“የባለሙያ ሃሳብ ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች ሲረገጥ ማየት በጣም ያማል”
“ለአብርሃም ሳይሆን ለሕጉ ነው የወገነው፣ ውበቱ እሳቱን ገለባ እንዲያደርግለት እመኛለሁ”
አቶ ሰለሞን አባተ
ፕሬዚዳንቱ የቴክኒክ ኮሚቴው ያቀረበውን ምክረ ሃሣብ “ከቴክኒካል ይልቅ አስተዳደራዊ ነው” ብለው ባለ 9 ነጥብ ምክረ ሃሳባቸውን አቅም ያሳጣ መግለጫ መስጠታቸው ክፉኛ አበሳጭቶታል፤ “የባለሙያ ሃሣብ እንዴት ባለሙያ ባልሆነ ሰው ይነጠቃል” በማለት የሚሞግተው የቀድሞው የአዳማ አሠልጣኝና የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አባል የሆነው በኢትዮጵያ ቡናው የወርቃማ ታሪክ ባለቤት የሆነው አሰልጣኝ ስዩም አባተ ታናሽ ወንድም የሆነው ሰለሞን አባተ ፌዴሬሽኑ በሠራው ስራና ፕሬዚዳንቱ በሰጡት መግለጫ አለመደሰቱን በተለይ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡ “የቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ የተከበሩና ከፍተኛ እውቀት ያላቸው ሙያተኞች የተሰባሰቡበት ነው የሙያተኞች ድምፅ ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች ሲነጠቅ ማየት በጣም ያማል” ይላል፡፡አሰልጣኝ ውበቱ እሳት ላይ ነው የተጣደው መልካም እድል እንዲገጥመው ምኞቴም ነው፤ ነገር ግን ብዙ ፈተና ይጠብቀዋል 7 ወር ያለ ልምምድና ያለ ጨዋታ የተቀመጡ ዳሌ ያወጡ የወፈሩ ተጨዋቾችን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ አሰልጥኖ ነው ለፈተና የሚቀርበው በዚህም በጣም አዝኜለታለሁ” በማለት ይናገራል የቴክኒክ ኮሚቴው አባል ሰለሞን አባተ፡፡
- ማሰታውቂያ -
የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክሲኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር ዋና ፀሐፊና የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴን ለበርካታ አመታት በማገልገል ላይ ያለው ደፋሩ፣ ያመነበትን ፊት ለፊት የሚናገረውና ማስመሰል የሚያውቀውን አሰልጣኝ ሰለሞን አባተን በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አነጋግሮት የተለመደውን ድፍረት ያለው ምላሽ ሰጥቶት ከዚህ በታኛ ባለው መልኩ አቅርበነዋል፡፡
ሀትሪክ፡- በመጀመሪያ ለቃለ ምልልሱ ስለተባበርከኝ በጣም አመሰግናለሁ…
አቶ ሰለሞን፡- …እኔም መድረኩን ስለሰጣችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክር ሃሣብ ጠይቋችሁ ባለ 9 ነጥብ ሃሳባችሁን አቅርባችኋል፤ያቀረብነው ምክረ ሃሳብ ትክክልና ተገቢ ነው ትላለህ…?
አቶ ሰለሞን፡- …በጣም ትክክልና ተገቢ ሁላችንም መክረንበት…አሁን ከምንገኝበትና…ከውድድሩ መቃረብ አንፃር…ተገቢ መፍትሔ ይሆናል ብለን ያመንበትን ባለ 9 ነጥብ ግብረ መልስ ነው የሰጠነው….፡፡
ሀትሪክ፡- …አንተ እንደዚህ በኩራት የምትናገርለትን ባለ 9 ነጥብ ምክረ ሃሳብን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳን አቶ ኢሳያስ ጅራ ለሚዲያ ሰዎች በሰጡት መግለጫ ላይ ከቴክኒክ ይልቅ አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ብለው ማጣጣላቸው አንተ ከምትለው ጋር አይጋጭም…?
አቶ ሰለሞን፡- …በመጀመሪያ ደረጃ አንድ እንድታውቅልኝ የምፈልገው ነገር…እኔ እዚህ ጋር የምናገረው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን ሳይሆን ራሴን ወክዬ መሆኑን ነው፤ፕሬዝዳንቱ “አስተዳደራዊ ነው” ብሎ የተናገረው ነገር ለእኔ በጣም የሚያሳዝንና የሚሳፍር ነው፤የእኛን ስሜት መጉዳት ብቻ ሳይሆን ሰውም በእኛ ላይ ያለውን አመለካከት የተዛባ የሚያደርግ አስተያየት ነው፤ከቴክኒክ ይልቅ አስተዳደራዊ ነው ማለት ምን ማለት ነው…?…የትኛውስ ነው አስተዳደራዊ ማለት…?…ደግነቱ የተናገረውንና ያጣጣለን ስለ ቴክኒክ የሚያውቅ ሰው ባለመሆኑ ብዙም አይሰማንም…ቦታም አንሰጠውም…፡፡
ሀትሪክ፡- …ለምሣሌ የቴክኒክ ኮሚቴው ካቀረባችው ባለ 9 ነጥብ ምክረ ሃሳብ ውስጥ…የኮቪድ ወረርሽኝ ሲመጣ በመቋረጡ…ከተጨዋቾች ጋር
በጣም ስለሚቀራረብ…ስለሚግባባ የሚሉት ይገኙበታል…እነዚህን ቴክኒካል ናቸው ከማለት ይልቅ አስተዳደራዊ የሚለው ቃል አይገልፃቸውም…?
አቶ ሰለሞን፡- …አትሳሳትም…!…የኮቪድ ወረርሽኝን ያነሳነው በምክንያት ነው…ምን ለማለት ፈልገን ነው…ብ/ቡድኑ ከትዲቯዋርን እስካሸነፈበት ጨዋታ ድረስ በጥሩ መሻሻልና በጥሩ አቋም ላይ ነበር፤ወደ መጨረሻ ላይ ጥሩ ብ/ቡድን ተስርቶ ነበር…ወረርሽኙ ሲከሰት ጨዋታዎች ተቋረጡ…በመቋረጡ ምክንያት እነዛ ጥሩ የነበሩት ልጆች ተበተኑ…ከዚህ አንፃር…ከጊዜው ማጠርና ረዥም ጊዜ ያለ ውድድርና ያለ ልምምድ በመቀመጣቸው…ቶሎ ወደ መስመር ለመግባት አብሮአቸው የሰራው አብርሃም ቢሆን የተሻለ ይሆናል የሚል ሃሳብ ነው ያስቀመጥነው፤ አዲስ አሰልጣኝ መጥቶ በዚህ አጭር ጊዜ…በራሱ ፍልስፍና አዳዲስ ተጨዋቾችን መርጦ መቀጠሉ ሊያስቸግር ይችላል ከሚል ስጋት በመነሣት ለቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች አብርሃም ይዞት ቢቀጥል ይመረጣል…ከ4ቱ ጨዋታዎች በኃላ ብትፈልጉም ከኒጀሩ የመጀመሪያ ጨዋታ በኃላ አባሩት የሚል ምክር ሃሣብ ነው ያቀረብነው፤ ሌላው ከተጨዋቾች ጋር ይቀራረባል… ይግባባል…የሚለው የምክረ ሃሳባችንን አንደኛውን ነጥብ ፕሬዝዳንቱ መረዳት አቅቷቸው እንጂ…ይሄም ሃሣብ በውስጡ ቴክኒካል ነገር አለው…
ሀትሪክ፡- …እንዴት…?…አብራራው እስቲ…?
አቶ ሰለሞን፡- አብርሃም እያንዳንዱን ተጨዋች በነበራቸው ረዥም ወይም የሁለት ዓመት ቆይታ በኮቪድ ምክንያት እስከተበተኑበት ጊዜ ድረስ ያለውን አቅማቸውን ጠንቅቆ ያውቃቸዋል…የእያንዳንዱን ተጨዋች ባህሪ፣ስብዕናቸውን፣ቴክኒካል ክህሎታቸውን በሚገባ ያውቃል…ማን ምን አለው…?…ማን ምን ይጎለዋል…?…ለሚለው የራሱ ዳታ አለው…ከዚህ አንፃር መጠነኛ ጥገና አድርጎ…በጎደላቸው ሞልቶ…ያላቸውን ይበልጥ አሻሽሎ…በቅርብ ላለብን የኒጀር ጨዋታ ለመድረስ የእሱ መቀጠል ይጠቅማል ነው ያልነው…ይሄ ታዲያ ቴክኒካል እይታ አይደለም…?…ፕሬዚዳንቱ ይሄን የመረዳት አቅም በማጣቱ ነው በሚዲያ ፊት የተሳሳተው…።
ሀትሪክ፡- …በአፍሪካ ጠንካራ የሆነውን የኮትዲቯር ብ/ቡድንን ሲያሸንፍ ተሸልማል የሚለውንስ ቴክኒካል ነው ብሎ መውሰድ ይችላል…?
አቶ ሰለሞን፡- …ኮትዲቯርን ካሸነፈ በኋላ…“ጎሽ እሰየው” ብለው በአደባባይ ሸልመዋቸዋል፤ ይሄ የሚያሳይህ አሰልጣኙም ብ/ቡድኑም ጥሩ ነው ብለው እውቅና እንደሰጡ ነው፤በዚያን ሰዓት በቡድኑ ችግር ዙሪያ አንድም ቃል አልተነፈሱም…ዛሬ…ሊበሏት ያስቧትን አሞራ…እንደሚባለው ፕሬዚዳንቱ ልክ ትልቅ ጥናት ያቀረበ ይመስል…በፊፋ 150ኛ…ምናምን…እያለ ብዙም እውቀትና ምርምር የማይጠይቅ ቁጥር ይጠራል…ታዲያ እውነታው ይሄ ከሆነ መጀመሪያ ለምን ሸለመ…?…ያኔ የፊፋ የደረጀ ሰንጠረዥ ላይ መውረዳችን ወይም አለመሻሻላችንንስ ማየት ለምን አልፈለገም…?…በፊፋ በካፍ ወርደናል…ወጥተናል…እያሉ ማውራት የፈለጉበት ምክንያት ግልፅ ነው “እኛ እዚህ እያለን አብርሃም አይቀመጥም” የሚለውን ፉከራቸውን ለመፈፀም ነው፡፡ ኮሌታህ ተጣሟል…እግርህ ተንሻፏል…ብለህ…አቃቂር አውጥተህ…ምክንያት ፈልገህ ማባረር…ለእኔ ፍትሀዊ አይደለም፤መሰራትም ካለብን ግለሰብን ሣይሆን ሀገርን ማዕከል አድርገን ነው፤ፕሬዝዳንቱ ትናንት እኮ ሁሉንም ነገር ለአብርሃም ሲሉ ነበር…ሌላውን ተወው ከሕግና ከደንብ ውጪ የብ/ቡድኑ አሰልጣኝን ተጠሪነት ለራሣቸው አድርገው ነበር…ይሄ በጣም የሚያሳፍር ሥራ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …የሚያሳፍር ሥራ ስትል… ?
አቶ ሰለሞን፡- …የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የብ/ቡድኑ አሰልጣኝ ተጠሪነትን ለራሣቸው አድርገው ነበር…ይሄ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተደርጎም ታስቦም አያውቅም…በዚህ ብቻ ሳያበቁ ያኔ ፍቅር በነበሩት ሰዓት እኮ በሀገሪቱ ሰው የጠፋ ይመስል ዋናውን ብ/ቡድን፣የኦሎምፒክንና የቻን ብ/ቡድኑን አንስተው ሰጥተውት ነበር…እንዴት ሁሉንም ነገር ጠቅልለህ ለአንድ ሰው ትሰጣለህ? ይህ የፕሬዚዳንቱ የአስተዳደር ስህተት ብቻ ሣይሆን በሀገሪቱ ያሉትን ሌሎች ሙያተኞች የመስራት ነፃነትን መጋፋት…ስሜታቸውንም መጉዳት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት አሠራር ገንዘብ በሌለበት ሰዓት እንኳን ተደርጎ አያውቅም…ኃላፊነቱን መወጣት ለሚችሉ አሰልጣኞች ነው በየደረጃቸውና ብቃታቸው የሚሰጠው፡፡ በዚህ ደረጃ የሀገሪቱን ብ/ቡድኖች ሲሰጡ የነበሩት ወገኖች ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነው “አብርሃም ከዚህ ቦታ ካልጠፋ ሞተን እንገኛለን” አይነት ውሣኔ የሚወስኑት? መልሱን ለእነሱ እተወዋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ከላይ በምላሽህ ስታነሣ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ተጠሪነት ለቴክኒክ ኮሚቴው መሆን ሲገባው ለፕሬዚዳንቱ ኢሳያስ ጅራ እንደሆነ ተናግረሃል…ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ…?
አቶ ሰለሞን፡- በወቅቱ እኛንም ግራ አጋብቶን ነበር…በየትኛውም የፌዴሬሽኑ የስልጣን ዘመን የብ/ቡድኑ አሰልጣኝ ተጠሪነቱ ለቴክኒክ ኮሚቴ እንጂ ለፕሬዚዳንቱ ሆኖ አያውቅም፤አቶ ኢሳያስ ጅራ ግን ይሄን አድርጎታል፤አብርሃም መብራቱ ወደ ብ/ቡድኑ እንደመጣ ተጠሪነቱ ለቴክኒክ ኮሚቴው አልነበረም…እቅድም አቅርቦ አያውቅም…ተገምግሞም አያውቅም…
ሀትሪክ፡- …ይሄ ሁሉ ሲሆን እናንተ ለምን ዝም አላችሁ…?…በወቅቱስ ለምን አልተቃወማችሁም…?
አቶ ሰለሞን፡- …ዝም አላልንም…ኧረ ይሄ ነገር አካሄዱ ልክ አይደለም ስንል…በደብዳቤ ስንጠይቅ የሚሰማን አልነበረም…በህጋዊ መንገድ ከመጠየቅ በላይ በጉልበት አንነጥቃቸውም…በኋላ ላይ ሚዲያው የቴክኒክ ኮሚቴው ምን እየሠራ ነው…?…አሰልጣኙ እቅድ ተጠይቆ አያውቅም…ተገምግሞም አያውቅም…እያሉ ሲያወሩና ሲዘገብ…እኛም እቅድ ቀርቦልን አያውቅም…የማናውቀውን ቡድንስ እንዴት ነው የምንገመግመው? ስንል መጨረሻ ላይ ከሌሴቶ በኋላ ነው የአሠልጣኙ ተጠሪነት ወደ ቴክኒክ ኮሚቴው የተመለሰው…እዚህ ጋር አንድነገር ባነሳ ደስ ይለኛል…
ሀትሪክ፡- …ምን…?
አቶ ሰለሞን፡- …የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የብ/ቡድኑ አሰልጣኝ ተጠሪነቱ ለሳቸው እንዲሆን ያደረጉት በየትኛው ቴክኒካል እውቀታቸው እቅዱን
ሊገመግሙ አስበው ነው…?…እንዴትስ ነው ቴክኒካል አናሊሲስ የሚሰጡት…?…እሳቸው የአስተዳደር ሰው አይደሉም
እንዴ…?…ያለሙያቸውስ ለምን ይሄን ማድረግ አሰቡ…?…በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው የተሰራው…ያኔ ተጠሪነቱንም…የዋናው፣
የኦሎምፒክና የቻን ብ/ቡድንን ጠቅልሎ እንዲይዝ ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ…ለምን ዛሬ የምንን ስም ያነሳ…ምን ይሁን…ነው
የሚባለው…አይነት አቋምን ለምን ያዙ…?…ከእሳቸው ውጪ መልሱን የሚያውቅ የለም…።
ሀትሪክ፡- የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብርሃም መብራቱ ይቀጥል በሚል ያቀረባችሁትን አስመልክቶ እንደገና ምክረ ሃሳባችሁን እንድታዩትና ሌሎች አማራጮችንም አካታችሁ እንድታቀርቡ ብለው እናንተ ግን ከአብርሃም ውጪ ማለታችሁ ምን ማለት ነው…?
አቶ ሰለሞን፡-ይሄ የምትለው ነገር ውሸት ነው፣ ፕሬዚዳንቱ በፍፁም እንዲህ አይነት ሃሣብ አላቀረበልንም፤ እኛ ትላልቅ ሰዎች ነን መወሻሸት የለብንም፤ በቃልም በፅሁፍም የደረሰን ነገር የለም መጀመሪያ የተጠየቅነው ምክረ ሃሣብ እንጂ አማራጭ አቅረቡ ስላልተባልን ከተባልነው ውጪ አልሠራንም” አማራጭ ብንባል ኖሮ ለቦታው ይመጥናሉ የምንላቸውን አንድ ሁለት ብለን ለማቅረብ አንቸገርም፤ ግን ምክረ ሃሣብ ነው የተጠየቅነው፤ በተጠየቅነው መሠረት መልሰናል፡፡
ሀትሪክ፡- የቴክኒክ ኮሚቴው “ኢንስትራክተር አብርሃም ይቀጥል” ብሎ የሙጥኝ ማለቱን ብዙዎች ነገሩ ምንድነው? ብለው ጥያቄ የሚያነሱ ጉዳዩን ከሌላ ጋር የሚያያይዙ አሉ ለእነሱ መልስህ ምንድነው?
አቶ ሰለሞን፡- ከምን ጋር ነው የሚያያይዙት? እኛ ለአብርሃም ሣይሆን ለህጉና ለአሠራሩ ነው የወገነው፤ ካለው ጊዜ አንፃር የተሻለ ነው ብለን ያመንበትን ሃሣብ ነው ያስቀመጥነው እንጂ ከአብርሃም ጋር የተለየ ግንኙነት ወይም ቅርበት የለንም፤ ግን ኃላፊነታችን በአግባቡ ከመወጣት አንፃር ነው ምክረ ሃሣቡን ያቀረብነው፡፡ እንደውም አንድ ነገር ልንገርህ…
ሀትሪክ፡- ምንድነው የምትነግረኝ፤…?
አቶ ሰለሞን፡- አንድ እውነት ልንገርህ ለቅርበት ለቅርበትማ ለእኔ በግሌ ከአብርሃም ይልቅ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጣም ይቀርበኛል፤ ውበቱን አዳማ እያለሁ ያሰለጠንኩት በጣም የምቀርበው የልጄ ያህል የማየው ሰው ነው፤ በቅርበት ቢሆንም አብርሃም አይቀጥል ነበር ማለት ያለብኝ፤ ጉዳዩ የቅርበት ሣይሆን ኃላፊነትን ሙያን በአግባቡ ከመወጣት ነው ውሣኔው የተላለፈው፡፡
ሀትሪክ፡- ኢንስትራክተር አብርሃም መሰናበት ካለበት እንኳን ለሰጠው አገልግሎት “ምስጋና ቀርቦለት በክብር መሸኘት እንጂ ክብሩን ነክተው ማባረር አልነበረባቸውም የሚሉ አሉ ሃሣቡ ይስማማሃል?
አቶ ሰለሞን፡- እንደ እኛ እምነት ከነበረው ሁኔታ መቀጠል ነው የነበረበት፤ ይሄ የማይሆን እንኳን ቢሆን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በሁለት አመት የስልጠና ቆይታው ለሠራው ጥሩም ያልሆነ ነገር ካለም “ለነበረህ ቆይታና ሀገርህን በማገልገልህ እናመሰግናለን” ተብሎ በክብር መሸኘት ነበረበት ይሄ አሰልጣኝ እኮ ኳታር በስራ ላይ እያለ “ና ሀገርህ ትፈልግሃለች” ሲባል ሣያመነታ ነው የመጣው፡፡ ሀገሬን ልርዳ ብሎ የመጣ ሰውን የካፍ እና የፊፋ ደረጃ እያልክ ጎል እየቆጠርክ በአደባባይ እያሳነስከው አይደለም ማባረር ያለብህ፤ ለሙያተኛና ለሀገሩ የቻለውን የአቅሙን ለሠራ ለሰጠ ሰው ውጤታማም ይሁን አይሁን በክብር ነው መሸኘት ያለብህ እንጂ ተደራጅተህ ቡድን መስርተህ አይደለም ከኃላፊነቱ መግፋት ያለብህ፤ ይሄ እንደ ሙያተኛ እንደ ሙያ ማህበር ኃላፊ በጣም ነው ያሳዘነኝ፡፡ ዳግሞም አንድ ነገር ልንገርህ…
ሀትሪክ፡- ምን፤..?
አቶ ሰለሞን፡- መቼ ነው ለሀገሩ የሠራን፣ ለመስራት የሞከረን ሰው የምናከብረው? መቼ ነው አክብረን እንደተቀበልን አክብረን የምንሸኘው? መቼ ነው አመራር ላይ ስንቀመጥ ብስል የምንሆነው? መቼ ነው ከግል ስሜት ወጥተን እንደ ሀገር የምናስበው? ካልተሳሳኩ እዛ ቦታ ላይ የተቀመጡት በሙሉ ሃምሣ አመትን የተሻገሩ ናቸው፤ እድሜ ካልመከረን ካላስተማረን መቼ ነው የምንማረው? እነሱ ናቸው እኮ መከባበርን፣ ተመራርቆ መሸኛኘትን ሊያስተምሩን የሚገባው፤ እነሱ እኮ ናቸው ለአርአያነት የሚያበቃ ሥራ ሠርተው ማሳየት ያለባቸው፡፡ ሁሌ በውዝግብ አሰልጣኝ ማባረር የቤቱ መለያ መሆኑ የሚቀረውስ መቼ ነው? ይሄን ሰውዬ እኮ ኮትዲቯዋርን አሸንፈሃል ብለው ሸልመውታል፤ ከኮትዲቯዋር በኋላ ጨዋታ አላረገም…ውድድር በሌለበት ስታባርረው ሌላ ትርጉም ነው የሚሰጠው፤ ሌላውን ተወው እንኳን የሀገሪቱን ትልቅ ባለሙያ የቤትህን ሠራተኛ እንኳን ስታሰናብት የትራንስፖርት ሰጥተህ በክብር ነው የምትሸኘው፤ ለኢንስትራክተር አብርሃም ግን የዚህን ያህል እንኳን ክብር አልተሰጠውም…ፌዴሬሽኑ አብርሃምን በዚህ መልኩ ክብሩን ባልጠበቀ መልኩ ሲያሰናብት አንድ የዘነጋው ትልቅ ነገር ያለ ይመስለኛል…
ሀትሪክ፡-….ምን….?
አቶ ሰለሞን፡- ኢንስትራክተር አብርሃም ካፍ አለኝ የሚለው ፊፋ ውስጥ በአባልነት የሚሠራ የተከበረ ባለሙያ ነው፤ ለሀገራችን አሰልጣኞች የሙያና የእውቀት ሽግግር በማድረግ ከአሰልጣኝነቱ ውጪ በሙያው ሰውን የሚቀርፅ ሰው ነው፡፡ እንኳን ሀገራችን ካፍ አለኝ የምትለው ከ21ንዱ ኤሊት አፍሪካዊያን ከሀገራችን ደግሞ ብቸኛው ኤሊት ኢንስትራክተር ነው፤ ብዙ አሰልጣኞችን በማስተማር ብቁ ያደርገ ሙያተኛ ነው፤ በዚህ በጣም አስቸጋሪ ወቅት እንኳን በ Online በVirtual ትልቅ የአቅም ግንባታ ሥራ እየሠራ ያለ ሰው ነው፤ ችግር ቢኖርበት እንኳን ክሬዲቱን ግምት ውስጥ ገብቶ ነገ አብሮ በትምህርትና ስልጠና እንደሚሰራ ሰው በክብር ልንሸኘው ሲገባ ይሄ አልተደረገም ዛሬ ገፍትረነው ነገ አሰልጣኞችን አስተምር የምንለው በምን ሞራላችን ነው? ደግሞም “አላሰለጥንም” ቢል ልናስገድደው ነው? እሱ ከፈለገ ሱዳን ወይም ሌላ የትም ሀገር ሄዶ ማስተማር ይችላል፤ ግን ይሄ ነገር የእኛን ሀገር ሙያተኞች አይጎዳም? ይጎዳል፤ አብርሃምን እንኳን እኛ ካፍና ፊፋም ጭምር በእውቀቱ እየተጠቀሙበት ያለ የሚደነቅ ሰው ነው፡፡ “ነብይ ባገሩ…” እንደሚለው ተረት ሆኖ እኛ ክብር ነፍገነው የፊፋና የካፍ ደረጃን እየቆጠርን እንባርረዋለን፤ይሄ በግሌ በጣም አሳዛኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤እዚህጋ ከአብርሃም ሌላ ለኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውም ተገቢው ክብር አልተሰጠውም…
ሀትሪክ፡-….ለኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውም ተገቢው ክብር አልተሰጠውም ስትል?
አቶ ሰለሞን፡- ኢንስትራክተር ሰውነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስራን የሰራ፣ የራሱን ደማቅ ታሪክ ያፃፈ፣ ከ31 ዓመት በኋላ ሀገሩን ወደ ጠፋችበት መድረክ የመለሰ ታላቅ ባለውለተኛ ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚ ውስጥ ካሉት በሙሉ በሕዝብም ተቀባይነት ያለው ሙያተኛ በመሆኑ ሁሉም ሊያከብሩት ሊያዳምጡት ይገባ ነበር፡፡ የስራ አስፈፃሚነት አባልነቱንና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢነቱን ተወውና በፕሬዝዳንትነትም መቀመጥ የሚችል በተሻለም የሚመራ ሰው ነው፡፡ ሰውነት ግን በስራ አስፈፃሚው ክብር ሊሰጠው ሲገባ በተቃራኒው ቆመው ነው የሚታገሉት፤ እሱ የሚለው ሊሰማ ሲገባ ተደራጅተው ነው የሚጠብቁት፡፡ ይህ ሙያተኛ ያልሆኑ ሰዎች ለባለሙያው ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ሁሌ ከእነሱ ጋር ተሰብስቦ ሲመጣ እንጠይቀዋለን፡፡ በጠላትነት ስሜት ነው የሚያናግሩህ ስንለው መልስ አይሰጠንም፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር በግልፅ ታይቷል፡፡ እንደዚህ ያለ የተከበረ ባለሙያ በዚህ ደረጃ ስሜቱን መንካት ሌላ በጣም ያዘንኩበት ነገር ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአብርሃም ምትክ አሰልጣኝ ለመምረጥ 4 አሰልጣኞችን ብቻ ነው ኮንታክት እንዳደረገ የተሰማው፤ ይሄ አሠራር የሌሎች መወዳደር የሚፈልጉ፣በሀገራቸው መስራት የሚፈልጉ አሰልጣኞችን መብት ተጋፍቷል የሚል ነገር ይነሣል… በዚህ ላይ የአንተ እይታ ምንድነው?
አቶ ሰለሞን፡- በጣም መሠረታዊ ጥያቄ ነው፤ አራቱን አሰልጣኞች በምን መስፈርት ነው የመረጧቸው? እነሱ ባለሙያ አይደሉም ለሌቹ ባለሙያዎችስ ለምን እድል አልታሰጠም? እኛ መጀመሪያ ማስታወቂያ ወጥቶ ሁሉም ይወዳደር ያልነው እንደዚህ አይነት ቅሬታ እንዳይነሣ ነው፤ “ማስታወቂያ ለማውጣት ጊዜው አጭር ነው” ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቀረብን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ባለሙያዎች 4 ብቻ ናቸው እንዴ? ሌሎች አሰልጣኞችስ በሀገሪቱ የሉም? እነሱ መጠየቅ ወይም የሚሳተፉበት እድል መኖር ነበረበት፤ “በአስቸኳይ በሁለት ቀን ውስጥ ሲቪያችሁን አምጡ” ተብሎ መታየት ነበረበት፡፡ በዚህ የተነሣ እድሉን ተነፍገዋል፡፡ ብሔራዊ ሊግ ያለ አሰልጣኝ በፕሪሚየር ሊጉ ካለ አሰልጣኝ በትምህርትም በእውቀትም ሊበልጥ እንሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እንደዚህ አይነት ስርክል ስላለ እኮ ነው በፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ፊት የማይመጣው፤ ተወዳድሮ በሥራው ቢያልፍና ቢወቅድ ቅሬታ አይሰማም፡፡
ሀትሪክ፡- የአብርሃም መብራቱ ኮንትራት ከተቋረጠ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከ110 ሚሊየን ህዝብ በላይ የሚወክለው ብ/ቡድን አለቃ ሆኖ ተሹሟል… በውበቱ ዙሪያ ምን ትላለህ… ?
አቶ ሰለሞን፡- … እኔም ሆንኩ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በውበቱ መሾም ዙሪያ ችግር የለብንም፤ እኔ በግሌ በውበቱ መሾም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ የእኛ ጥያቄና ችግር ከፌዴሬሽኑ አሠራር ነው፤ እናንተ ባለሙያ ናችሁ ሃሳባችሁን አምጡ ብሎ ሃሣባችንን መጣሉ ነው ቅሬታችን፤ ከዚህ በተረፈ በውበቱ መሾም ምንም ቅሬታ የለንም፤ እኔ በግሌ ውበቱ ያሰለጠንኩት የልጅ ያህል የሚየው አሰልጣኝ መሆኑ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ በመሾሙ ብደሰትም ግን ደግሞ ለውበቱ በጣም ነው የማዝንለት…?
ሀትሪክ፡- በምንድነው የምታዝነው….?
አቶ ሰለሞን፡- ውበቱ በክለብ የሠራቸውን፣የሊጉ አሸናፊ የሆነባቸውን፣የሚገነባቸውን ቡድኖች እንዲሁም ሱዳን ድረስ ሄዶ በአል-አህሊ ሸንዲ ላይ የሠራቸውን ስራዎች ሁሉም ያውቀዋል…በአቅሙ ላይ ጥያቄ የሚያነሣ ሰው ያለ አይመስለኝም፤ውበቱ አሁን የተቀመጠው ግን በሚንቀለቀል እሳት ላይ ነው…እሳቱን ገለባ ያድርግለት እንጂ በዚህ በጣም ነው የማዝንለት፣ኃላፊነት የወሰደበት ወቅት ለእኔ እጅግ አስቸጋሪና ፈተና የበዛበት ወቅት በመጀመሪያው ኃላፊነቱ ይሄ መሆኑ በውስጤ ሥጋት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
ሀትሪክ፡- ውበቱ ባለፈው በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ሁላችንም አዲስ ብ/ቡድን ነው የሚኖረን” ከማለቱ ውጪ 41 ተጨዋቾችን በመጥራትም አዲስ ቡድን እንደሚገነባ በተግባር አሳይቷል፤ ይሄንን እንዴት ታዘብከው?
አቶ ሰለሞን፡- የእኛ ምክረ ሃሳብም ያጠነጠነው ካለው ጊዜ አንፃር አዲስ ቡድን መገንባት አስቸጋሪ ነው ከሚል ስጋት ነው፤ አሁን ውበቱ ከ40 በላይ ተጨዋቾችን ጠርቷል በዚያ ላይ ጨዋታው ጥቅምት 30 ነው በተጨማሪ ደግሞ ተጨዋቾቹ 7 ወር ሙሉ በኮቪድ ምክንያት ከጨዋታም ከልምምድ ውጪም ሆነው ነው የቆዩት፤ አንድ የዝግጅት ጊዜ የሚባለው ከ6-8 ሳምንታት ነው 7 ወር ተቀምጠው የመጡ ተጨዋቾችን እንዴት ነው ከ4 ሣምንት ባነሰ ጊዜ አዘጋጅተህ ለጨዋታ የምተደርሰው? ይሄ ለእኔ እንደ ባለሙያ በጣም ያስፈራኛል፡፡ በውበቱ መሾም ተደስቼ ግን አዝኚለታለሁ ያልኩት ከዚህ አንፃር ነው፤ መጥፎ ተመኘህ አትበለኝ እንጂ ነገሮች በጣም ከባድ ናቸው፡፡ የእኛ ሀገር ተጨዋቾች እንኳን 7 ወር ከውድድርና ከልምምድ ርቀው ውድድር ውስጥም ሆነውም የምናውቃቸው ናቸው፤ አንዳንዶቹን ተጨዋቾች ልምምድ በማቆማቸው ምን እንዳወጡ ታውቃለህ?
ሀትሪክ፡- .. ምን አውቃለሁ አንተው ንገረኝ እንጂ?
አቶ ሰለሞን፡- ውበቱ የጠራቸው ተጨዋቹች 7 ወር ቤታቸው የተቀመጡ ናቸው.. በዚህም አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ዳሌ አውጥተዋል፣ በጣም ወፍረዋልም ብዙዎቹ የውጪ ተጨዋቾች የራሣቸው ጂም አላቸው፤ በዚህም ምክንያት ቤታቸው ይንቀሳቀሳሉ፤ የኛዎቹስ ተጨዋቾች የራሳቸው ጂም አላቸው? የላቸውም ተጨዋቾቹ የጅምናዚየም ዕቃ ከመግዛት ቪትዝና መሽቀርቀር ላይ ነው ገንዘባቸውን የሚያፈሱት ጂም በመዘጋቱም ጂም ያለበት ቤት ሄደው ለመስራት እንኳን አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሣ ብዙዎቹ ዳሌ አውጥተዋል፤ ይሄንን በ4 ሳምንት ውስጥ እንዴት ነው አጥፋተህ ለጨዋታ የምታደርሰው? ለዚህ ነው ለውበቱ አዝንለታለሁ እሳት ላይ ነው የተቀመጠው እሳቱን ገለባ ያድርግለት የምለው፡፡
ሀትሪክ፡- ውበቱ አባተ በሣምንቱ አጋማሽ አሰልጣኝ አስራት አባተንና አንዋር ሲራጅን በረዳትነት የቀድሞ የቅድስ ጊዮርጊሱን ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስን በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት በመምረጥ የኮቺንግ ስታፉን አዋቅሯል…እንዴት አገኘኸው… ?
አቶ ሰለሞን፡- እኔ በአሰልጣኙ ምርጫ ላይ ምንም የምለው የለም በተሰጠው መብት ላይ ይጠቅሙኛል ያላቸውን መርጧል፤ ግን እኔ በሀገራችን የረዳት አሰልጣኞች ምርጫ ላይ ማለት የምፈልገው ነገር አለ እንደ ካፍ ኮንቬንሽን እንኳን ዋናው ምክትል አሰልጣኞች አመራረጥ ላይ የሚያስቀምጠው ነገር አለ፤ ምክትል ሆነው የሚሾሙት ቢያንስ የካፍ A ላይሰን ያላቸውና ከዋናው አሰልጣኝ ጋር ተመጣጣኝና ተቀራረቢ እውቀት ያላቸው ናቸው መሆን ያለባቸው፤ ዋናው አሰልጣኝ ሰው በመሆኑ ቢሳሳት የሚያርሙት፣ ትክክል አይደለህም፣ እንዲህ እናድርግ ብለው በእውቀት ሃሣብ የሚያዋጡ የሚሞግቱት… ዋናው አሰልጣኝም ምክትሎቹን የሚያከብራቸው ብሎም የሚፈራቸው እንጂ የሚንቃቸው መሆን የለባቸውም፤ እኛ ሀገር ግን ይሄ ይሠራበታል? ብትለኝ በፍፁም ነው መልሴ፤ ምክትል አሰልጣኝ የምንቀጥረው አይሸረሽረኝም፣ በጓደኝነት፣ በቲፎዞ የሆነች ቡድን ወይም ጋዜጠኛን ያስደስታል፣ እይዝበታለሁ ከዚህ ውጪ ደግሞ ሥራ የለውም ይጦርበት ብለን ነው ነው እኮ ረዳት አድርገን የምንቀጥረው፤ ይሄ ውለታ ውሏል ከማለት ውጪ ጠቀሜታው አይታየኝም፡፡ እኛ እንደውም ለስራ አስፈፃሚ ምክትል አሰልጣኝ የመቅጠር ኃላፊነቱ የዋናው አሰልጣኝ ቢሆንም በቴክኒክ ኮሚቴው በኩል ማለፉ ነው የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ኮን ተካይ፣ ተጧሪ ምክትል አሰልጣኝ ሣይሆን ተመጣጣኝ እውቀቱ ያለው ዋናው አሰልጣኝ ድንገት ችግር ቢገጥመው እንኳን የ110 ሚሊየን ህዝብ ውክልናን መሸከም የሚችልና እውቀት ያለው ረዳት ነው መሾም ያለብን፡፡
ሀትሪክ፡- የቴክኒክ ኮሚቴው ሙያዊ ምክረ ሃሳብ ሙያተኛ ባልሆኑ ሰዎች ውድቅ እንደሆነባችሁ ተናግረሃል በቀጣይስ እንዴት አብራችሁ ተስማምታችሁ መስራት ትችላላችሁ…. ?
አቶ ሰለሞን፡- ይሄ በጣም ከባድ ነገር ነው፤ የሙያተኛ ሃሣብ ሙያተኛ ባልሆነ ሰው ሲረገጥ ስታይ በጣም ያማል ስሜትም ይጎዳል፤ የእኛም ስሜት ተጎድቷል፤ እንዳልከው ሙያተኛ ያልሆነ ሰው የሙያተኛን ሃሣብ እስካላከበረ ድረስ ነገሮች ከባድ ነው የሚሆኑት፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚህ በመነሣት ብዙዎች የሙያተኛ ሃሣብ የማያከበር ከሆነ ቦታው ላይ አታስፈልጉም በሚል ራሳቸሁን ከኃላፊነት ማንሣት አለባችሁ በማለት አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል፤ ከእናንተ በኩልስ ሪዛይን ስለማድረግ ያሰበችሁት ነገር አለ…?
አቶ ሰለሞን፡-አሁን እንዲህ ነው ማለት አልችልም በግሌ የመስራት ፍላጎቴን የሚፈታተን ነገር ነው እየገጠመኝ ያለው፤ በቀጣይ እንደቴክኒክ ኮሚቴ ውሳኔያችን ምን ይሁን? የሚለውን በጋራ የምናየው ይሆናል፡፡
ሀትሪክ፡- አቶ ሰለሞን ድፍረት ላለው መልስህ አድናቆቴንም አክብሮቴንም ምስጋናዬንም አከታትያለሁ፡፡
አቶ ሰለሞን፡- እናንተም ለሰጣችሁኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡ የቴክኒክ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ሰለሞን አባተ የሰጡትን ምላሽ ተከትሎ ይመለከተኛል ወይም ቅሬታ አለኝ የሚል
ተቋምም ይሁን ግለሰብ ካለ ሀሳብን በሃሳብ የመታገል የሰለጠነ መንገድ ለማስተናገድ የዝግጅት ክፍላችን በር ሁሌም ክፍት መሆኑን የምንገልፀው በደስታ ነው፡፡
E-mail- [email protected]
MOB NO- 0911478296