“ኢትዮጵያ ውስጥ ሕልሜን አሳክቻለሁ፤ በአፍሪካ መድረክ ከፋሲል ጋር አዲስ ታሪክ ማፃፍን እመኛለሁ”
“ኢትዮጵያ ውስጥ 8ዐ በመቶ ደሞዝ መክፈል እንኳን አይችሉም፤ የፋሲል ተጨዋች ባልሆን ምርጫዬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይሆን ነበር”
ሚኬል ሳማኪ (ፋሲል ከነማ)
N’tiji Mikel Samake
የማሊውን ዱጉዎሎፊላን ለቆ ኢትዮጵያዊውን ፋሲል ከነማን የተቀላቀለው በ2010 ዓ.ም. ነው፡፡ ከመጣበት ቀን ጀምሮ አቋሙን ጠብቆ በመጣበት አራተኛ ዓመት የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል፡፡ ንቲጂ ሚኬል ሳማኬ ከሁለት ዓመት በፊት የሊጉ ምርጥ ተጫዋች ከፋሲል ስለበር እንጂ እኔምምርጥ ግብ ጠባቂ መሆን ይገባኝ ነበር ይላል፡፡ ኣምና ወድድሩ በኮቪድ ምክንያት ሲቋረጥ ክለቡ ፋሲል የሰንጠረዡ ኣናት ላይ ነበር እሱ ደግሞ ትንሽ ግብ የተቆጠረበት እና በርካታ ጨዋታ ያለግብ የዘለቀ ሆኖ በመምራት ላይ ነበር፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ ተሳክቶለት ክለቡም ሻምጲዮን ሆኗል እሱም የሊጉ ምርጥ ዘበኛ ሆኖ የወርቅ ጓንት አሸንፏል፡፡ የፋሲል ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬ የዛሬ የ« Big interview » እንግዳችን ነው መልካም ንባብ
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፡- ሚኬል ሳማኬ እንኳን ደህና መጣህ ! ዘንድሮ መንታ ድል ነው ያስመዘገብከው፣ ክለብህ ፋሲል ከነማ የዓመቱ ሻምፒዮና ሲሆን አንተ ደግሞ በግልህ የዓመቱ የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ በረኛ ሆነህ ተመርጠሃል ምን ተሰማህ?
እኔም ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለው፡፡ ሻምፒዮና መሆን በጣም ደስ ይላል፡፡ በዛ ላይ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሲጨመርበት ደስታው ታላቅ ነው፣ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እውነት ነው ህልሜ ተሳክቷል ኢትዮጵያ ውስጥ እምመኘውን አሳክቻለው አሁን ደግሞ በአፍሪካ መድረክ ከፋሲል ጋር የተለየ ታሪክ ብጽፍ ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ዘንድሮ ውድድሩ ባንጻራዊነት ቀለል ያለ ነበር ምክንያም አንድ ቦታ ተቀምጦ መጫወትና በቀናት ልዩነት በመኪና እየተጓዙ መጫወት አንድ አይደለም፣ እስቲ ስላለፈው ውድድር አጠቃላይ ግምገማህን ንገረን ?
እውነት ነው ዘንድሮ ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት ቀለል ይላል፡፡ አዘጋጆቹ በዚህ መልኩ ሻምፒዮናውን ማሰባቸው እጅግ የሚያስመሰግን እና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ብዙ አልደከምንም እዛው ባለንበት ስለነበርን ለተጫዋቾች የተሻለ ነበር፡፡ ለክለቦችም ወጪ በአንጻራዊነት የተሻለ የነበረ ይመስለኛል ከቦታ ወደቦታ፣ ከክልል ወደክልል መዘዋወር ስላልነበረው ወጪ ቆጣቢ ነበር፤ አዘጋጆቹ ጥሩ ነው ያደረጉት፡፡ ለተመልካች ግን ደስ አይልም፤ ማንም ተጫዋች በሜዳውና በደጋፊው ፊት ቢጫወት ነው ደስ የሚለው ነገር ግን ያው እግዚአብሔር ያመጣው ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፤
ሀትሪክ፡- ግንቦት ወር ላይ ለሃገርህ ሚዲያ የሰጠኸውን ቃለ-ምልልስ አይቼው ነበርና፤ ህልሜ ምርጥ በረኛ መሆን (የሃገሪቱን የወርቅ ጓንት ማሸነፍ ነው) ብለህ ነበር ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ ውስጥ ህልምህ ተሳክቷል ?
እውነት ነው ህልሜ እሱ ነበር የኔ ብቻ ሳይሆን የየትኛውም በረኛ ህልም ይኸው ነው ዘንድሮ ተሳክቶልኛል እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ ለዚህ ደግሞ ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለው፣ የቡድን ጓደኞቼ፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት፣ ደጋፊዎች፣ የክለቡ አመራሮች ይህ እንዲሆን አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሁሉ አመሰግናለው በጣም ነው ደስ ያለኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ የአፍሪካ ደግሞ ይቀጥላል ከፋሲል ጋር ብዙ ታሪክ መሥራት እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ለሃገርህ ማሊ ብሔራዊ ቡድን በተለያየ ደረጃ ተጫውተሃል ከ20 ዓመት፣ ከ23 ዓመት በታች፣ ለቻን ወዘተ. አሁን ግን ትንሽ ቆየህ ምናልባት የዘንድሮ አቋምህ በቂ የሚዲያ ሽፋን አሰጥቶሃል እና ወደዋናው ብሔራዊ ቡድን የሚመልስህ ይመስልሃል፤ ካልሆነስ ምናልባት ዜግነት የመቀየር ዕድል ብታገኝ ትቀይራለህ ?
አዎን እንዳልከው በተለያየ ደረጃ ለብሔራዊ ቡድን ተጫውቻለው፣ ከ20 ዓመት በታች፣ ከ23 ዓመት በታች፣ የቻን ቡድን እንዲሁም ዋናው ብሔራዊ ቡድን፤ ወሳኝ አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ለሃገሬ ከዋናው ቡድን ጋር አድርጌያለው፤ እንዲሁም በ2015 ዓ.ም.እነሴይዱ ኬይታ፣ ሞላ ዋጌ፣ ባካሪ ሳኮን የመሳሰሉ በትላልቅ ሊጎች ላይ የተጫወቱ አንጋፋ ተጫዋቾች የነበሩበት የኢኳቶሪያል ጊኒው የአፍሪካ ዋንጫ የቡድኑ አባል ስለነበርኩሁሌም ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁንም እኔ አቋሜን ጠብቄ እስከሰራው ድረስ ይጠሩኛል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከአሰልጣኞች ቡድን ጋር መልካም ግንኙነት አለኝ፡፡ የመጠራት ዕድሉ ያለኝ ይመስለኛል ፍላጎቱ ሲኖር ይጠሩኛል ብየ አስባለው ከጠሩኝ ለመመለስ እኔ ሁሌም ዝግጁ ነኝ፡፡ ዜግነት መቀየር ላልከው የምችል አይመስለኝም ምክንያቱም ዋናው ቡድን ተጫውቻለው፣ የሚቻል ከሆነ ግን ለምን አልቀይርም ለኔ አዲስ ልምድ ነው ፡፡
ሀትሪክ፡- ስለዘንድሮው የአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር እናውራ እስቲ ተጎድተህ ወጣህ ያንተን መጎዳት ተከትሎ ግብ ተቆጠረባችሁ ፋሲልም በዛው ከውድድር ወጣ፤ እስቲ ስለጉዳትህ ምናልባትም ክለቡ በጣም ወሳኝ ተጫዋች ነኝ ብለህ እንዳታስብ አያረግህም ?
የቡድኑ አንድ አባል ነኝ በፍጹም ከሁሉም በላይ በጣም አስፈላጊው ሰው ነኝ ብየ አላስብም፡፡፡ በቡድኑ ውስጥ ሁሉም ሰው እኩል አስፈላጊ ነው፡፡ የአንዳችን ሚና ከሌላችን አይበልጥም ወይም አያንስም፡፡ እግር ኳስ ቡድኑ ውስጥ 30 ተጫዋቾችና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ሁሉም፣ ሁላችንም የየራሳችን አስተዋጽኦ አለን፣ የኔ አስተዋጽኦ ለቡድኑ ወሳኝ ነው፤ የኔ ብቻ ሳይሆን የማንም፣ ከግብ ጠባቂ ጀምረህ እስከአጥቂ፣ ተቀያሪ ወንበር ላይ ካለው ተጫዋች ጀምረህ እስከአሰልጣኝ ቡድኑ እንዲሁም አመራሩና ደጋፊው ሁላችንም የተናጠልናየቡድን ኃላፊነት አለብን፡፡ እንደቡድን ተጫውተን ነው ውጤቱን ያመጣነው፡፡ ጉዳቱ እኔንም አሳዝኖኛል ጨዋታውን ብጨርስ ደስይለኝ ነበር፤ነገር ግን ሆስፒታል ደርሼ ህክምና ተደርጎልኝ ሲሻለኝና ስነቃ አለማለፋችንን ሰማው ያሳዝናል፡፡ በጣም የሚዘገንን ጉዳት ነበር፡፡ ባለማለፋችን ባዝንም እግዚአብሔር ይመስገን ተርፌያለው፣ አሁንም ከምን ጊዜውም በላይ በአካልም በሞራልም ዝግጁ ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውጪ ሃገር ግብ ጠባቂ ማሰፈረምን የሚከለክል ህግ ለማውጣት እያሰበ ነው፣ እዚህ ላይ አስተያየት ይኖርሃል ?
እውነት ለመናገር ውሳኔው ትክክለኛ አይመስለኝም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሠራ የውጭ ሃገር ግብ ጠባቂ እኔንም ይመለከተኛል፡፡ የውጪ ሃር ግብ ጠባቂዎች ለሃገሪቷ እግር ኳስ አሉታዊ አስተዋጽኦ ነው ያላቸው ማለት ልክ አይመስለኝም፡፡ እንደኔ እንደኔ ሙሉ በሙሉ ከመከልከል እንዴት በተሻለ ሁኔታ ሃገርን እንዲጠቅም ቢታሰብበት ደስ ይለኛል፡፡ እኔ ከማሊ ስመጣ ማንንም አላውቅም ብሄድም ክለብ ለማግኘት አልቸገርም ሌላ ሃገር መጫወት እችላለው፤ አሁንም ብዙ ጥሪዎች አሉኝ፡፡ እኔ የራሴን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው የመጣሁት ደግሞ እያደረኩም ነው፡፡ የማልጠቅም ቢሆን ክለቤም እስካሁን አያቆየኝም፤ ታላላቅ ቡድኖችን ልትመለከት ትችላለህ ማንችስተር ዩናይትድ ግቡን የሚያስጠብቀው በስፔናዊ ነው፣ ፓሪሰንጀርሜይን ግብጠባቂው ኬይለር ናቫስ ነው፡፡ በጅምላ አስተዋጽኦ የለውም ማለት ልክ አይመስለኝም፡፡ ምልመላውን ፕሮፌሽናል ማድረግ ግን ይቻላል፡፡
ሀትሪክ፡- በያዝነው ሳምንት ውልህን ከፋሲል ጋር አድሰሃል ምን ተሰማህ ?
በጣም ነው ደስ ያለኝ ፋሲል አራት ዓመታት የቆየሁበት ቤቴ ነው በጣም ደስተኛ ነኝ ፋሲል ቤተሰብ ነው በፋሲል ቤት ደስተኛ ነኝ፡፡ ከተወሰኑ ክለቦች ጥያቄ ነበረኝ ገር ግን ከዚህ ቤተሰብ ጋር ሻመፒዮንስ ሊግ መጫወት እፈልጋለው፣ የምድብ ድልድል ውስጥ ብንገባ ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎችን ጥንካሬና ድክመት እንዴት ትገመግመዋለህ ?
እውነት ለመናገር ብዙ ምርጥ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች አሉ፤ እሚገርም እሚገርም አቅም ያላቸው ምርጥ ምርጥ ልጆች አይቻለው፤ ታዳጊም ሲኒየርም፡፡ ጥቃቅን ነገሮች ማስተካከል ከተቻለ፤ የስልጠና ዓላማውና ዓይቱን ማዘመን ከተቻለ በርካታ ግብ ጠባቂዎች ማፍራት ትችላላችሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት ፋሲል ጥሩ ተፎካካሪ ነው ነገር ግን ሻምፒዮን ለመሆን አልቻለም፡፡ ዘንድሮ በተለየ ያደረጋችሁት ምንድን ነው
የመጀመሪያው እንደቡድን ጥሩ ሆነን መስራታችን ነው፡፡ ፋሲል ሁሌም ምርጥ ልጆች አሉት እንደቡድን መናበብ መሰራት ላይ ስንሠራ የነበረው፡ በ2019 ለጥቂት ነው ዋንጫውን ያጣነው አምናም ግን ሻምፒዮናው ባይቋረጥ እምናነሳበት ዕድል ነበር፡፡ ያው ዘንድሮ እኛ ካልሆንን ማን ሊሆን ይችል ነበር በጣም ወጥ የሆነ ቡድን ነበር፡፡ ስለዚህ ሚስጥሩ የቡድን ሥራ፣ ህብረት፣ መከባበር፣ የማሸነፍ ጥማት ናቸው… ውድድሩን ስንጀምር ሁላችንም ዐላማችን አንድ ነው……. ማሸነፍ ብቻ፡፡ ኳስ ላይ ንተ ጥንካሬ ብቻ ሻምፒዮን አያረግህም… የተቀናቃኝህም ድክመት እንጂ፡፡የተቃራኒህን ድክመት ማወቅና መጠቀም አስፈላጊ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ባለፉት አራት ዓመታት ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሰርተሃል፤ ከምንተስኖት፣ ከውበቱ እንዲሁም አሁን ከስዩም ጋር እየሰራህ ነው፡፡ ላንተ የተለየ ነው የምትለው አሰልጣኝ ማነው ምናልባት በፋሲል ቤት የሠራም ባይሆን አብሬው ብሠራ የምትለው አሰልጣኝ ካለ
አዎን ከሶስት አሰልጣኞች ጋር ሰርቻለው፡፡ በመጀመሪያ እንዳልከው ስመጣ ያገኘሁት ምንቴን ነው ምንቴ ርጋታው ይገርማል፤ ምንቴ ሰው ያዳምጣል በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ቀጥሎ ያገኘሁት ውበቱን ነው፡፡ ውበቱ ኮስታራ ነው መሸነፍ አይወድም እሱን እወድለታለው፡፡ ሦስተኛ ያገኘሁት ስዩም ነው እሱ ደግሞ የተጫዋች አያያዙ ይገርማል፡፡ ከተጫዋቾቹ ጋር ያለው ግንኙነት በጣም አሪፍ ነው፡፡ ሥዩም ተጫዋች ሲያነሳሳ በጣም ምርጥ ነው፡፡ ሦስቱም የራሳቸው ጥንካሬ እንዲሁም የሚጎድላቸውም ነገር አለ፡፡ ሦስቱም የተለያዩ ናቸው ውበቱ ጋር ያለ ስዩምጋ ያለ ብዙ ነገር አለ፡፡ ሁለቱምጋ የሌለ ምንቴጋ ያለም እነደዚው፣ ውበቱ ያለው ስዩምም ምንቴም የሌላቸው ነገር አለ፡፡ እኔ ሶስቱንም አደንቃለው ከአሰልጣኘጋ ችግረ ኖሮብኝ አያውቅም፡፡ የኔ ኃላፊነት እሚሉኝን በአግባቡ መስማትና ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ማነም አሰልጣኝ የራሱ መንገድ አለው፤ የአሰልጣኝን ስትራቴጂ መስማትና ከሱጋር መስማማት ነው የተጫዋች ኃላፊነት፡፡ እግር ኳስ ተጫዋች እንደ እስስት ነው፡፡ ስዩም ይሄን ታደርጋለህ፣ ይሄን አፈልጋለው ይሄ ደግሞ አልፈልግም ካለ በቃ የሚፈልገው ታደርጋለህ የሚጠላውን ደግሞ ትተዋለህ፣ ለሌላውም እንደዛው ፕሮፌሽናል ተጫዋች እስስት ነው… ከዛ በቀር ግን ቢያሰለጥነኝ ብዬ የምለው ማንም የለም እስካሁን ባሰለጠኑኝ ሰዎች በጣም ደስተኛ ነኝ
ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በተቃራኒ ከገጠምካቸው ተጫዋቾች ውስጥ ምርጡ አጥቂ ማነው ምናልባት በተቃራኒ መጫወት የማትፈልገው በሌላ በኩል ደግሞ አብረህ ስትጫወት በራስ መተማመን የሚሰጥህ አብረህ ስትጫወት ወይም ብጫወት ብለህ የምትመኘው ምርጥ ተከላካይ ?
አዳነ ግርማን ! አዳነ ፈጣን ነው ጉልበቱ ይገርማል፡፡ አይምሮው በጣም ፈጣን ነው በጭቅላቱ እንደልቡ ይገጫል እኔ ከአዳነ በተቃራኒ መጫወት ደስይለኛል ምክንያቱም ትኩረት እንዳታጣ ያደርግሃል፡፡ አሁን ደግሞ አቡበከር ናስር በጣም ፈጣን አጥቂ ነው ተከላካዮችን በፍጥነት እና በብልጠት በቀላሉ ያልፋቸዋል፤ ኦኪኪ አፎላቢ፣ ኢዙ አዙካ በጣም ጥሩ አጥቂዎች ናቸው፡፡ አዳነ ከሁሉም የተሻለ አጥቂ ነው ማለት ግን ከአዳነ ፊት መጫወት አልፈልግም ማለት መሆን የለበትም፤ ያ ማለት እኮ ግብ ጠባቂ መሆን አልፈልግም ማለት ነው፡፡ እንደውም በተቃራኒ መግጠም የምፈልገው አጥቂ አዳነ ግርማ ነው፡፡
ተከላካይ ለኔ የተሟላ ተከላካይ ካዲር ኩሊባሊ ነው፤ ምርጥ ኮማንዶ ! ካዲር የምትነግረውን ሁሉ ተዕዛዝ የሚቀበል ምርጥ ተከላካይ፡፡ ያሬድ ያሬድ ነው ምርጥ ፊት አውራሪ የያሬድ አመራር ሁሌም ለአንድ ቡድን አስፈላጊ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የፋሲል በረኛ ባትሆን የየትኛውን ክለብ በር ልትጠብቅ ትችል ነበር ?
አሁን የፋሲል ተጫዋች ነኝ መጫወት የምፈልገውም ለፋሲል ከነማ ብቻ ነው፡፡ በፋሲል በጣም ደስተኛ ነኝ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ክለቦች የተጫዋቾቻቸውን ደሞዝ እንኳን ባግባቡ አይከፍሉም፡፡ ፋሲል ደሞዛችንን ባግባቡ የሚከፍል ፕሮፌሽናል ክለብ ነው፡፡ የፋሲል ተጫዋች ባልሆን ኑሮ ምናልባት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ልጫወት እችል ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ታሪክና ፕሮፌሽናል መዋቅር ያለው ክለብ ነው አሁንም አስተዳደሩ ጥሩ ስለሚመስለኝ ጊዮርጊስን እመርጣለው፡፡
ሀትሪክ፡- ስለበረኛ አሰልጣኞችህ ደግሞ ንገረኝ እሰቲ ምን ያህል ይረዱሃል ?
የበረኛ አሰልጣኜ አዳሙ ከመጣሁበት ቀን ጀምሮ በጣም ነው የሚረዳኝ፡፡ ስመጣ ክለቡ ውስጥ እንድለምድ ያገዘኝ እሱ ነው፡፡ እንደልጁ ነው ያሳደገኝ፣ በልምምድ፣ በሞራል፣ በሥራ፣ አዳሙ በብዙ ነገር ነው የረዳኝ፡፡ በፋሲል ቤት እንድለምድ ያረገኝ አዳሙ ነው አሁንም ዕለት ዕለት አቋሜ ሳይወርድ እንድጫወት በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው አዳሙ ነው፣ እጅግ በጣም ነው የማመሰግነው፡፡
ሀትሪክ፡- በማህበራዊ ሚዲያ በርካታ ተከታይ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ አንተ ነህ በርካታ ተከታይም አለህ ምን ምን ማህበራዊ ሚዲያ ትጠቀማለህ እንዴትስ ነው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምህ…
የፋሲል ደጋፊዎች አስደናቂ ናቸው ለኔ ፍቅር አላቸው እኔም ለነሱ ክብር አለኝ፡፡ ደጋፊዎቻችን አስራ ሁለተኛ ተጫዋቾች ናቸው፣ በሄድንበት ሁሉ እየመጡ ያበረታቱናል፡፡ ስናሸንፍ የነሱን ደስታ ማየት ከምንም በላይ ደስ ይላል፤ በርግጥ ሽንፈት አይፈቀድልንም ፋሲል ቤት ሁሌም ማሸነፍ ነው ያለብህ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ዎን እጠቀማለው ብዙ ተከታዮች አሉኝ ፌስቡክና ኢንስታግራም እጠቀማለው ይወዱኛል፣ ያበረታቱኛል፣ ይጽፉልኛል፤ ከደጋፊዎች ጋር የምገናኘው በማኅበራዊ ሚዲያው ስለሆነ እጠቀማለው፡፡
ሀትሪክ፡- በትርፍ ጊዜህ ምን ያስደስትሃል ?
በትርፍ ጊዜ ፊልም አያለው፡፡ ፊልምና ሙዚቃ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ልምምድ ከሌለ ሙሉ ቀን ተኝቼ ፊልም ላይ እችላለው፤ ፊልም ካልሆነ የሙዚቃ ክሊፖችን አያለው፣ አዎ ፊልምና ሙዚቃ ናቸው የትርፍ ሰዓት ሥራዎቼ፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ውስጥ የልብ ጓደኛህ ማነው ? አብዛኛውን ጊዜህን ከማን ጋር ታሳልፋለህ ? ፋሲል ውስጥ በጣም የሚያስቃችሁ ሰው ማነው ? ምርጡ ደናሽ ? ዘፋኝ ? ምናልባትም ተመጋቢ ?
ፋሲል ውስጥ የልብ ጓደኛዬ ኩሊባሊ ነው፡፡ አዎ ሊሆን የሚችለው ኩሊባሊ ነው በባህል፣ በቋንቋ የሚቀርበኝ እሱ ነው ስለሁሉም ነገር እናወራለን፣ ችግሬንም ደስታዬንም ለሱ ነው የማጋራው እሱም እንደዛው ነው፤ ምንም ነገር ሲኖረው ከኔ ጋር ነው የሚያወራው፡፡
ፋሲል ውስጥ በጣም አስቂኙ ሰው ሽመክት ነው፡፡ አውቶቢስ ውስጥ፣ ሆቴል ውስጥ ልምምድ ላይ፣ መልበሻ ክፍል፣ ሽመክት ካለ ሳቅ አለ፤ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ነው የሚያስቀው፤ አንድ ቡድን ውስጥ እንደሽመክት ዓይነት ሰው በጣም ነው የሚያስፈልገው፤ ለመነሳሳት ወሳኝ ነው፡፡ ፋሲል ውስጥ ሽመክት ሪትም ነው፤ ይደንሳል፣ ይፎግራል፣ ይዘፍናል፣ ይጮሃል እብድ ነው፤ እወድሃለው በልልኝ አቦ፡፡
ሀትሪክ፡- ጎንደር ወይስ አዲስ አበባ የት መጫወት ይበልጥ ደስ ይልሃል ?
እኔ ጎንደር መጫወት እመርጣለው፤ ከጎንደር ውጪ ካልከኝ ግን አዲስ አበባን እመርጣለው፡፡ አዲስ አበባ እንደምታውቀው ዋና ከተማ ነች፣ ለሁሉም ነገር መዲና ነች አዲስ መጫወት በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ለመጪው ዓመት ዕቅድህ ምንድን ነው ?
ዋናው ዓላማዬ ዘንድሮ በግሌም ሆነ በቡድን ያገኘነውን ክብር ማስጠበቅ ነው፡፡ በተከታታይ ሻምፒዮን መሆን ዋናው ዓላማችን ነው በግልም በድጋሚ የውድድሩ ምርጥ በረኛ ሆኖ መመረጥ እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከፋሲልስ ዘንድሮ ምን እንጠብቅ በአፍሪካ ውድድርስ የተለየ ነገር ማሰብ እንችላለን ?
ፋሲል በተከታታይ ዓመታት ዋንጫውን በማንሳት ታሪክ ይጽፋል፡፡ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወደምድብ ድልድል መግባት ነው ዕቅዳችን፤ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፈን ምድብ ማጣሪያ ከገባን በኋላ ደግሞ አብረን እናያለን አሁን ግን ወደምድብ ድልድሉ ገብተን ከጊዮርጊስ ቀጥለን ታሪክ መጻፍ እንፈልጋለን፡፡
ሀትሪክ፡- እርግጠኛ ነኝ ሰምተሃል አስቻለው ፋሲል ፈርሟል ያሬድ አስቻለው የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ የተከላካይ ጥምረት ይሆናል
ይሄን የሚያውቀው ስዩም ነው ኩሊባሊ ግን ቀላል ተፎካካሪ አይደለም፡፡ እሚሰለፈውን መምረጥ ቀላል ውሳኔ አይሆንም ለአሰልጣኝ ስዩም፡፡ አሁን የሊጉ ምርጥ ተከላካዮች እኛጋ ናቸው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
ሀትሪክ፡- ከመጣህ አራተኛ ዓመት አጠናቀቅክ አማርኛ እስካሁን አለመድክም ?
አማርኛ አልታማም በደንብ ማውራት አልችልም እንጂ በደንብ እሰማለው የቆየውባቸው ዓመታት ቀላል አይደሉም በነገራችን ላይ አራት ዓመት ቀስ በቀስ አማርኛን እያሻሻልኩ ነው፣ ያውም ጎንደርኛ…
ሀትሪክ፡- የበለጠ የምትወደው ኢትዮጵያዊ ምግብ ?
ዶሮ ወጥ እወዳለው የመጀመሪያ ምርጫዬ ግን አሳ ለብለብ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ታሪካዊ ቦታዎችን አየህ ?
ታሪካዊ ቦታዎች በተለይ ጎንደር ያሉትን አዎን፡፡ የፋሲል ግንብ፣ የጎንደር ከተማን አይቻለው ብቻዬን ብዙ ርቄ መሄድ አልፈልግም ግን የአጼ ፋሲል ቤተመንግስት፣ የጥምቀተ በዓልን አዎ፣ ከዛ ውጪ ለውድድር ስወጣ የሄድኩባቸውን ቦታዎች አያለው፡፡
ሀትሪክ፡- እናጠቃልል፣ ማመስገን፣ መጠየቅ፣ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ አሁን ሰዓቱ ያንተ ነው ?
በመጀመሪያ የመጀመሪያ ቃለምልልስ ዕድል የሰጠችኝን ሃትሪክን አመሰግናለው፣ አንተን አመሰግናለው፣ የኢትዮጵያ ህዝብን፣ የፋሲል ደጋፊዎች፣ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ አስተዳደር፣ የፋሲል ከነማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት፣ እስካሁን ያሰለጠኑኝ አሰልጣኞች በሙሉ፣ ሑሉም የቡድን ጓደኞቼ አሁንም ያሉ ክለቡንም የለቀቁትን አመሰግናለው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ ድካሜን አይቶ እውቅና የሰጠኝ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ሁሉንም አመሰግናለው እግዚአብሔር ይስጥልኝ (በአማርኛ)