“አምስት የጋና ተጨዋቾች ቢመጡ ለኛ ቋሚ ናቸው አምስት የኛ ተጨዋቾችን ለጋና ተሰላፊ እንዲሆኑ መስጠት ይቻላል?”
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
/ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ/
የዋሊያዎቹ አለቃ ውቀቱ አባተ በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ ዛሬ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር በነበረው የደርሶ መልስ ጨዋታና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ በሰጡት መግለጫ “የአለም ዋንጫ ማጣርያ ምድባችን የነበሩት ዚምቧብዌ ጋናና ደቡብ አፍሪካ ከኛ የተሻሉ ቢሆንም ከነሱ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ጥረናል ያ ባለመሳካቱ ፊታችንን ወደ አፍሪካ ዋንጫ መዘጋጂያ አድርገን እየሰራን ነው በነጥብ ደረጃ የምንፈልገውን ባለማግኘታችን ውስጣችን ቅር ተሰኝቷል።በቀሪ ሁለት ጨዋታ ላይ የተሻለ ለመሆን እንሰራለን” ሲሉ ተናግረዋል።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ “ንግድ ባንክ ሜዳ ላይ በቀን አንዴ ልምምዳችንን እስከዛሬው ቀን ድረስ እየሰራን ነው ወደ 5 ተጨዋቾች በተለያየ ምክንያት ከቡድኑ ተለይተዋል ካሉን ቀሪ ተጨዋቾች ጋር የምንችለውን እናደርጋለን ቀጣይ ሁለቱ ጨዋታዎች ግን ለኛ ለውጥ ባይኖራቸውም ማንንም ሳንጎዳ ሳንጠቅም በጨዋነት ግጥሚያዎችን ለማድረግ እንጥራለን” ሲሉም ገልጸዋል።
አሰልጣኙ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ጋዜጣዊ መግለጫው ለምን ዘገየ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ” ይሄ በቀጥታ አይመለከተኝም ፕሮግራሙን ማዘጋጀት የፌዴሬሽኑ ሃላፊነት ነው በኔ በኩል ከሚዲያ ጋር ባለው ጉዳይ ላይ ለማውራት ዝግጁ ነኝ” ሲሉ መልሰዋል።
አሰልጣኙ እንዳሉት “ከኒጀሩ ጨዋታ ጀምሮ ለውጥ ያየንበት ሂደት አለ ባለፉት 7 ጨዋታዎች ያለውን ሂደት ስንገመገም በአማካይ 556 ፓስ አድርገን 520 የተሳካ ኳስ መኖሩ የቡድናችን አጨዋወቱ ምን እንደሚመስል ያሳየን ነው” ሲሉ ዕድገቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።
ስለ ፕሪሚየር ሊጉ ጅማሮ ሜዳ ሀዋሳ ስታዲየም የተጠየቁት አሰልጣኙ “የሀዋሳው ሜዳ ኳስ መቀባበል የማይቻልበት ሜዳ ነው በዚህ ሜዳ ማጫወትም ራሱ በደል ነው ተጨዋቾቹ ሲወድቁ ጠርሙስ ላይ እንደወደቀ እግራቸው ተቆራርጦ የሚነሱበት መሆኑ ያሳዝናል በቀጣይ ሌሎች ሜዳዎች ከሀዋሳ ትምህርት ሊያገኙ ይገባል” ያሉት አሰልጣኙ ስለወቅታዊው የሀገሪቷ ሁኔታ በሰጡት አስተያየት “አሁን ኢትዮጵያ ካላችበት አገራዊ ችግር አንጻር ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተናል ሁላችንም ከዚህ ቤተሰብ ነው የወጣነው ይሄ አይመለከተኝም የሚል የለም ነገር ግን ቻሌንጁን ለማለፍና ሀገራችንን በወከልንበት መድረክ የተሻለ ተፋላሚ ለመሆን እንጥራለን” በማለት አስረድተዋል።
በጨዋታ ሂደት የኳስ ቁጥጥር የተደረገው ቦታ የት ነው ያን ያህል ብልጫው ሊገርመን ይገባል ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አሰልጣኙ” ተጨዋቾቹ በእኛ ግብ ክልል ኳሱን ቢያንሸረሽሩና ብልጫ ቢኖራቸው ደስተኛ ነኝ ስለሚቆጠርብን ግብ ከሚያስብ በራሱ የግብ ክልል ኳስ የሚይዝ ተጨዋች ማፍራት ሊበረታታ ይገባል። ተቀይሮ ሊገባ ሲል ጫማ ከሚደብቅ ተጨዋች ኳስ ለመያዝ ወደመድፈር ከመጣን ለውጥ መኖሩን ያሳያል ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ተጨዋቾቻችን የተሻለ አቅም ላይ ሊገኙ ይገባል።
አሁን ግን አምስት የጋና ተጨዋቾች ወደኛ ቢመጡ ለኛ ቋሚ ናቸው አምስት የኛ ተጨዋቾችን ለጋና ተሰላፊ እንዲሆኑ መስጠት ግን ይቻላል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል።