ከጥር 1/2014 ዓ.ም ጀምሮ በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከስምንት አመታት በኋላ ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከዝግጅት አንስቶ ለሚኖራቸው አጠቃላይ ወጪ 41 ሚሊዮን ብር እንዲለቀቅላቸው የሚመለከተዉን የመንግስት አካል መጠየቃቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ገልጸዋል።
ከዉድድሩ አስቀድሞ የሚኖራቸውን ዝግጅት ከተቻለ ከሀገር ዉጭ ለማድረግ በዕቅድ ደረጃ ሀሳብ እንዳለ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ይህ ካልተሳካ ግን ዝግጅታቸውን በሀገር ዉስጥ እንደሚያገርጉ አሳዉቀዋል።
ከዝግጅቱ ጋር ተያይዞም ቢያንስ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ታዉቋል።
ይሄንን እና ተያያዥ የዋልያዎቹን ዝግጅት በተመለከተም ከኢትዮጵያ ባህል እና ስፖርት ሚኒስተር ጋር ዉይይት መደረጉ ታዉቋል።