነኝ
ሁሉንም አስደስታለሁም ብዬ አልከራከርም፡
፡ ግን ከሁላችንም በላይ 100 ሚሊዮን ህዝብ
የማይደራደርበት ነገር አለ፤ እሱን ብናስቀድም
ነው የሚመረጠው፡፡
ሀትሪክ፡-አለም አቀፉ የአትሌቲክስ
ፌዴሬሽን(IAAF) የአንተን ከስልጣን መልቀቅ
አስመልክቶ ጉዳዩን ከመንግሥት ጣልቃ
ገብነት ጋር አያይዞት ሀገራችን የቅጣት
ሰለባ የምትሆንበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር
የሚል ነገር ሰምቻለሁ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ
የአትሌቲክሱ አለም ወይም የውጭ ሚዲያዎች
በመልቀቅህ ዙሪያ ያሉትን ነገር ታዝበሃል…?
ኃይሌ፡-ሚዲያው ምን አለ የሚለውን እኔ
ሣልነግርህ ራስህ በስሜ ጎግል አድርገህ ምን
እንዳተባለ ተመልከት፤ ግን ከዳር እስከዳር ብዙ
እንደተዘገበ አውቃለሁ፡፡ እኔ ከዚህ ከተራገበው
ዜና በላይ ያስጨነቀኝ በጣምም ያስደነገጠኝ
አሁን አንተ በጥያቄህም ያነሣኸው ነገር ነው፡
፡ IAAF የእኔ ከኃላፊነት መነሣትን ተከትሎ
የፌዴሬሽኑን ጽ/ቤት በተደጋጋሚ ጠይቀው
የተሰጣቸው ምላሽ ሊያጠግባቸው ባለመቻሉ
በዚህ ጉዳይ ላይ ትክክለኛውን ምላሽ መስማት
የምንፈልገው ከኃይሌ ብቻ ነው በማለት
ጉዳዩን ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጋር
አያይዞ የማሰብ ነገር ነበር፡፡ ሁኔታው በጣም
አሳሳቢና ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየሄደ
በመሆኑ ይሄንን መድፈን ስለነበረብኝ የ IAAF
ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮኸ ጋ ደወልኩለት፡፡
እሱም በተፈጠረው ነገር በጣም እንደደነገጠና
ለአትሌቲክሱም አደጋ እንደሆነ ከገለፀልኝ
በኋላ ስልጣን የለቀኩበትን ትክክለኛውን
ምክንያት እንድነግረው ጠየቀኝ..
ሀትሪክ፡-…ምን አልከው…?… አትሌቶች
ሰልፍ ወጥተውብኝ ለቀኩ… አልከው…?
ኃይሌ፡- …ምን ሆነሃል…?…ጤነኛ
አይደለህም እንዴ…?…(ሳቅ)…እንደዚህ
ብል እኮ ኢትዮጵያ ትታዘበኛለች፤ በአሁኑ
ሰዓት ስንት ሰው እውነቱን እንደሚቀበል
ባላውቅም የሆዴን በሆዴ ይዤ እናንተ
አሁን አዲስ ባወጣችሁት ሕግ መሠረት
ማለትም ፕሬዚዳንቱ ወንድ ከሆነ ፀሐፊዋ
ሴት ፕሬዚዳንቷ ሴት ከሆነች ፀሐፊው
ወንድ መሆን አለበት የሚለውን ተግባራዊ
ለማድረግ የተወሰነ ውሳኔ ነው፡፡ ምክንያቱም
የእኛ ፀሐፊ ወንድ በመሆኑ እኔ ፕሬዚዳንት
መሆን ስለሌለብኝ ሴት ፕሬዚዳንት ወደ
ስልጣን መምጣት ስላለበት ደራርቱን ወደ
ፕሬዝዳንትነት ለማምጣት የተወሰነ ውሳኔ
ነው እንጂ ሌላ ችግር የለም፡፡ ደግሞም
እኮ እኔ ከፕሬዚዳንትነት ወረድኩ እንጂ
በአልባነት እያገለገልኩ ነው፤ ምንም አይነት
የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የለውም አልኩት፡
፡ የ IAAF ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮኸ በደንብ
አልተዋጠለትም መሠለኝ “ለማንኛውም ኃይሌ
የአለም የአትሌቲክስ ኮኮቦች ምርጫ (ጋላ)
ሞናኮ ላይ ሲካሄድ እዛ እንገናኝና በዚህ
ጉዳይ በደንብ እናወራለን” ሲለኝ መምጣት
አልችልም ሌላ ጊዜ ብዬው ተለያየን እንጂ
ነገሮች መስመር ስተው ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-ስለ ደራርቱ ስታነሣ ደራርቱ
ኃላፊነቱን ላለመቀበል በጣም አንገራግራ
እንደነበር ሰምቻለሁ…? ከሁለት ወር በኋላ
በሚደረገው ምርጫ በፕሬዚዳንትነት ሌላ ሰው
ሊመረጥ ይችላል ብለህ ታስባለህ…?
ኃይሌ፡- ደራርቱ አልቀበልም ብላ ነበር
አውነት ነው፤ ደራርቱን አገር ይበላሻል
እረፊ እንጂ ብዬ ጮኬ በግድ አሳመንኳት
ተቀበለች፡፡ በወቅቱ ምርጫ ከሁለት አመት
በኋላ ይደረጋል ተብሏል እዚህ ጋር
እንድታሰምርበት የምፈልገውና አስረግጬ
የምነግርህ ነገር ከ2 ወር በኋላ ይካሄዳል
በሚባለው ጉባኤ ከደራርቱ ውጪ ሌላ
ሰው በፍፁም ማሰብ እንደሌለባቸው ነው፤
ከእሷ ውጪ ከታሰበ በጣም አደጋ አለው፤
ለሀገርም ጥሩ አይመጣም፤ ሁሉም ሰው
ሚዲያውም ይሄንን ማወቅ አለበት፡፡ ከዚህ
ውጪ የሚንቀሳቀስ ካለ ኃላፊነቱ የራሱ ነው
የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡- ኃይሌ ወደ አትሌቲክሱ ፕሬዚዳ
ንትነት የመጣህበትን ቀን ምነው እግሬ
በተሰበረ ብለህ ቀኑን ትረግመዋለህ?
ኃ ይ ሌ ፡ – … ( ሣ ቅ ) … ው ይ … ው ይ …
ምነው…?…ምን አረገኝ…?…እኔ አትሌቲክስን
በማገልገሌ አልቆጭም፡፡ ከዚህ ውጪ ህይወት
ስለሌለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-አንተ ወደ ስልጣን በመምጣትህ
ሰራሁት ወይም አመጣሁት የምትለው ሊነገር
የሚችል ለውጥ አለ…?
ኃይሌ፡-ወደ ፌዴሬሽኑ ስልጣን ስመጣ
ብዙ አሳካቸዋለሁ እለውጣቸዋለሁ ብዬ
ያቀድኳቸው የጀመርኳቸው ነገሮች ነበሩ፡
፡ እነሱን እስካላሳካሁ ከእቅድ እስካላለፈ
ድረስ ለውጥ አመጣሁ ብዬ አልናገርም፡፡
ከቆይታችን አንፃር ጅምሮች ነበሩ፤ በሁለት
አመት ውስጥ 30 በመቶ እንኳን ሰርተናል
ብዬ አላስብም፤ እንደ ምኞቴ ካየኸው ምንም
አልተሰራም ማለቱ ነው የሚገልፀው ፡
፡ አብዛኛዎቹ ፍሬያቸው በሂደት የሚታዩ
ነበሩ፤ በአትሌቲክስ ለውጥ መጣ፣ ተሠራ
የምትለው በውጤት ነው፡፡ ግን ይሄን ስልህ
ምንም ሳልሰራ ገብቼ ነው የወጣሁት ማለቴ
አይደለም፡፡ በውጤት ካልከኝ ከተስፋ በዘለለ
የተገኙ ትላልቅ ውጤቶችም ነበሩ፤ የአለም
የወጣቶች ሻምፒዮና፣ የአለም ክሮስ ካንትሪ፣
የዓለም ግማሽ ማራቶን ከአራት ወርቅ
ሶስት ያገኘንበት ከሁሉም በላይ የአገራችን
ስም ላይ ጥላሸት አጥልቶ የነበረው ዶፒንግ
ላይ ብዙ ሊነገር የሚችል ሥራ ሠርተናል፡
፡ እንዴት እኛን በዶፒንግ አምስት ዝርዝር
ውስጥ ትከቱናላችሁ ብለን ከ IAAFና ከዋዳ
ጋር ሳይቀር ጦርነት ውስጥ ገብተን ነበር፡
፡ በአትሌቲክስ ላይ ሪፎርም አካሂደናል፡፡
ማንዋል አዘጋጅተናል፣ አዲስ አበባ ለስልጠና
እንደማይሆን ካጠናን በኋላ ሁሉም ከአዲስ
አበባ ወጥቶ እንዲሰራ ዲሴንትራላይዝ
አድርገናል፡፡ አዲስ አበባ የአየር ብክለት፣የኑሮ
ውድነት፣ ፋታ የማይሰጥ እንቅስቃሴ ያለባት
ከተማ በመሆንዋ ለአትሌቶች ምቹ አይደለችም
ውጡ ብለን ለማስወጣት ሞክረናል፡፡ ከዚህ
ሌላ የዛሬ 2 አመት ስንነሣ ታርጌት ነበረን፤
ሻምፒዮናዎችን መቆጣጠር አለብን ብለናል፡፡
የአለም ሻምፒዮናም በለው ኦሎምፒክ አሊያም
ማራቶንን መቆጣጠር አቅደን እየሠራን ነበር፡፡
ከዚህ ውጪ የፌዴሬሽኑን አቅም ለመገንባት
ገቢ መፍጠር ነበረብን፡፡ ሄይኒከኖች ምስጋና
ይግባቸውና በሶፊ ማልት ምርታቸው ገቢ
ፈጥረውልናል፤ ከዚህ ውጪ የናሽናል
ሆቴልን የገቢ ምንጭ በማሳደግ ተጨማሪ
የገቢ ምንጭ ለማድረግ አቅደን በወር 300 ሺህ
የሚያሰገኝልን ሆቴል በሶስት እጥፍ ገቢውን
አሳድጎ እስከ 1 ሚሊዮን ብር እንዲያመጣ
አድርገናል፡፡ ምክንያቱም ገቢያችን በዚህ ደረጃ
ካለሳደግን አስቸጋሪ ነው፤ አንድ የአፍሪካ
ቻምፒዮንስ ሺፕ ስትሄድ እስከ 6 ሚሊዮን ብር
ነው የሚጠይቅህ። ቀጣይ እቅዳችን አዲዳስን
ወደዚህ መሳብ ነበር፤አዲዳስን ለማምጣት
ውጤት ግድ ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህንና
ሌሎች ሥራዎችን ለመስራት ምክረናል፤
በብዙ ችግርና ትግል ውስጥ ሆነን፡፡
ሀትሪክ፡-አልሰራሁትም ብለህ የምትቆ
ጭበት፤ የምትፀፀትበትስ ነገር አለ…?
ኃይሌ፡- ወደ ስልጣን መጥቾ እንደ
ፍላጎቴ የህዝቡን ስሜት የሚያረካ ማየት
የሚፈልገውን ለውጥ ባለማምጣቴ
መቆጨቴና መፀፀቴ የማይቀር ነው፤ ግን
እንደው በእኔ የስልጣን ዘመን ሆኖ አይቼው
አሳክቼው ብወጣ ደስ የሚለኝ ለሁሉም ነገር
መሠረት ይሆናል ብለን ያሰብነውን ወደ 7
ደንቦች ያሉት መመሪያ አውጥተን ነበር፤
እሱን ተግባራዊ ሳላደረግ መውጣቴ ቁጭት
ፈጥሮብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- አንተ ወደ ስልጣን ስትመጣ
“ኃይሌ ምን ነካው…?…መሮጥና መምራት
ይለያያሉ” ብለው ጥሩ አትሌት ጥሩ መሪ
ላይሆን ይችላል በማለት ስጋታቸውን
አስቀምጠው ነበር አሁን ያ ስጋታቸው ደረሰ
ብሎ መናገር ይቻላል…?
ኃይሌ፡-… (ሣቅ)…አንተ ምን ሆነህ
ነው…?…እኔ እኮ ብዙ ድርጅቶችን ነው
የምመራው… እኔ የምመራቸውን ድርጅቶች
ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ካነፃፀርከው
ፌዳሬሽኑን መምራት በጣም ቀላል ነው፤
የጨዋታ ያህልም ነው፡፡ ልክ አንተ እንዳልከው
ወደ ስልጣን ስመጣ “መምራት እንደ መሮጥ
ቀላል መስለው እንዴ?” ብለው አስተያየት
የሰጡ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፤ ስመራው
የነበረው ፌዴሬሽን እኮ 40 ሰው ነው በትልቁ
ያለው፤ በእኔ ድርጅት ስር ያሉና የምመራቸው
እኮ ከ2500 የበለጡ ናቸው፤ ይሄንን ሁሉ
ድርጅትና ሰው የመራሁ እንዴት 40 ሰው
መምራት ያቅተኛል? ፌዴሬሽኑን ከመምራት
ይልቅ እኔ የከበደኝ የአሌቲክሱ ፖለቲካ ነው፤
ፖለቲካ ስልህ የአትሌቱ፣የአሰልጣኙ፣
የማህበሩ፣ የሰው፣ የተለያዩ ሰዎች የግል
ፍላጎቶች የሚያርፉበት መሆኑ ነው፤ ይሄ
ነው የከበደኝ ነገር፡፡ ከዚህ ውጪ እንኳን እኔ
በውስጡ ያለፍኩ በወሬ ሳይሆን በተግባር
የማውቀው ሰውን ተወውና የእኛን አትሌትክስ
ፌዴሬሽን አትሌቲክሱን የማያውቅ ሰው ሁሉ
እኮ መርቶታል፡፡
ሀትሪክ፡- በሁለት ዓመት የፌዴሬሽኑ
ፕሬዚዳንትነትህ ምን አተረፍክ…?
ኃይሌ፡-…(ሣቅ)… ምን አተረፍክ ነው
ያልከኝ…?…(የምፀት ሳቅ እየሳቀ)…ቤተሰቤም
እኔም የማናውቀውን ደም ብዛት በሁለት
አመት የፌዴሬሽኑ ቆይታዬ አትርፌያለሁ፡፡
በፊት ደም ብዛትን በወሬ ብቻ ነበር የማውቀው
አሁን በተግባር ተዋውቀናል፤ከዚህ ውጭ
ተንኮል እንዴት እንደሚሰራም ያለ አስተማሪ
ተምሬበታለሁ፤ በስፖርት አልችልም ከእኔ
እከሌ ይሻላል የሚባል ነገር አለመኖሩን
በቅርበት አይቻለሁ፤ አሰልጣኞችም አትሌቱም
ከእኔ ወዲያ ላሳር ባዮች ሆነው አይቼ
ታዝቤያለሁ፡፡ ይሄን ማለታችን ምን ጎዳን
መሠለህ ራሳችንን እንዳንፈትሽ እንዳናውቅ
በር ዘግቶብናል፤ ወደ ውስጥ ማየት ነው
የሚጠቅመው፡፡
ሀትሪክ፡-ኃይሌ ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
ፕሬዚዳንትነት የመጣው ወደ አለም አቀፉ
አትሌቲክስ ማህበር (IAAF) መሸጋገሪያ
ለማድረግ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ውክልናን
ለማግኘት ነው በሚል ስትተችም ነበር፤
ትችቱ ተገቢ ነበር…?…ትቀበለዋለህ…?
ኃይሌ፡- …እንደመገረም እያለ…ምን…
ያልተባለ ነገር አለ… ይሄንንም እኔም
ሠምቸለሁ…፤ …እንደዚህ አይነቱ ነገር
ሰዎች ካለማወቅ የሚሣሣቱት ስህተት ነው፡
፡ እኔ እንደውም አንድ ነገር ልንገርህ ወደ
ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከምመጣ
ወደ IAAF ብሄድ ነበር መንገዱ ይበልጥ
ቀላል ይሆንልኝ የነበረው፤ አሁን የተሰላቸ
ወይም እኔ የማልወደው ነገር እኔ በጣም
ተፈልጌ ነበር፤ እዛ መግባት እችል ነበር
ተጠይቄያለሁ፤ምናምን እያልኩ አሰልቺ ነገር
ማንሣትን አልፈልግም እንጂ ሀቁን እንየው
ካልክ ከኢትዮጵያ ይልቅ ወደ ዓለም አቀፉ
አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚወስደው
መንገድ በጣም ቀላል ነበር፤ ደግሞም
ይሄንን ነገር በተመለከተ ከእኔ ይልቅ
የሚያውቁ ሰዎች ቢናገሩ ይሻላል እንጂ ወደ
IAAF የሚወስደው መንገድ ለእኔ የውሃ
መንገድ ነው፡፡ ግን ከውጪ ይልቅ እኔን
የሚያስደስተኝ ለሀገር መስራት ነው፤ ከዚህውጪ ብዙ ድርጅቶችን ስለምመራ ፋታ
የማይሰጥ ስራም ስላለኝ IAAF ም ይሁን ሌላ
ቦታ ማገልገል ይቸግረኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ስፖርቱ በተለይ እግር ኳሱ
የዘርና የጎሣ ሠለባ እየሆነ ብዙ ግጭቶች
እየደረሱ ውድድሮችም በተደጋጋሚ እየታጠፉ
ነው፤ አንተ ስትመራው በነበረው አትሌቲክስስ
የዘር ጉዳይ ገብቷል…?
ኃይሌ፡- አትሌቲክስ ውስጥ እስካአሁን
እንደዚህ አይነት የጎላ የዘር ችግር የለም፤ ግን
ስፖርቱን በዘርና በመንደር ደረጃ የሚያጠብ
ትንንሽ አዕምሮ ያላቸው ድካማ ሰዎች
ውስጣችን አይጠፉም፡፡ በዘር የመመካት
ፍላጎትን፣ ዘርን ማዕከል አድርጎ በኃል
የማፈን ምኞት ያላቸው ሰዎች አልነበሩም
ማለት አልችልም ነበሩ፤ ይሄንን እንደልባቸው
የሚያሳኩበት እድል እንደምኞታቸው
አላገኙም እንጂ፡፡ ይሄንን ከዘር ጋር የተያያዘ
ችግር ለማስወገድ መጀመሪያ ፌዴሬሽኑ
ሊያስተካክለው የሚገባ ነገር አለ፤ እኔም ወደ
ስልጣን በመጣሁበት ወቅትም ይሄ መቆም
አለበት ስል ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ “ተው
ኃይሌ አሁን ባትነካካው ይሻላል” የሚሉ
በመበራከታቸው እንጂ በቀጣይ ጉባኤም ይሁን
ወደፊት ይሄንን ማስወገድና ማስተካከል
ምርጫ ሊቀርብለት አይገባም፡፡
ሀትሪክ፡- …ምንድ ነው መስተካከል
ያለበት…?
ኃይሌ፡- የኦሎምፒክም፤ የIAAFም
በለው አንድ ቡድን መቋቋም ያለበት ከዘር፣
ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት ነፃ ሆኖ ነው ይላል፤
እኛ ግን አሁንም ከዚህ ጋር የሚጋጭ ሥራ
እየሠራን መሆኑን ስታይ ትደነግጣለህ፡
፡ ቡድኖቻችንን ያዋቀርነው ወይም
የምናወዳድረው የትግራይ ክልል፣ የኦሮሚያ
ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የቤንሻንጉል ክልል
ምናምን እያልን ነው፡፡ ይሄ በጣም ስቅጥጥ
የሚልና የሚያስፈራ ከአለም አቀፉ መርህ ጋር
የሚጋጭ ትልቅ ስህተት በመሆኑ በፍጥነት
ልናርመው ይገባል፡፡ በስፖርት ውስጥ አንድ
ቡድን ሁለተኛ ሽንፈት የሚሸነፈው ዘርን፣
ክልልን፣ ፖለቲካን መሠረት አድርጎ ሲቋቋም
ነው፡፡ ስፖርተኛው፣ አመራሩ በዚህ ሠርክል
ውስጥ የገባ ዕለት ሌላው ሞት ነው፡፡ የአማራ፣
የትግራይና የኦሮሚያ ክልል እያልን አሁንም
የምንወዳደር ከሆነ አደጋ ስላለው መለወጥ
አለበት፡፡
ሀትሪክ፡-በያዝነው አመት የተካሄደው
የካናዳ አቷዋ ማራቶንን ያሸነፈችው አትሌት
ገለቴ ቡርቃን ከድሏ በኋላ እዛው ካናዳ
ኦታዋ ላይ አግኝቼያት ከለንደን የአለም
ሻምፒዮና ስለመቀነስዋ ጥያቄ አንስቼባት
“ኃይሌ ገ/ስላሴ ሁለቴ አስለቅሶኛል አንዴ
ሮጦ ሲያሸንፍ በደስታ አልቅሻለሁ፤ አሁን
ደግሞ እሱ በተራው ከውድድር ውጪ አድርጎ
አስለቅሶኛል” ብላ የከረረ ቅሬታ አቅርባብሃላች።
ምናልባት በዚህ ደረጃ ቅሬታ ያቀረበችብህ
እሷን አስቀንሰህ አልማዝ አያናንና ጥሩነሽ
ዲባባን ይዘህ በመሄድ ይሆን….?
ኃይሌ፡- …ፈገግ እያለ…አልማዝ አያና
እንድትሄድ የተደረገው ከእሷ ጋር የተለየ
ትውውቅና ቅርበት ስላለኝ አይደለም፤
ለቅርበት ለቅርብት ከአልማዝ አያና ይልቅ
ገለቴ ቡርቃ ናት በጣም የምትቀርበኝ፡፡ ካለን
በጣም የቀረበ ግንኙነት መጥቀም ካለብኝ
መጥቀም የነበረብኝ ገለቴን ነበር፤ ነገር ግን
ጉዳዩ የመጥቀም ሣይሆን የውጤት በመሆኑ
አላደረኩትም፡፡ ገለቴን ተዋትና በእሷ ቦታ
የአብራኬ ክፋይ ልጄም ብትሆን ከቻለች ቻለች
ካልቻለች አዝናለሁ ምንም ልረዳት አልችልም
ወደ ቤትሽ ሂጂ ነው የምላት፤ ይሄ የእኔ
ፕሪንስፕል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለዚህ ለአልማዝና ለጥሩነሽ
የሚያደላ ውሳኔ ወስኜ ገለቴን አልበደልኩም
እያልክ ነው….?
ኃይሌ፡- …ትክክል…፤ ደግሞም እነሱ
ይሄዱ ብዬ እኮ አላፈረኩም፤ ውሳኔውም
ትክክል ነበር፡፡ ምክንያቱም አልማዝና ጥሩዬ
ወርቅና ብር አመጡ እኮ፡፡ ከገለቴ ቡርቃም
ከአልማዝና ከጥሩነሽም በላይ በወቅቱ
የሚቀርበኝ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? የወርቅ
ሜዳልያው ነው፤ እንጂ በቅርበት ካየህ ገለቴ
በጣም ቅርቤና ጥሩ እህቴም ናት፡፡ ይሄንን
ማድረጌን በራስዋ ስሜት ወይም በተሳሳተ
መንገድ አይታው ከሆነ በዚህ አጋጣሚ
ይቅርታ እጠይቃለሀ፤ ከዚህ ውጪ እሷን
በድዬ ሌላውን የምጠቅምበት ምንም ምክንያት
የለም፡፡
ሀትሪክ፡- የቼልሲ ደጋፊ እንደነበርክ
አውቃለሁ…፤… አሁንስ…?
ኃይሌ፡- …ሞውሪንሆን… ተከትዬ
ማንችስተር ዩናይትድ ገብቻለሁ፤
ሀትሪክ፡- …የሞውሪንሆው ማን.ዩናይትድ
አሁን የሚገኝበት የውጤት ቀውስንስ እንዴት
አየኸው…?
ኃይሌ፡- …ፊተኞች ኋለኞች ይሆናሉ
የሚለው ቃል ተፈፀመ በሚለው ያዘው፤ከዚህ
ውጪ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንም የውጤቱን
የመክፈቻ ቁልፍ ይዘው መሄዳቸው
ሞውሪንሆን አሁን ለሚገኝበት ደረጃ
ዳርጓቸዋል… (ሳቅ)…፡፡
ሀትሪክ፡- …በፊት ከቴሌቭዥን
ፕሮግራሞች የአይናችን ፕሮግራም ቀንደኛ
ተከታታይ እንደሆንክ አውቃለሁ አሁንስ…?
ኃይሌ፡- … ሳቅ… አሁን “የምን ልታዘዝ?”
የቴሌቪዥን ድራማ ተከታታይ ነኝ… (ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …እኔ ጨረስኩ… ቀረ
የምትለው ካለ እድሉን ልስጥህና በድፍረት
ለተነሱት ጥያቄዎች ለሰጠኸኝ ድፍረት ያለው
ምላሽህ ከልቤ አመሰግኜህ እንለያይ…?
ኃይሌ፡- …ከዚህ በላይ ደግሞ ምን
ቀረህ?… ስንቱን አስለፈለፍከኝ…፤ በል…ሂድ
ልኝ… ውጭ ብዙ… እንግዶች ይጠብቁኛል፤..
ቻው …! ቻው…!! ሀ
photo source – getty images and social medias