ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና እና ዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር በተከታታይ ላሉበት ጨዋታዎች ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ዝግጅቱን የጀመረዉ የአሰልጣኝ ዉበቱ አባተ ስብስብ ከነሀሴ 04/12/2013 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅቱን በመከወን ላይ ይገኛል።
በአሠልጣኝ ዉበቱ አባተ ጥሪ ከተደረገላቸው 28ተጫዋቾች መካከል በቋሚነት ዝግጅት ወደ ሚያደርጉበት አዳማ ከተማ ያመሩት 24ተጫዋቾች ብቻ እንደሆኑ ታዉቋል። የፈረሰኞቹ አማካይ ሀይደር ሸረፋ እና በቅርቡ ወደ አልጀሪያዉ ክለብ ዝዉዉር ለማድረግ ሂደት ላይ የሚገኘዉ የቀድሞዉ የአፄዎቹ አጥቂ ሙጂብ ቃሲም በቋሚነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅለዉ ዝግጅት መጀመር ያልቻሉ ሲሆን በአንፃሩ አጥቂዉ አቡበከር ናስር እና የጣና ሞገዶቹ አማካይ ፍፁም ዓለሙ ፍቃድ በመጠየቃቸው ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ብሔራዊ ቡድኑን መቀላቀል ባይችሉም በቅርቡ ወደ አዳማ አምርተው ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
በተያያዘም አሰልጣኝ ዉበቱ ለሁለት አዳዲስ ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውም ይታወሳል። በዚህም መሰረት አጥቂዉ ቸርነት ጉግሳ እና አማካዩ በዛብህ መለዮ ወደ አዳማ በመጓዝ ስብስቡን መቀላቀላቸውን ታዉቋል።
- ማሰታውቂያ -
ማረፊያቸውን በኤክስኪዩቲቭ ሆቴል ያደረጉት ዋልያዎቹ ልምምዳቸውን በቀን ሁለት ጊዜ በማከናወን ላይም ይገኛሉ። ብሔራዊ ቡድኑ በወርሃ ነሐሴ መጨረሻ እና ጳጉሜ ወስጥ ከሚያከናውናቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በፊት የወዳጅነት ጨዋታ በቅርቡ እንደሚያደርግም ሀትሪክ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።