የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2021 አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በካሜሩን ለሚደረገው ቆይታ የደጋፊዎች ጉዞን አስመልክቶ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ተጨማሪ ኃላፊነት በተሰጠው Elnet Tour and Travel አማካኝነት ዛሬ ከሰዓት በኢሊሌ ሆቴል የሚዲያ አካላት በተገኙበት መግለጫ ተሰጥቷል።
በመግለጫውም:-
ከጥር 1/2014 ጀምሮ በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሸን ጋር በመተባበር ደጋፊዎችን ወደ ካሜሩን ለመዉሰድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ ሆሊደይስ ጋር በርካታ ደጋፊዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ፣ ምቹ በሆነ እና ጥራት ባለዉ መስተንግዶ ብሔራዊ ቡድኑን ደግፈዉ አንድነታቸውን አሳይተዉ እና ሀገር ጎብኝተዉ የሚመለሱበት ሁለት ፓኬጆች አዘጋጅተዋል።
የመጀመሪያዉ ፓኬጅም ለአስራ አንድ ቀናት የሚቆይ ሲሆን የደርሶ መልስ የአዉሮፕላን ትኬትን ጨምሮ በካሜሩን ያዉንዴ በሚኖራቸዉ ቆይታም የትራንስፖርት አገልግሎት ፣ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶችን ፣ የጉብኝት ፣ የምግብ እንዲሁም የቪዛ እና ኢንሹራንስ ወጪዎች የሚሸፈኑ ይሆናል። ለዚህም አጠቃላይ 135ሺ ብር ተጓዥ ደጋፊው የሚከፍል ይሆናል።
- ማሰታውቂያ -
ከዚህ በተጨማሪም በሁለተኛው ፓኬጅ ደግሞ ለአስራ ሰባት ቀናት ቆይታ የሚኖረዉ ሲሆን ከላይ በመጀመሪያው ፓኬጅ በሙሉ የተጠቀሱትን ጨምሮ የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እና መሰል ፕሮግራሞችን የሚያካትትም ይሆናል።
በተያያዘም ካሜሩን አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴል በሚገኙት Hotel Le Best ፣ Simson Hotel ፣ Minolo Hotel እና Hotel Belvie ተመርጠው የተዘጋጁ ሆቴሎች መሆናቸው ተገልጿል ።
በሌላ በኩል ከጋዜጠኞች ጋር በተያያዘም የተወሰኑ የሚዲያ አካላትን ወደ ስፍራው ለመዉሰድ ሀሳብ እንዳለ እና ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ የትኞቹ ጋዜጠኞች ሊጓዙ እንደሚችሉ መስፈርት ስላልወጣ በቅርቡ ተጓዥ ጋዜጠኞች ማለትም መስፈርቱን የሚያሟሉት ይፋ እንደሚደረጉም ተገልጿል።