“500 ደጋፊ ሊሄድ ቀርቶ ብሄራዊ ቡድኑ ራሱ ወደ ካሜሩን ይሄዳል ወይ? የሚለውን የምዕራባውያንን ምኞት የምናከሽፍበት መድረክ ነው”
አቶ ባህሩ ጥላሁን
/ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ/
“500 ዘማች ደጋፊዎችን ይዘን ወደ ካሜሩን ለመመጓዝ ተዘጋጅተናል”
አቶ ሲሳይ አድርሴ
/የሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስኪያጅ/
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን 500 ደጋፊዎችን ወደ ካሜሩን ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ።
የሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አድርሴና የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በሸራተን አዲስ በሰጡት መግለጫ “የሀገርን መልካም ገጽታ የምናሳይበትና ሀገሪቷን ለአለም የምናስተዋውቅበት መድረክ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
- ማሰታውቂያ -
“ከኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የሰላምና የጀግኖች ሀገር መሆኗን የምናሳይበት ምዕራባውያን በተሳሳተ መረጃ የሚያስተላልፉት ውሸት የምናከሽፍበት መድረክ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተነዋል” ሲሉ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልጸዋል።
” መላው አለም እንኳን 500 ደጋፊ ወደ ካሜሩን ሊሄድ ብሄራዊ ቡድኑ ራሱ ይሄዳል ወይ እያሉ ነው አዲስ አበባ ተከባለች ጦርነቱ ቀጥሏል የሚለውን ወሬ ለማክሸፍ የሚካሄድ ጉዞ ነው ይህም እንደሚሳካ ርግጠኛ ነኝ” ያሉት አቶ ባህሩ “25ቱ ጋዜጠኞች አምባሳደሮቻችን ናቸው ከዘገባ ውጪ በውድድሩ ላይ ከሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞች ጋር ተወያይቶ እንደ ሀገር የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ መገንባትና ያለውን እውነታ መግለጽ ይጠበቃል ይህም ከውጊያው አውድማ በተመሳሳይ በሚዲያ ላይ ያለውን ጦርነት ሊዋጉ የሚሄዱ ናቸው” በማለት የሚዲያውን ተልዕኮ አሳውቋል።
የሲሳይ ፕሮሞሽን ባለቤትና የጉዞው ዋና አስተባባሪ አቶ ሲሳይ “ለጉዞው የአውሮፕላን የምግብና የማረፊያ የሀገር ውስጥ ትራንስፖርት የስታዲየም መግቢያ ወጪን የሚሸፍን ሲሆን ለዚህም 55 ሺህ 223 ብር እንደሚከፈል ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 25 ጋዜጠኞች በነጻ የሚጓዙ ሲሆን ሙሉ ወጪያቸውንም በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች የሚሸፈን መሆኑ ታውቋል። አቶ ሲሳይ ” ሀገሬ አምናብኝ ፌዴሬሽኑም ለሰጠኝ ሀላፊነት ታማኝ ነኝ ሀገሬን ለማገልገልም ዝግጁ ነኝ ልዩነታችንን አጥበን እንደ ሀገር በርትተን ከሰራን ኢትዮጵያን የማኩራት ስራ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ” ሲሉ አስረድተዋል።
“በቀጣዩ አርብ ወደ ካሜሩን ስለምሄድ የ48 ሰአት የኮቪድ ምርመራ ሂደቱን በተመለከተ እንዴት ማድረግ እንዳለብን ተወያይቼ ስለሚጓዘው የልኡካን ቡድን የተሻለ ስራ ሰርቼ እመለሳለሁ እንደኔ 500 ዘማች ደጋፊዎች አሉን ብዬ ነው የማምነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንና በሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን በሁለቱ ተቋማት ስምምነት መሠረት ሁለቱ ተቋማት ከተጣራው ገቢ 50 በመቶ የሚካፈሉ ይሆናል” ተብሏል።
ሁለቱ ተቋማት የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ለተጓዦች ምዝገባ መጀመሩ ታውቋል።