በይስሐቅ በላይ
“ምንም የማይወጣልኝ ልቅም ያልኩ ቆንጆ ነኝ”
“እንባዬን አፍስሼ ያለቀስኩት የወጣቶች ሕይወት መቀጠፉ ያብቃ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው”
አምሳሉ ጥላሁን
የታሪክ ሀብታም የሆነችው የጎንደሯ አራዳ ሰፈር ያፈራችው አምሳሉ ጥላሁን ስሙ ካልሆነ በስተቀር መልኩን ትኩር ብሎ ለተመለከተ የውጭ አገር ዜጋ ነው ብሎ ቢጠረጥር አይፈረድበትም፤ በርካቶችም ይሄ ግርታ በውስጣቸው ተፈጥሮ ዜግነቱን እስከመጠራጠር ደርሰዋል እሱም በተደጋጋሚ የዚህ አጋጣሚ ሰለባ መሆኑን ተነግሯል፤ ብዙዎች መልኩን ተመልክተው የተለያዩ አስተያየቶችን ቢሰጡም እሱ ግን እራሱን ምንም የማይወጣለት ልቅም ያለ ቆንጆና መልከ መልካም እንደሆነ በኩራት ይናገራል፤ ከሣምንት በፊት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን ቦርቆ ይገልፃል ተብሎ ሲጠበቅ እንባውን አስቀድሞ ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰው የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን በዚህ ድርጊቱ የብዙዎች መነጋገሪያ ለመሆንም በቅቷል፡፡ እንደ ስፖርት ቤተሰቡ ሁሉ አምሳሉ ያንን የመሰለ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ለምን ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ? የሚል ጥያቄ ያጫረበት የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዴተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የእጅ ስልኩን አንስቶ ወደ አምሳሉ ጥላሁን ስልክ በመደወል “ያን የመሰለ ማራኪ ግብ ማስቆጠር ያስለቅሳል እንዴ?” ብሎ ጠይቆት ያልጠበቀው ልብን የሚነካ አሳዛኝ ምላሽ ይዞ ስልኩን ዘግቷል፡፡
- ማሰታውቂያ -
አምሳሉ ጥላሁን ለጋዜጠኛው ያለቀሰበትን ምክንያት፣ የውጭ ዜጋ ይመስላል ስለመባሉ፣ ስለ ቁንጅናው፣ ስለ ትዳሩ፣ ፋሲል ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሣት ስለመቁረጡና ልዩ ናቸው ስለሚባሉት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የውስጡን ስሜቱን ሳይሰስት አጫውቶታል፤ አብራችሁን ከሆናችሁ ሁሉንም ትሰማላችሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙ ሰው ጠቆር ያለው መልክህን፣ፈርጠም ያለው ተክለ ሰውነትህን ሲመለከቱ የውጪ ሀገር ተጫዋች (ዜጋ) ትመስላቸዋለህ…በርካቶችም “ይሄ ልጅ ዜጋ ነው እንዴ?” ብለው ጠይቀውኛል… አንተሰ እንደዚህ አይነቱ ነገር አጋጥሞህ ያውቃል…?…
አምሳሉ፡- … ኡው…… በጣም ብዙ ጊዜ…(በጣም ሣቅ)…አንዳንደች እንደውም አጠገቤ ሆነው… አማርኛ አይችልም ብለው “…ይሄ ዜጋ ነው መሠለኝ…” ሲሉ እሰማቸውና ምን አላችሁ ስላቸው በጣም ይደነግጣሉ…(በጣም ሣቅ)…እንዳልከው ብዙዎች ዜጋ አድርገው ነው የሚያስቡኝ…ሀገር ቤት ተወውና ውጪ ለጨዋታ ስንሄድም መልኬ ከሌሎች ለየት ስለሚል የክለቡ ፕሮፌሽናል ተጨዋች (ዜጋ) እኔ ነኝ የምመስላቸው…እኔም እንግሊዘኛ ትንሽ ስለምሞካክር…“ዜጋ ነህ?”…ብለው ሲጠይቁኝ ‘Yes’ ብዬ ነው የምመልስላቸው…(ሣቅ)…
ሀትሪክ፡- …ስለመልክህ ካነሣን አይቀር…በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር ብጠይቅህ ትመልስልኛለህ…?…
አምሳሉ፡- …ልመልስልህ አይደለም እንዴ የተደዋወልነው?…የፈለከውን ጠይቀኝ…
ሀትሪክ፡- …አምሣሉ መልከኛ ነው…?…ቆንጆ ነው…?…
አምሳሉ፡- …(በጣም ያላባራ ሣቅ)…እንደዚህ አይነት ጥያቄ ተጠይቄ አላውቅም…(አሁን ሳቅ)…እኔ ራሴን የማየው ምንም እንደማይወጣለት ቅንጆ…መልከኛ ሰው ነው…ደግሞስ ምን ይወጣልኛል…(አሁንም ሣቅ)…በጣም የሚገርምህ ባለቤቴ “…በጣም መልከኛ ነህ፣ቆንጆ ነህ…” ብላ አግብታኛለች…እሷ በቅጡ ካመነችብኝና፣ከወደደችኝ…ስለሌላው አይመለከተኝም…ዋናው እሷ ብቻ ትመንበት፣ትውደደኝና ታረጋግጥበት፣ህይወታችንን እንምራበት እንጂ…ሌላው ነገር ብዙም አያስጨንቀኝም…
ሀትሪክ፡- …በዚህ ዙሪያ ግን ባለቤትህ ምን ትልሃለች…ስትጠራህስ ምን ብላ ነው…?…
አምሳሉ፡- …(አሁንም ያላባራ ሣቅ)…አንተ ሰውዬ ምን አይነት ጥያቄ ነው የምትጠይቀኝ…?…ምን ብላ ትጠራኛለች…?…“የእኔ ፍቅር…!…የእኔ ቆንጆ…!”…ብላ ነዋ…ሌላ ምን ትላለች…?…(በጣም ሣቅ)… ምክንያቱም…ለእሷ ከእኔ በላይ…ለእኔም ከእሷ በላይ ቆንጆ…በምድር ላይ የለም…ደግሞም የልጆቿ አባት መሆኔን አትርሳ…እኔን የእኔ ፍቅር…የእኔ ቆንጆ…ብላ ካልጠራች…ማንን ልትጠራ ነው…?… (ሣቅ)….
ሀትሪክ፡- …እስቲ ስለባለቤትህ አውራኝ…ልጆችስ አፍርታችኋል…?…
አምሳሉ፡- …ባለቤቴ በጣም መልካም ሰው ናት…ለሚዲያ ስለሆነ አይደለም የምልህ…አምላክ መርቆ የሰጠኝ ትልቅ ስጦታዬ ናት…የእሷ ከአጠገቤ መኖር ነው ለዛሬው ማንነቴ ያበቃኝ…ባለቤቴ ስሟ ራሄል. ይባላል…የጎንደር ልጅ ናት…የአምስት አመት ሴት ልጅና ሁለት መንታ ልጆች…ማለትም አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጅን በአጠቃላይ ሶስት ልጆችን ያሳቀፈችኝ…በጣም የምወዳት ሰው ናት…ለኳሱም ጥሩ ፍቅር አላት…ታግዘኛለች፣ታበረታታኛለች፣ትደግፈኛለች…
ሀትሪክ፡- …መንታ ልጆችም አግኝተናል…ነው ያልከኝ…?…
አምሳሉ፡- …አዎን…!…ምነው ደነገጥክ…?…
ሀትሪክ፡- …አይ አልደነገጥኩም…በጣም እድለኛ ነህ…እንደ ድፍረት ካላየኸብኝ…እንደ ቅጣት ምቱ አነጣጥሮ ተኳሽም ነሃ…?…
አምሳሉ፡- …(በጣም ሣቅ)…እንግዲህ ምን አደርጋለሁ…ካልከው በለው…(ሣቅ)…
ሀትሪክ፡- …ባለፈው…ከሐዋሳ ጋር በነበረው ጨዋታ በጣም ልዩና ማራኪ ጎል አስቆጥረህ ትቦርቃለህ፣ ትጨፍራለህ ተብሎ ሲጠበቅ…ከደስታው ይልቅ እንባህ ቀደመ…አለቀስክ…በሠላም ነው…?…
አምሳሉ፡- …በውስጤ የተፈጠረ አንድ ከባድ ሐዘን ነበር…ያ ሐዘን ከውስጤ ገንፍሎ ነው እንባ አውጥቼ ያለቀስኩት…ከዚያ ውጪ ማዘኔን በጣም መከፋቴን አስመልክቶ መልዕክት ለሁሉም ማስተላለፍ እፈልግ ነበር…ያንን መልዕክቴንና ሐዘኔን ደግሞ ከእንባ በስተቀር የሚገልፀው ስለሌለ ነው…ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩት…
ሀትሪክ፡- …ይሄ ያህል ምን ገጥሞህ ነው…?…
አምሳሉ፡- …እኔ የተወለድኩበት ጎንደር ውስጥ አራዳ በሚባል ሰፈር ውስጥ ነው…እዛ አካባቢ ባሉ ወጣቶች መካከል በሠፈር ፀብ ድንጋይ መወራወር ተጀምሮ ደስ ወደማይል ነገር ነው የተገባው… በዚህ ፀብ ወደ አምስትና ስድስት የሚጠጉ ልጆች በማይረባ ነገር በመሞታቸው ውስጤ በሀዘን በጣም ደምቶ ነበር…የሞቱት ልጆች ከእኔ በጣም የሚያንሱ በጣም ህፃናት ነበሩ…የእነሱ አሟሟት ልቤን ነክቶት ስለነበር…ስሜቴንም እንባዬንም መቆጣጠር አልቻልኩም…ከዚህ ውጪ ይሄንን ሀዘኔን ለመግለፅና ድርጊቱን ለማውገዝ፣መልዕክት ለማስተላለፍም ነበር…ሣላስበው ወደዛ ነገር የገባሁት…መንግሥትም የአካባቢው ወጣቶችም አውቀውት ስርዓት እንዲያሲዙልን…የወጣቶች ህይወት ከመቀጠፍ እንዲተርፍ በማሰብ ነው…በእንባ የታጀበ መልዕክቴን ያስተላለፍኩት…አሁን በወሬ ደረጃ ስነግርህ በጣም ቀላል ይመስላል…በውስጤ ግን የከበደ ሀዘንና ቁስል ነው የነበረው…
ሀትሪክ፡- …እንደዚህ አይነት የተረበሸ፣የተጎዳ ስሜት ይዞ ምርጥ ግብ ማስቆጠር አይደለም መጫወት ራሱ አይከብድም…?…
አምሳሉ፡- …በጣም የሚገርምህ ሀዘኑ ውስጤን በጣም ሲበላው ነው የከረመው…በጣም ትናንሽ ምንም የማያውቁ ህፃናትን ህይወት በማይረባ ነገር ማጣት በጣም ይረብሻል…እንዳልከውም በስነ-ልቦና በመጎዳቴ መረጋጋት ሁሉ አቅቶኝ ነበር…ግን ለእነዚህ ልጆች መታሰቢያ የሚሆን አንድ ግብ ማስቆጠርና መልዕክት ማስተላለፍ አለብኝ ብዬ ራሴን እያጠነከርኩ ነበር ወደ ሜዳ ስገባ የነበረው…የሚገርምህ አብሮኝ ለሚያድረው ልጅ ይሄንን ነገር እነግረው ነበር…በሞት ለተነጠቁት ልጆች መታሰቢያ የሚሆን ጎል አግብቼ መልዕክት ማስተላለፍ አለብኝ የሚል ቃል ኪዳን በውስጤ ነበር…ያንን ቃል ኪዳንን ነው የጠበኩት…ምክንያቱም እኔ ከአራዳ አካባቢ ነው የወጣሁት…ይሄን መልዕክት ማስተላለፍ የሚጠበቅብኝ እኔ ነኝ…. ከእኔ ውጪ ሌላ ሰው ማድረግ አለበት ብዬ አላስብም…
ሀትሪክ፡- …አሁን በድጋሚ እንደ ድፍረት አትቁጠርብኝና…ከሐዋሳ ጋር በነበረው ጨዋታ በጣም ልዩና ማራኪ ጎል አስቆጥረሃል…ጎሉን ያስቆጠርከው አስበህበት…ነው ወይስ በአጋጣሚ ነው…?…ብልህ ትቆጣኛለህ…?…
አምሳሉ፡- …የምን ድፍረት…?…የምን ቁጣ አመጣህ…?…የሚገርምህ ነገር ገና ወደ ሜዳ ስገባም… ለእነዚህ ምስኪኖች መታሰቢያ ጎል እንደማስቆጥርና መልዕክት እንደማስተላለፍ ውስጤ በጣም እርግጠኛ ነበር…ኳሱ እግሬ ሲገባም ያን ምኞቴን የምታሳካው ወደ ግብነት የምትቀየረው ኳስም ያቺ እንደነበረች በጣም እርግጠኛ ነበርኩ…ፈጣሪም የልቤን አይቶ ረዳኝ…ከሁሉም አእምሮ የማትጠፋ ምርጥ ጎል አስቆጠርኩ…መልዕክቴንም ሣላስበው በእንባ አጅቤ አስተላለፍኩ…በሆነው ባልሆነው የሚጠፋው የወንድሞቻችን ሞት እንዲያበቃ እፈልጋለሁ…ለዚያ ደግሞ ከእኔ ብዙ ይጠበቃል…አርአያም መሆን ስለነበረብኝ ኃላፊነቴን ለመወጣት ሞክሬያለሁ…
ሀትሪክ፡- …ስለዚህ አስቤበት እንጂ…በአቦ ሰጡኝ አይደለም ያስቆጠርኩት እያልከኝ ነው…?…
አምሳሉ፡- …ነገርኩህ እኮ…የምን አቦሰጡኝ ነው የምታወራው…?…ገና ወደ ሜዳ ስገባም…ኳሷ እግሬ ስትገባም ወደ ግብነት የምትቀየረው ኳስ እሷ እንደነበረች በጣም እርግጠኛ ነበርኩ…ብቻ ምን አለፋህ በዚያ ጨዋታ ግብ እንደማስቆጥር ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የሚያውቅ የተለየ የእርግጠኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር…ያ ስሜቴ ነው ወደ እውነትነት የተለወጠው…ኳሱን ያገባሁበትን ቦታ አይተኸዋል…?… እንዴት ከዚያ ቦታ በአቦሰጡኝ ወይም በአጋጣሚ ግብ ታስቆጥራለህ…?…አስቤበት…ወደ ግብነት እንደሚቀየር…አምኜበት ነው የገባው…
ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ስለጎሉ ምርጥነት አስተያየታቸውን ሲሰጡ አያለሁ..ለእኔም ከውድድሩ ምርጥ ግቦች ቀዳሚውን ቦታ የምሰጣት ናት…አምሣሉስ እስከዛሬ ካስቆጠራቸው ግቦች የተለየች ልዩ ጎሉ አድርጎ ይቆጥራታል…?…
አምሳሉ፡- …እኔ ሁሌም የእስከዛሬው የጨዋታ ዘመኔ በምርጥ ጎልነት የማነሣት ታስታውስ እንደሆነ አላውቅም ደደቢት ላይ ያስቆጠርኳትን ጎል ነው…ጨዋታው ከእግር ኳስነት በዘለለ ፖለቲካዊ ስሜት ነበረው..በዛ ላይ ብዙ ደስ የማይሉ ስድቦች ይወርዱብን ነበር…በዚህ የተነሣ በጣም ጫና የበዛበት ጨዋታ ነበር…በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ እያለን በቅጣት ምት ያስቆጠርኳት ጎል ለእኔ የእስከዛሬው ምርጡ ጎሌ ብትሆንም…ሐዋሳ ላይ ከርቀት ላስቆጠርኳት ኳስም በጣም የተለየ ቦታ አለኝ…ምርጥ ጎል በማስቆጠሬና በሞት ለተነጠቁት ወንድሞቼ መልዕክት ያስተላለፍኩባት ጎል በመሆንዋ ደደቢት ላይ ካስቆርኳት ምርጥ ጎሌ በመቀጠል በተለየ መንገድ የማስታውሳት ይሆናል…
ሀትሪክ፡- …ፋሲል ከነማ የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በ29 ነጥብ እየመራ ይገኛል…ይህ መሪነቱ ፋሲል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የሚያነሣበት ቀን መቅረቡን ይጠቁማል…?…
አምሳሉ፡- …በጣም…!…ፋሲል የዋንጫ ቡድን ሆኖ የተገነባ ነው…ዋንጫውም በትክክል የሚገባው ነው…ታስታውስ እንደሆነ የዛሬ ሁለት አመትም እስከመጨረሻው ተናንቆ ነው ዋንጫውን ያጣው… አምና በኮቪድ ምክንያት ሊጉ ባይቋረጥ ኖሮ ወደ ዋንጫው እየተንደረደርን ነበር…ዘንድሮም ሊጉን በብቃት እየመራን ነው…ይሄንን አስጠብቀን መጓዝ ከቻልን ዋንጫውን ከማንሣት የሚያግደን ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም….
ሀትሪክ፡- …ይሄ የምትለው ነገር በአንተ የተጫዋችነት ዘመን በእርግጠኝነት ተሳክቶ የሚታይ ይመስልሃል…?…
አምሳሉ፡- …በእርግጠኝነት ይታያል…!…ያውም ሩቅ አይደለም…ዘንድሮ ዋንጫውን እንደምንወስድ የምናገረው እርግጠኝነት በተሞለበት ስሜት ነው…ፋሲል ዋንጫ ማንሣት አለበት ከተባለ አሁን ነው… ያ ደግሞ በእርግጠኝነት ዘንድሮ በእኛ የተጨዋችነት ዘመን ተሳክቶ አዲስ ታሪክ ለራሳችንም ለክለባችንም እናፅፋለን…
ሀትሪክ፡- …የፋሲል ከነማ ደጋፊ ፍፁም የተለየ ደጋፊ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው…ደጋፊውን በአንደበትህ ግለፅልኝ ብለህ እንዴት ነው የምትገልፀው…?…
አምሳሉ፡- …የጎንደር ወይም የፋሲል ደጋፊ ኳስን የሚወድ ነው…ኳስ ድቡልበል መሆንዋን ብቻ ሣይሆን ረቂቅ ምስጢርዋንም የሚያውቅ፣ክለቡን ከልቡ የሚወድ፣ለክለቡ ከልቡ የሚጨነቅ ደጋፊ ነው… ለእኛ ለተጨዋቾች ከእኛ በላይ የሚያስብ ራሱን ለክለቡ አሣልፎ የሚሰጥ እውነተኛ ደጋፊ ነው…የእንደዚህ አይነት ምርጥ ደጋፊ ባለቤት በመሆናችን በጣም እድለኞች ነኝ…ይሄ ደጋፊ ዋንጫ በጣም ይፈልጋል…ዋንጫ የተራበውን ደጋፊያችንን ለማስደሰት ምንም የምንሰስተው ነገር የለም… ሁሉም ተጨዋች ደጋፊውን ለማስደሰት ዘንድሮ ቆርጧል…የዋንጫ ባለቤት ማድረግ አለብን ብለን ሁላችንም ተነሳስተናል…ደግሞም ደጋፊው ዋንጫ ይገባዋል…ዋንጫ ማግኘት ያንሰዋል እንጂ የሚበዛበት አይደለም…ምክንያቱም የፋሲል ደጋፊ ከዚያ በላይ ይገባዋልና…የእኔ የጨዋታ ዘመኔ ሙሉ ሆነ የምለው ዋንጫውን አንስተን ደጋፊው በደስታ ሲሰክር በአይኔ ሣይ ብቻ ነው…እኔ በህይወት እስከአለሁ ከቡድኑ፣ከደጋፊውና ከአመራሩ ጋር አብሬ ዋንጫ ሳላነሳ መለየት አልፈልግም…አምላኬንም የምለምነው ይሄንን እንደያሳየኝ ነው…
ሀትሪክ፡- …ዘንድሮ ምርጥ አቋም አሣይተኻል…ምርጥ ምርጥ ጎሎችንም አስቆጥረሃል…ለፋሲል ውጤታማነትም የአንተ ሚና ተጠቃሽ ነው፤የዚህ ሁሉ ስኬት ባለቤት መሆንህ ግን ለብ/ቡድን ተመርጠህ እንድትቆይ ሣይሆን ተመርጠህ እንደትባረር ነው ያደርገህ…በዚህ ላይ ምን ትላለህ…?…
አምሳሉ፡- …በነገራችን ላይ እኔም ቤተሰቤም ለውበቱ የተለየ አድናቆትና ክብር አለን…ውበቱን በጣም የምናደንቀው አሠልጣኝም ነው…ውበቱ ማለት የጎንደርን እግር ኳስ አሳድጎትና አነቃቅቶት የሄደ ሰው ነው…በእኔም በባለቤቴና በልጆቼም የተለየ ቦታ ያለው ሰው ነው…ከእሱ ጋር ምንም አይነት ችግር የለብኝም…በውበቱና በእኛ መካከል ስላለው ነገር ለአንተ ማስረዳት አይጠበቅብንም….
ሀትሪክ፡- ..ግን እኮ በዚህ ደረጃ በገለፅከው…አንተም ቤተሰብህም የተለየ ቦታ በምትሰጡት ውበቱ ለብ/ቡድን ጠርቶህ መመለሱ ይረብሽሃል…ይሄ ነገር መሆኑ…ለአሱ ያለህን ፍቅር ወይም አክብሮት እንዲቀንስስ ያደርገዋል…?…
አምሳሉ፡- …(ሳቅ)…ምንም የረብሸኝ ነገር የለም…ለብ/ቡድን ተጠርቼ መመለሴ ለእሱ ያለኝን አክብሮትና አድናቆትም አይቀንስውም…እኔ ውበቱን የማያው ልክ እንደ አባቴ ነው…እኔን ተወኝ…ልጄ እንኳን ስለውበቱ ትጠይቀኛለች…ጥሩ ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው ያለን…ይሄ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ አይረብሸኝም…አክብሮቴም አይቀንስም…
ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላስ ዳግም ተጠርተህ የብ/ቡድኑን ማልያ ለብሰህ ሀገርህን የምታገለግልበት እድልን የምታገኝ ይመስልሃል…?…
አምሳሉ፡- …አትጠራጠር…!…ሀገሬን የማገልገል ትልቅ ህልም ነው ያለኝ…ለዚያ የሚያበቃ ብዙ ነገር አለኝ ብዬም ነው የማስበው…እምነቱ ተሰጥቶኝ ከገባሁ ከፈጣሪ ጋር ለሀገሬ ብዙ ነገር ያውም በቅርቡ እሠራለሁ ብዬ ነው የማስበው…
ሀትሪክ፡- …አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ጨመረልኝ የምትለው ነገር አለ…?…
አምሳሉ፡- …ስዩም ውስጤ ምንም አይነት ነገር እንዳይኖር አቅሜን አውጥቼ እንድጫወት አድርጎኛል… ስዩምን እኔ የምገልፀው እንደ አባቴ ነው…የሚያወራህ፣የሚመክርህ ልክ የአባት ያህል ነው…ስዩም የዋህ ነው…ለእኔም ለክለቡም ብዙ ነገር ጨምሯል…ስዩም ሁሉንም ተጨዋች በአንድ አይን የሚያይ አሰልጣኝ ነው…እኔ እንደውም አሁን የመጣው ውጤት መጣ የምለው በስዩም ነው…
ሀትሪክ፡- …ግን እኮ ከተወሰኑ ጨዋታዎች በፊት በተለይ ሊጉ አዲስ አበባ ላይ ሲካሄድ “ስዩም ይባረር” የሚል ነገር ይደመጥ ነበር…?…
አምሳሉ፡- …ተብሏል…!…በወቅቱ የፋሲል አስፈሪነት አብሮን አልነበረም…በዛን ወቅት የፋሲል አስፈሪነት ይመለሣል ብዬ አስተያየት ሁሉ ሰጥቼ ነበር…በዛን ወቅት ቅሬታዎች ሁላችንም ላይ ነበሩ… አሁን ግን ቀደም ብዬ እንዳልኩት የፋሲል አስፈሪነት ተመልሷል…በጣም ከምነግርህ በላይ ተመልሷል…አስፈሪነቱ በመመለሱ በፊት በመቆጨት ሲነሱ የነበሩ ነገሮች አሁን አይሰሙም…
ሀትሪክ፡- …በአንተ እምነት የፋሲል ዋነኛ የዋንጫ ተቀናቃኝ ማነው ትላለህ…?…
አምሳሉ፡- ..ለፋሲል ሁሉም ተቀናቃኝ ነው…ከአዳማ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ለእኛ የዋንጫ ያህል ነው…ከቅዱስ ጊዮርጊስም ከኢት.ቡና ጋርም የምናደርገው ለእኛ የዋንጫ ያህልና ከባድ ነው…ሁሉም ለእኛ የዋንጫ ተቀናቃኞቻችን ናቸው አስቀደመን እስካላረጋገጥን ድረስ…
ሀትሪክ፡- …በልጅነትህ ማንን መሆን እየተመኘህ እያደነክ ነው ያደከው…?…
አምሳሉ፡- …እኔ ጎንደር ነው ተወልጄ ያደኩት…ብዙዎችን በቅርበት የማየት እድል አላገኘሁም…ያም ቢሆን ግን አሁን የክለባችን ምክትል አሰልጣኝ የሆነው ሙሉቀን አባይ ኢንጂኒየር ይባላል እሱን በጣም እያደነኩና እንደ እሱ ለመሆን እየተመኘሁ ነው ያደኩት…ሙሉቀን ባህሪ ከችሎታ ጋር ያለስስት የተሰጠው ሰው ነው…
ሀትሪክ፡- …አንተ በምትጫወትበት ቦታ ምርጡን ተጨዋች ጥራ ብልህ ማንን ትጠራለህ…?…
አምሳሉ፡- …አበባው ቡታቆን…አበባው በጣም ምርጥ ተጨዋች ነው…
ሀትሪክ፡- …በቦታህ በጣም የሚፈትንህ የሚያስችግርህ ተጨዋችስ…?…
አምሳሉ፡- …የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አማኑኤል ገ/ሚካኤልና አቤል ያለው እንዲሁም የኢት.ቡናው አቡበከር ናስር ለእኔ በጣም የተሻሉ ተጨዋቾች ናቸው….በጣም አከብራቸዋለሁ… በጣምም እጠነቀቃቸዋለሁ… እነዚህ ተጨዋች እንደ ክለብ ብቻ ሣይሆን እንደ ብ/ቡድንም በጣም ትልቅ ቦታ ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው…
ሀትሪክ፡- …ከየትኛ ቡድን ጋር ስትጫወት የተለየ ስሜት ይሰማሃል…?…
አምሳሉ፡- …ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር…!…ኢትዮጵያ ውስጥ ለእኔ ትልቁ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው… ከጊዮርጊስ ጋር መጫወት ትልቅ ኃላፊነት እንዲሰማህ ያደርጋል…ከ14 በላይ ዋንጫ ያነሣ መሆኑም ክብደቱን ይጠቁምሃል…
ሀትሪክ፡- …በጨዋታ ዘመንህ በፀፀት ወይም በቁጭት የምታነሣው ጨዋታ አለ…?…
አምሳሉ፡- …በዚህ ደረጃ የለም…
ሀትሪክ፡- …ሀውስኮድና ዳሽን ከፋሲል በፊት የነበርክባቸው ክለቦች ናቸው…ስለነበርህ ቆይታና ስለ ዳሽን መፍረስ ምን ትላለህ…?….
አምሣሉ፡- …በሁለቱም ክለቦች በጣም ጥሩ የሚባል ጊዜ ነው የነበረኝ…ዳሽን መፍረሱ አያሰገርምም…ምክንያቱም ዳሽን የገንዘብ አቅም እንጂ የሚቆረቆርለት ሰው የሌለው ክለብ ነበር…
ሀትሪክ፡- …ራስህን ግለፅልኝ ብልህ…አምሳሉ ምን አይነት ሰው ነው ትለኛለህ…?…
አምሣሉ፡- …ሌሎች ሰዎች ቢናገሩ ደስ ይለኛል…ለራስህ አደላህ ካላልከኝ…አምሣሉ ማለት ፊት ለፊት መናገር የሚወድ፣ውስጡ ምንም የሚያስቀረው የሌለ፣መልካም የሚያስብ ሰው ነው… ውስጤ ምንም ስለሌለና…ፊት ለፊት በመናገሬ ይመስለኛል እግዚያአብሔር እየረዳኝ ያለው…
ሀትሪክ፡- …ቀጣይ ህልምህ…?
አምሣሉ፡- …ፈጣሪ ካለ ወጥቼ መጫወት…የራሱንም የሀገሬንም ስም የማስጠራት ትልቅ ህልም አለኝ…ፈጣሪ ከረዳኝና ካሳካልኝ ህልሜ እሱ ነው…ሌላው ህልሜ ፋሲል የሊጉ ሻምፒዮን ሆኖ ይሄንን ምርጥ ደጋፊ ማስደሰት እፈልጋለሁ…
ሀትሪክ፡- …ገንዘብ ላይ ቆጥቆጣ፣አባካኝ ወይስ በፕሮግራም የሚጠቀም…?…አምሳሉ የቱ ጋ ነው…?…
አምሣሉ፡- …ኧረ የምን ገንዘብ…?…(በጣም ሳቅ)…እኔ ተወልጄ ያደኩት ጎንደር ውሰጥ አራዳ የሚል አካባቢ ነው…አራዳ ሰፈር እንደ ስሙ አራዶች ያሉበት…ብዙ ነገር የሚሠራበት የተለየ ሠፈር ነው…በአራዳ ሰፈር ስትኖር ገንዘብ ኖረህ አልኖረህ…ሁሉም እኩል ተደስቶ የሚኖርበት ሁሉም አንድ የሚሆንበት ሠፈር ነው…ምክንያቱም አንተ ገንዘብ ባይኖርህና እኔ ገንዘብ ካለኝ ከእኔ መውሰድ ስለምትችል ገንዘብ የሌለው ያህል አይሰማህም…በአራዳ ገንዘብ ሳይሆን ትልቅ ዋጋ ያለው ሰው በመሆኑ ገንዘብ ስለማትረፍ ሳይሆን…ሰው ስለማትረፍ የምታስብበት አካባቢ ነው…በአራዳ ሰፈር አካባቢ ያለኝን ሶሻል ላይፌን በጣም የምወደውም ለዚህ ነው…
ሀትሪክ፡- …በሰው ላይ ባላየው የምትለው…?
አምሣሉ፡- …ቀናተኛ ሰው አይመቸኝም…ወሬኛ ሰውም እንደዛው…
ሀትሪክ፡- …የልብ ጓደኛዬ የምትለው…?
አምሣሉ፡- …በጣም የምወደውና የማከብረው ኤርሚያስ ኃይሉ…
ሀትሪክ፡- …ፕሪሚየር ሊጉ በዲኤስ ቲቪ መተላለፉን አስመልክቶ ምን ትላለህ…?…
አምሣሉ፡- …ዲ.ኤስ.ቲቪ ብዙ ጠቀሚ ነገሮችን ይዞልን መጥቷል…በመላው አለም የምንታይበትን እድል ፈጥሮልናል…ከዚያም በላይ ደካማም ሆነ ጥሩ ጎናችንን እንድንናይ ረድቶናል…ከዚህ በፊት ብዙ ጥሩ ጥሩ ጎሎችን አስቆጥሬያለሁ…እንደ አሁኑ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ግን አልገባም…በጎሌ ዙሪያ ብዙ ሰው አስተያየት የሰጠኝም በዲኤስቲቪ በመታየቱ ነው…ሌላው የተሻለ የውጪ እድል እንድናገኝ ይረዳናል…ሌላውን ተወውና ዲኤስቲቪ ለወጌሾችና የቡድን መሪዎችም ጠቅሟል…ለዛም ነው ሸንቀጥ ብለው ለመታየት ሲሉ Sit up እየሰሩ ያሉት እኮ በዲ.ኤስ.ቲቪ ለመታየት ሲሉ ነው…በአጠቃላይ ግን ዲኤስቲቪ ለእግር ኳሱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡