የወልዋሎች 4ዐ አስጨናቂ ቀናቶች በትግራይ
“ሙሉ ድጋፍ አድርጎ የተቆረቆረልን የአዲግራት ነዋሪ እንጂ ክለቡ አይደለም”
አክሊሉ አየናው /ወልዋሎ አዲግራት/
ያለፈውን 1 ወር ከ24 ቀን አካባቢ ከሞት ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጠ መቆየታቸውቸን ይናገራል… ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡ ደግሞ ሲረብሸው ሲጨነቅበት ከርሟል… ለወልዋሎ አዲግራት ፊርማውን አኑሮ ከአዲስ አበባ ወደ አዲግራት የተጓዘው እንግዳችን ለአዲግራት ህዝብ ያለው ፍቅርና ክብር ተነግሮ አያልቅም፡፡ “የምር ልቤን ማርከውታል ከኛ ጎን ሆነው ያላቸውን ያለስስት ሰጥተውናል፤ ለዚህ ህዝብ ጦርነት አይገባም በጣም አመሰግናለሁ” ሲል ምንም አይነት ልዩነት ሳይፈጥሩ ያላቸው አካፈሉን ሲል የአዲግራትን ነዋሪ ያመሰግናል፡፡ ከከተማው መውጣት ያውም በሠላም ለኛ የሰማይ ያህል ርቆብን ነበር የሚለው የዛሬው እንግዳችን አክሊሉ አያናው ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ አዲግራት ህዝብ፣ ስለጦርነቱ፣ ምግብና ውሃ ተቸግረው ነበር ስለመባሉ፣ ከክለቡ አመራሮች ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፣ መትረፉንና ቤተሰቡን በነፃነት እንደሚያገኝ ስላረጋገጠባት ቀን፣ ፕሪሚየር ሊጉ በዲኤስ.ቲቪ መተላለፉ ስላለው ጥቅም፣ ስላሳለፈው የተጨዋችነት ዘመኑ እና ስለሚሰማው ስሜት፣ ለፕሪሚየርና ለከፍተኛ ሊግ ክለቦች በሩ ክፍት ስለመሆኑና ሌሎች ጉዳዮች ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡-እንኳን በሠላም ወደ አዲስ አበባ ተመለስክ… ከቤተሰብ ጋር በሠላም ተገናኘህ?
- ማሰታውቂያ -
አክሊሉ፡- አዎ በሠላም ተገናኝቻለሁ ያለፈው ጊዜ ለቤተሰብ በጣም ያስጨነቀ ጉዳይ ነው ድንገት ለስራ ብለህ ወጥተህ ድምፅህ ሲጠፋና ያለህበትን ቦታና ሁኔታ ሳያውቁ መረጃ ሲያጡ ይረበሻሉ እንኳን ቤተሰብ የአካባቢው ያሳደገህም ማህበረሰብ እንደዚያ ነበር ሲጨነቅ የነበረው… የመጀመሪያ ስልክ ስቀበል የነበረው ስሜት ከባድ ነው… ሁሉም አልፎ ስላገኘኋቸው እግዚብሔር ይመስገን፡፡
ሀትሪክ፡- ምናልባት የመጀመሪያ ስልክ የተደወለልህ ከማን ነበር.. ምን ስሜት ተስማህ?
አክሊሉ፡- የመጀመሪያ ስልክ የተቀበልኩት የባለቤቴን ነው… ድምጿን ስሰማ ደነገጥኩ የሆነ ነገር ነዘረኝ ደስታዬን መግለፅ አልቻልኩም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተነሳሁና አዲግራት ከደረስን በኋላ መጨረሻ ላይ የደወልኩት ለርሷ ነው… ኔትወርኩም ሲከፈት የመጀመሪያ የስልክ ጥሪ የርሷ ነበር ስሜቴን መግለፅ ይከብደኛል ብቻ እግዚአብሔር ይመስገን ማለት ብቻ ነው የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡-አዲግራት የነበረው ስሜት ምን ይመስል ነበር? እንዴትስ ሳይከብድ መውጣት አልቻላችሁም?
አክሊሉ፡- ክለቡ ባደረገው ጥሪ መሠረት አዲግራት ላይ ተሰባስበን ልምምድ ልንጀምር ስንል ያልተሟሉ ነገሮች ስለነበሩ እስኪሟሉ ጠበቅንና ልምምዱ ለመጀመር የተነሳበት ጥቅምት 24/2013 ደግሞ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ትንሽ ከበድ ያለ ነገር ነበር… በእርግጥ አዲግራት ላይ የከፋ ጦርነትና እልቂት አልነበረም ህብረተሰቡም ያለውን እውነት በመቀበል ከከተማ የመውጣት ሂደት ነበር.. በቅርብ ርቀት የከባድ መሳሪያ ተኩሶች ይስሙ ስለነበር ሁሉም የመሸሽ ፍላጎት ነበረው፡፡ አዲግራት ደግሞ በተራራ የተከበበች ከተማ በመሆኗ የነበሩበትን ቦታ በመልቀቅ ወደ ተራራዎቹና ገጠራማ ስፍራዎች የመውጣት ነገር ነበር… ደገሀሙስ ከአዲግራት ወጣ ያለ ስፍራ ሲሆን ከባድ እልቂት የነበረበትም ቦታም ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ምግብና መጠጥ ተቸግራችሁ ነበር?
አክሊሉ፡- የአዲግራትን ህዝብ በጣም አመሰግናለሁ እንደራሱ ልጅ የቤተሰብ አካል አደርጎ በርበሬ ሽሮ መኮረኒ ፓስታ ሳይቀር በማምጣት በምግብ በኩል እንዳንቸገር አድርገውናል ካምፓችን ድረስ እየመጡ ውሃም በማቅረብ ሙሉ ድጋፍ አድርገውልናል እነሱን ከልብ ማመሰገን እፈልጋለው፡፡ እንዲሁ ባይተዋርነት እንዳይሰማን እናንተ የኛ አምባሳደር ናችሁ የሚያስፈልገው ነገር አይጎልም ብለው ከጎናችን ነበሩ የአዲግራት ነዋሪ ከክለቡ በተሻለ መልኩ ደግፎናል አግዞናል፡፡
ሀትሪክ፡-የክለቡ አመራሮች ጋር ግንኙነት አልነበረም?
አክሊሉ፡-አዲግራት ከገባንበት ሰዓት ጀምሮ ከስራ አስኪያጁ ሚካኤል አምደ መስቀል እና ከቴክኒክ ዳይሬክተሩ ውጪ የትኛውም የቦርድ አባልና የስራ አስፈፃሚ አላገኘንም ሳናገኛቸውም ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣነው፤ ሙሉ ድጋፍ አድርጎ የተቆረቆረልን የአዲግራት ነዋሪ እንጂ ክለቡ አይደለም፤ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው የሚያስፈልገንን ነገር አላሟላም፡፡ ገና ስንሄድም ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም አንፃር ያልተሟሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከ7 ወር በኋላ የተገኘ የመጫወት እድል በመሆኑና ጉጉቱ ስለነበረን ኳስ የመጫወቱ ነገር በልጦብን እየሰራን ሊሟሉ የሚገባቸውን ስንጠይቅ ቆይተናል.. ክለቡ ብዙም ድጋፍን አላደረገልንም፡፡
ሀትሪክ፡- ባንኮች ዝግ መሆናቸው የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች እጥረት መከሰቱ ጫና አልፈጠረባችሁም?
አክሊሉ፡- ችግሮችማ ነበሩ… መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት ተቸግረን ነበር እውነት ነው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ገንዘብ አዋጥተው የመደገፍ ነገር በመኖሩ አልተቸገርንም… በቅርብ ደግሞ የቡድናችን አባል የሆነው የአይናለም ኃይለ እናቱ እዚያ ስለነበሩ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማዘጋጀት ያመጡልን ስለነበር አልተቸገርንም እንጂ ክፍተቱና ችግሩ ሰፊ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- በፌስቡክ ገፅህ ላይ የሠላም ዋጋዋ ስንት ነው? ብለህ ጠየቅ… እስቲ አብራራው?
አክሊሉ፡- ሠላም ሲጠፋ የሚሆነውን ነገር ቦታው ላይ ካልነበርክ ሊገባህ አይችልም፡፡ ሠላም ቀላል ነገር ይመስለናል እንጂ ሠላም በየትኛውም ዋጋ የሚተመን አይደለም… በአንደበትህ በቀላል የምትገልፀው አይደለም ሠላም ሲኮን ወጥተህ መግባት ሠርተህ መኖር ትችላለህ ልጅ ታሳድጋለህ ቤተሰብ ትመራለህ አገር ሠላም ከሆነ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ይቻላል ሠላም ከሌላ ያልናቸውን ነገሮች በሙሉ በዜሮ ይባዛሉ ይህን አይቼ ለመግለፅ ብዬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከፍርሃቱ ወጥተህ በቃ አሁንስ ተርፍን ያልከው የት ስትደርስ ነው?
አክሊሉ፡- እውነት ለመናገር ከአዲግራት ከተማ መውጣት በጣም ከባድ ነበር ምንም መረጃ አልነበረንም የተለያየ የተዛባ ወሬ እንሰማ ስለነበር ፈርተን ነበር ኔትወርክ መብራት የለም.. በጣም ከባድ ነበር ከአዲግራት ደግሞ ትንሽ ወጣ ስንል ደገሐሙስ ላይ ከፍተኛ ጦርነት የተካሄደበት ቦታ ነው ያቺን ስፍራ ለቀን እስክንወጣ ድረስ ስጋት ነበረኝ በኋላ ላይ ግን መከላከያ ሠራዊታችንን ስናይ እንደ ሀገር የሚሰማን ስሜት ነበር ባንዲራችንን ስናይ የተፈጠረብን የደስታ ስሜት ነበር፤ የመከላከያ ሠራዊቱን በየመንገዱ እያየን ስንመጣ ልባችን በተስፋ ተሞላ ጥሩ ጊዜ እንደሚኖርም ገባን መቐሌ ከደረስን በኋላ ደግሞ በረራው ሲጀመር የመጀመሪያው በራሪ እኛ ስለነበረን በረራው መሠረቱን እስኪይዝ ድረስ አዲስ አበባ ለመግባቴ ርግጠኛ አልነበርኩም ፀሎት እያደረግንም ነበር ትክክለኛ መስመሩ ላይ ሲገባ ሁላችንም ተረጋጋን ደስም ብሎን አዲስ አበባ እንደምንገባ አረጋገጥን ብቻ የነበረው ሁኔታ ይጨንቃል፡፡
ሀትሪክ፡-ከአዲግራት መቐለ በምን ተጓዛችሁ?
አክሊሉ፡- ከአዲግራት ለመውጣት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገናል ወደ አምስት ተጨዋቾች እኔ አይናለም ኃይለ፣ ሽመልስ ተገኝ፣ ወንደወሰን እና አመለ ሚኪያስ ተወክለን ብዙ ሞክረናል የተለያዩ ቦታዎች ሄደናል ደብዳቤ አፅፈናል ያንን ሁሉ አድርገን አልተሳካም የመጨረሻዋ ቀን የመከላከያ ሰራዊት ኦራል መኪና ሹፌር አገኘንና ያለውን ሁኔታ በዝርዝር አስረዳነው ሹፌሩ ቀና ሰው ስለነበር ተባብሮን በኦራል መኪና ተጭነን መቐለ ገባን፤ ይሄ ሁሉ በራሳችን ያደረግነው ትግል ተሳካቶልን እንጂ ማንም አልረዳንም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሹፌሩን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ይሄ ሁሉ የአምስታችሁ ተጨዋቾች ውክልናና ትግል ላይ ክለቡ ምንም ያደረገው ነገር የለም?
አክሊሉ፡-በፍፁም የለም ምን እንብላ እንጠጣ ምን ያስፈልጋቸዋል? ያመጣናቸው እኛ ነን ኃላፊነት አለብን ያለ አንድም የክለቡ ሰው አልነበረም፡፡
ሀትሪክ፡- በአዲግራት ቆይታችሁ አመስግን ተብለህ እድሉን ብታገኝ ማንን ታመሰግናለህ?
አክሊሉ፡- የአዲግራት ህዝብ ላሳየን ፍቅርና ክብር ከልብ አመሰግናለሁ ያለኝን አክብሮትና ምስጋና አቀርባለው፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሰስቱ ያላቸውን አካፍለውናል ከዚያ ውጪ አይናለም ኃይለና እናቱን አመሰግናለሁ… አይናለም በደደቢትም አብረን ተጫውተናል ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ከአጠገባችን ሳይለይ ከእናቱ ጋር ሆኖ ስንቸገር አብረው እየተቸገሩ ስንራብ አብረው ከጎናችን ሆነው ደግፈው እናትና ልጅ አግዘውናል በእግዚአብሔር ስም ማመስገንን እፈልጋለው እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው ይሄ የአዲግራትና የአካባቢው ህብረተሰብ ሳይኖረው ያለውን ያካፈለን መልካም ባህሪ ያለው ህዝብ ነው አሁን ግን ትልቅ ችግር ላይ ነው ያለው መብራት፣ ውሃ፣ ትራንስፖርትና ባንክ ግልጋሎት እየተሰጡ አይደለም፡፤ይህም ኀብረተሰቡ ከባድ ችግር ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ የሚመለከተው አካል ቶሎ ችግሩን እንዲቀርፍላቸው ጥሪ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ዘር ተኮር ጫና አልገጠማችሁም?
አክሊሉ፡- በፍፁም አልነበረም ሙሉ ህብረተሰቡ ከጎናችን ሆኖ ክፉውን ጊዜ አልፈናል ይሄ ነው እውነቱ ህዝቡ ምርጥ ነው፡፡ ህዝቡ ሲያበረታታና ሲደግፈን በኳሱ የምንወክለው ይህን ህዝብ ነው በደንብ ተጠናክረን ልናስደስተው ይገባል ብለን ስንተጋ ነበር መጨረሻ ላይ ግን አልተሳካም፤ ህዝቡ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይደርስብን አድርጓል፤ ምርጥ ህዝብ ምርጥ ባህሪ ያለው ምርጥ አመለካከት ያለው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡
ሀትሪክ፡-ቤተሰቦቼን አላገኛቸውም ብሎ ልብህ አልሰጋም?
አክሊሉ፡- ትንሽ ነገሮች መስመራቸውን እየሳቱ ከመጀመርያው ይልቅ ጠንክር እያለ ሲመጣ ከቤተሰቦቼ ጋር የምገናኘው እንዴት ነው? እንዴትስ ነው ከከተማው የምወጣው ብዬ ጨንቆኝ ነበር አደጋው ከባድ ስለነበርና ስለተጨነቅኩ እንቅልፍ የለም ተረጋግቼ ማሰብ አልቻልኩም ከጓደኞቼ ጋር ሳይቀር በነፃነት ማውራት መጫወት አልቻልኩም ሃሳብ ይዞኝ ይሄዳል በጣም ፈርቼ ነበር….፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን ተርፋችሁ አዲስ አበባ ገብታችኋልና ፌዴሬሽኑ የዝውውር መስኮቱ ቢዘጋም የናንተን በልዩ ችግር አይቶ ክለብ ካገኛችሁ ዝውውር እንድታደርጉ ፈቅዷል… ለክለቦች ማለት የምትፈልገው ነገር አለ?
አክሊሉ፡- አዎ! 2013 መጫወት እፈለጋለሁ በርግጥ የፕሪሚየር ሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች ቁጥር ማነሱና 13 ብቻ መሆናቸው ተጨዋች የመያዝ አቅማቸውና ፍላጎታቸው ሊወርድ ይችላል ይህን እረዳለሁ ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ ስዘጋጅ ስለነበር ለጨዋታ ዝግጁ ነኝ የፕሪሚየር ሊጉም ይሁን የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ሊወስዱኝ ከፈለጉ በሬ ክፍት ነው መጫወት ስራዬ ነው ለስራዬ ደግሞ ዝግጁ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ኳስ የቆመበትን 7 ወራት እንዴት አለፍከው…?
አክሊሉ፡-ትንሽ አሰልቺ ጊዜ ነው ያሳለፍነው.. ውድድሩ በመቋረጡና ግንኙነቶች በመቅረታቸው እንቅስቃሴያችንም ቤት ውስጥ ስለነበርና ቤት ውስጥ ሲሆን የሚሰሩት ስራዎች ደግሞ ውስኖች ስለነበሩ ያሰለች ነበር በጣምም ፈትኖኛል አስቸጋሪ ጊዜውን አልፈን ውድድሩ ሊጀመር ሲል ጦርነቱ መነሳቱ ደግሞ የባሰ ጥሩ ስሜት የማይፈጥር ክስተት ሆኖብኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ፕሪሚየር ሊጉ በዲ.ኤስ.ቲቪ የመታየቱ ነገርስ ለተጨዋቾች ትልቅ ጥቅም አላመጣም?
አክሊሉ፡-ትልቅ ጥቅምማ አለው… በተለይ ለተጨዋቾች ትልቅ ተስፋ ፈጥሯል፡፡ ለነገ የተሻለ ነገር ማለም እንድንችል የተሻለ ቦታ ላይ የመድረስ ራዕይ እንዲኖረን አድርጓል፤ በእኛ በኩል ጠንክረን ከሰራን የሌሎች አፍሪካዊያን አገራት ተጨዋቾች በአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች ላይ እንደሚታዩት በኛም ሀገር ምርጥ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች ስላሉን ይህን እድል ለማሳካት በር ከፍቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡-የተጨዋችነት ዘመንህ ከየት ይነሳል?
አክሊሉ፡-ከባንክ ታዳጊ ቡድን ይጀምራል ታሪኬ… ከዚያ ፋሲል ከነማ፣ ሙገር፣ ከዚያ ውጪ የመን ሄጄ ለአንድ አመት ተጫውቼ ተመለስኩ ከዚያ መልስ ወደ ደደበት ገባሁ.. ኢትዮጵያ ቡና ብሎ የመጨረሻው ወልዋሎ አዲግራት ጋር ይደርሳል ቀጣዩን ክለቤ በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡-የጦርነት ነገር ተደጋገመሳ.. የመን ሄደን ጦርነት ተነሳ.. ወልዋሎ አዲግራት ልትጫወት ሄደህ ጦርነቱ ተከሰተ.. ይሄ ነገር ጦርነት ጠሪ ያስባለህ አይምስልህም…?
አክሊሉ፡- /ሳቅ በሳቅ/ በአጋጣሚው ሆኖ የነካኋቸው ክለቦችና ከተሞች ጦርነት ያገኛቸዋል /ሳቅ/ ይሄ ገጠመኝ ደግሞ ከባድ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-በተጨዋችነት ዘመንህ ያንተ ምርጡ አሰልጣኝና ተጨዋች ማነው?
አክሊሉ፡- ከአሰልጣኝ ያለጥርጥር ገ/መድህን ኃይሌ ነው ከተጨዋች ደግሞ ታደለ መንገሻ ምርጫዬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ ቆይታህን ስታየው የድል ነው? ወይስ የባከነ ይመስልሃል?
አክሊሉ፡-በዚህማ ደስተኛ ነኝ የድል አመታቶች ይበዙበታል፡፡ ከባንክ ቢ ቡድን ሲነሣ በዋንጫ የታጀበ ነው፡፡ በፋሲል ከነማም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ በነበርኩበት ወቅት የደረጃ ተፎካካሪ ነበር ብሔራዊ ቡድን ተመረጥኩ ይህም ለኔ ስኬት ነው.. ከዚያ ደደቢት ገባሁ እዚያም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አንስቻለሁ… በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የአሰልጣኝነት ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የቡድኑ አባል ነበርኩ ኢትዮጵያ ቡና ከጉዳቱ በፊት ጥሩ ጊዜ ነበረኝ ከተጎዳሁ በኋላ ነው ችግር የተፈጠረው… ወልዋሎ አዲግራት ነው ምን ይግጠመኝ ሳላውቅ ችግሩ የተከሰተው…. በኔ በኩል ቆይታዬን ስንመግመው ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ያኔ ከደቡብ አፍሪካው የዋሊያዎቹ ስብስብ ለምን ተሰናበትክ?
አክሊሉ፡-ዛሬም ድረስ ምላሽ ያጣሁለት ጉዳይ ይሄንን ነው ከቡድኑ ብስናበትም ቤኒንን ስንጥልም ሆነ ሱዳንን አሸንፈን ለአፍሪካ ዋንጫ ስናለፍ የዋሊያዎቹ አባል ነበርኩ፡፡ መጨረሻ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ አንድ በረኛና እኔን ቀንሰው ነው የሄዱት… አሁን ድረስ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈው ቡድን ውስጥ ለምን እንደተቀነስኩ የነገረኝ አሰልጣኝ የለም… በጣም የተከፋሁበት ጊዜ ነበር የተቀነስኩበት ጊዜም በራሱ አሳማኝ ስላልነበር ስሜቴ ተጎድቶ ነበር ስንብቴም አልተዋጣልኝም… ያሰናበቱኝም አሰልጣኞች አሁንም ድረስ ምክንያታቸውን አልነገሩኝም ይሄ ደግሞ የባሰ ያማል፡፡ አሰልጣኞቻችን ይህን ማስተካከል አለባቸው ተጨዋች ሲቀንሱ ወይም ሲያሰናብቱ ተጨዋቹን ጠርተው መንገር አለባቸው… ለምን እንደቀነሱት ምን ማስተካከል እንዳለበት የመንገር ልማድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-ትልቁ የሀዘኔ ቀን ነው በለኛ?
አክሊሉ፡-በእግር ኳስ ተጨዋችነቴ በጣም ያዘንኩበትና የከፋኝ ቀን ያኔ ከቡድኑ ስሰናበት ነው የሀገርን ብሔራዊ ቡድን ወክለህ በትልቅ መድረክ ላይ የመካፈል መብትን ስታጣ ያማል ያን እድል በማጣቴ ቅር ብሎኛል፡፡
ሀትሪክ፡-ከዚያ በኋላ መመረጥ አልፈልግም የሚል ስሜት ውስጥህ አልመጣም?
አክሊሉ፡-ትተወዋለህ እንጂ ካሁን በኋላ አልጫወትም እንድጠራ አልፈልግም የሚል ስሜት ተፈጥሮብኝ ነበር፡፡ በየጊዜው እጠራለሁ አሳማኝ ባልሆነ መልኩ ደግሞ እቀነሳለሁ እስከ መቼ ሄጄ እመለሳለሁ የሚል ስሜት ይፈጥራልና አልፈልግም የሚል ስሜት ተፈጥሮብኝ ያውቃል አብዛኞቹ ተጨዋቾች ብሔራዊ ቡድንን የማገልገል ስሜት የሌላቸው አሳማኝ ባልሆነ መንገድ እየተቀነሱ ስለተቸገሩ ነውና መስተካከል አለበት፡፡
ሀትሪክ፡-ይሄን ቅሬታህን ስሰማ አንድ ገመጠኝ አስታወሰኝ… የቦክስ ተወዳዳሪ ነው አሉ ከሰፈሩ ውድድሩ ስፍራ ሁሌ በሰፈሩ ልጆች ታጅቦ ይሄዳል ግጥሚያው ሲጀመር ግን በዝረራ ይሸነፋል.. መታጀቡም በዝረራ መሸነፉም ብዙ ጊዜ ሲደጋገም አንዱ የሠፈሩ ሰው ቦክሰኛውን ጠራውና “ለምን ከአሁኑ በቃሬዛ ላይ ተኝተህ አትሄድም?” ብሎት እርፍ … እናም ተመርጦ ለመመለስ ስትመለስም ምክንያቱ ሳይነገር ሲሆን ልክ ነህ ስሜትን ይጎዳል…
አክሊሉ፡- /ሳቅ በሳቅ/ አዎ ከባድ ስሜት ይፈጥራል ክለብ ላይ ጥሩ ሆነህ ተመርጠህ ትሄድና ወዲያውኑ መቀነስ ያማል.. ያውም አሰልጣኞች ሲያሰናብቱህ ማስተካከል ያለብህን ነገር ሳይነግሩህ መሆኑ ስሜት ይጎዳል፡፡
ሀትሪክ፡- ከውጪ ተጨዋች የማን ወዳጅ ነህ…?
አክሊሉ፡-ያለጥርጥር የክርስቲያኖ ሮናልዶ… ለኔ ልዩ ነው ታታሪ፣ሠራተኛና የሚያነሳሳ ተጨዋች ነው ልቤ ለርሱ ያደላል፡፡
ሀትሪክ፡-ዘንድሮ አክሊሉ የአሮጊቷ ነዋ?
አክሊሉ፡-ሮናልዶን እወደዋለው እንጂ በዞረበት ሁሉ አልዞርም… ታታሪነቱ ያነሳሳኛል ያበረታኛል፤ ከምንም በላይ ተምሣሌት እንዳደርገው ውስጤ ይገፋፋኛል፤ እርሱ ለኔ ልዩ ተጨዋች ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ጨረስኩ … የምትለው የመጨረሻ ቃል?
አክሊሉ፡- እንደ ፋሽን ሆኖ ብጥብጦች ያለመረጋጋቶች በሃይማኖት፣ በዘርና በብሔር ተከፋፍሎ አንዱን ከአንዱ የማጋጨት ባህሎች ይታያሉ… እነኚህን በአጭሩ ሣንገታቸው እንደ ቀልድ የምናያቸው ከሆነ ነገ የማንቋቋመው ችግርና ፀፀት ውስጥ ሊከተን ይችላልና መታረም አለበት… ህብረተሰቡ ለሠላም፣ ለመተሳሰብ፣ ለአንድነትና ለፍቅር እራሱን ሊያስገዛ ይገባልና ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ሠላምን ያብዛልን ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ስለ ኮሮና
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የጠፋ ነው የሚመስለው… ብዙ መዘናጋቶች አሉ ይሄ መስተካከል አለበት.. ኅብረተሰቡ ያለውን ወረርሽኝ ከግንዛቤ በማስገባት በጥንቃቄ ህይወቱን ሊመራ ይገባል… መተሳሰብ ባለበት የአኗኗር ህይወት ይቺ ቀን እስክታልፍ መጣር ይኖርብናል.. አብዛኛው ሰው ማክስ ማድረግ በሳኒታይዘር እጅን ማፅዳት ላይ የተዘናጋ ይመስላል ይሄ መታረም አለት ለሌላው በማሰብ ማክስ በማድረግ የጤና ባለሙያዎች የሚሉትን ምክሮች በመተግበር ቫይረሱን መታገል ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ስለ አባይ ግድብ
የመጀመሪያው ቀን የውሃ ሙሌት የፈጠረብኝ ደስታ ልዩ ነው፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ ጊዜያት ለአባይ ግድብ በብሔራዊ ቡድን፣ በክለብና በግል ድጋፍ አድርጌያለው ይሄ ትልቅ ደስታ የፈጠረልኝ ጉዳይ ነው.. የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት ሲከናወን በኔ ጊዜ ለሀገሬ አንድ ነገር ማድረግ ችያለሁ የዚህ ታላቅ ክብር ተቋዳሽ ሆኛለሁ በማለት ለልጆቼ የምናገረው ታሪክ ሠርቻለው ብዬ ስላመንኩ ልዩ የደስታ ስሜት ተፈጥሮብኛል፡፡ የቦንድ ግዢም ይሁን 8100 A ላይ በስፋት ተሳትፎ አድርጊያለው ሁለቱም ላይ በሚባኝ ደረጃ አለው ከዚህም በኋላ እቀጥላለሁ ህብረተሰቡም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን ማድረግ አለበት በኔ በኩል እስከመጨረሻው ድረስ አቅሜ የፈቀደልኝን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡