አሰልጣኝ ፍሬዉ ሀይለገብርኤል ከሳምንታት በፊት ከሜዳዉ ዉጭ የቦትስዋና ብሔራዊ ቡድንን 3ለ1 በሆነ ዉጤት በረታበት ጨዋታ የተጠቀማቸዉን ቋሚ አስራ አንድ ተጫዋቾች ዛሬም የአንድም ተጫዋች ለዉጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በሩዋንዳዊያን ዳኞች በተመራው ጨዋታም የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታዉ ጅማሮ አንስቶ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያስመለከተን ነበር በተለይ በአጥቂዎቹ አርያት ኦዶንግ ቱሪስት ለማ እና ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተዉሏል። ለዚህ ማሳያም በ12ኛዉ ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ ግልፅ የግብ ዕድል ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርቷል። በ16ኛዉ ደቂቃ ደግሞ አርያት በአንድ ሁለት ቅብብል ከመሀል ተጫዋቾች የተሻገረላትን ኳስ ሰብራ በመግባት ኳሷን ለመቆጣጠር ብትሞክርም ኳሷ አምልጣት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠናክረዉ የቀጠሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በኋላም በ26ኛዉ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ግባቸዉን አግኝተዋል። የቀኝ መስመር ተከላካይ እና አምበሏ ያሻማችዉን ኳስ የቦትስዋናዋ ተከላካይ ኳሱን ብሎክ ለማድረግ በምትሞክርበት ጊዜ ኳሷ ተጨርፋ ወደ ግብ ተቀይራለች ።
ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ በቀላሉ ወደ ቦትስዋና የግብ ክልል ይደርሱ የነበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ ጎላቸዉንም ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ አስቆጥረዋል። በዕለቱ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችዉ አርያት ኦዶንግ ከመሀል የተሻገረላትን ኳስ የግል ብቃቷን ተጠቅማ ተጫዋቾችን በማለፍ ሁለተኛ ግብ አስቆጥራለች።
በተደጋጋሚ ወደ ግብ የሚሞከሩ ኳሶችን በቻሉት መጠን ከማፅዳት ዉጭ ይህ ነዉ የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልነበራቸው ቦትስዋናዎች በ 35ኛዉ ደቂቃ ላይ ሶስተኛ ግብ አስተናግደዋል።
የኢትዮያ ብሔራዊ ቡድን በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት ሰዓት ላይ ከቦትስዋና ተከላካዮች ተደርባ የተመለሰችን ኳስ ረድኤት ከርቀት አክርራ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጠረች ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ ብዙም ሳይቆይ ረድኤት ለራሷ ሁለተኛዉን ለብሔራዊ ቡድኗ ደግሞ አራተኛውን ግብ አስቆጥራለች።
ሙሉ ጌዜያቸዉን በመከላከል ላይ ሲያሳልፉ የነበሩት ቦትስዋናዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሲቃረብ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራን በፊት መስመር አጥቂያቸው አማካኝነት ቢያደርጉም የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በዚሁ የጨዋታ ዉጤትም የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛዉ አጋማሽ ይበልጥ የማጥቃት ሀልላቸዉን አጠናክረው የተመለሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች በተደጋጋሚ ጫና ፈጥረዉ በመጫወት በ57ኛዉ ደቂቃ ላይ አምስተኛ ግብ አስቆጥረዋል። ቱሪስት ለማ ግብ ጠባቂዋን አታላ በማለፍ ኳሷን ከግራ መስመር አካባቢ ወደ ግብ ስትልካት የቦትስዋናዋን የመሀል ተከላካይ ነክታ ወደ ግብነት ተቀይራለች።
ከአምስተኛው ግብ በኋላም ተቀይራ ወደ ሜዳ በገባችዉ አረጋሽ ካልሳ አማካኝነት ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ያህል ደቂቃዎች በቀሩበት ሰዓትም የቦትስዋና ብሔራዊ ቡድን ከባዶ መሸነፍ የዳኑበትን አንድ ግብ በፊት መስመር አጥቂያቸው አማካኝነት ማስቆጠር ችለዋል።
ጨዋታውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ5ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል ። በድምር ዉጤትም ኢትዮጵያ 8ለ2 የቦትስዋና አቻዋን በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።