በሀገር ውሰጥ ሊግ ብቻ በሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚደረገው የቻን ውድድር በመጪው ዓመት ጥር ወር ላይ በአልጄሪያ እንደሚደረግ ይታወቃል ። በውድድሩ የሚሳተፉ ሀገራትን የሚለዩት የማጣሪያ ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ሲጀምሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከደቡብ ሱዳን አቻው ጋር በመጪው አርብ በታንዛኒያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል ።
ለዚህ ጨዋታ ዝግጅት ቡድኑ በአዳማ ከተማ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ዝግጅቱን ያደረገ ሲሆን በነገው ዕለትም ወደ ዳሬ ሰላም የሚያቀና ይሆናል ።
የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ዝግጅታቸውን በተመለከተ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል ።
” ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አስታላልፍን ዝግጅታችንን ከሐምሌ 6 ጀምሮ ጀምረናል ። በዕርግጥ የገቡት በ4 ነው ግን በ4 እና በ5 የጤና ምርመራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ካደረግን በኋላ መደበኛ ልምምዳችንን ወደ አዳማ በመጓዝ ጀምረናል ። አንደምታውቁት ከፍተኛ ጫና ካለበት ወድድር ነው የመጡት የማገገም እና ታክቲካል ስራዎች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ከነበሩን ስድስት የልምምድ ቀናት ውሰጥ አምስቱን አንድ ጊዜ ብቻ ስናከናውን የቀረውን አንድ ቀን ሁለት ጊዜ ለመስራት ሞክረናል ። አብዛኛውን ሜዳ ላይ ነው ያሳለፍነው ። ”
- ማሰታውቂያ -
” ከጠራናቸው 23 ተጫዋቾች መካከል አማኑኤል ዮሀንስ ቀደም ሲል በወድድር ላይ እያለ መጠነኛ ጉዳት ነበረበት ዳዋም እንደዚሁ በዛብህ መለዮ ደግሞ ከጡንቻ መሳሳብ ጋር የተያያዘ መጠነኛ የህምም ስሜት ከመፈጠሩ ውጪ ሌሎች ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ነው የሚገኙት ። ከሞላ ጎደል ዝግጅታችን መጥፎ የሚባል አይደለም ። ይህን እንድል የሚያስገድደኝ ነገር ምንድነው ወቅቱ ነው ። አብዛኞቹ ተጫዋቾቻችን አንደኛ ከረጅም ድካም ላይ ነው ያሉት ሁለተኛ ከተጫዋች ዝውውር ጋር ተያይዞ ከክለብ ክለብ መዘዋወሪያ ጊዜ ከመሆኑ አንፃር በአዕምሮም በአካልም ዝግጅታችንን በፈለግነው ደረጃ እንዳናከናውን እንቅፋት እንደነበሩ ለመመልከት ችያለሁ ። ”
” ተጋጣሚያችንን ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ ሰፊ የሆነ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም በዕርግጥ ከሰኔ 28 ጀምሮ ልምምድ እንደጀመሩ መረጃው አለን ። ቀደም ብለው አስበውበት እየተዘጋጁ እንደሆነ አውቃለሁኝ ። ያው የቻን ውድድር ከመሆኑ አንፃር ሁሉም በሀገር ውሰጥ የሚወዳዳሩ ከመሆናቸው አንፃር በቂ መረጃ ለማግኘት ትንሽ አዳግቶናል ። ከዛ ውጪ ግን ጨዋታውን አሸንፈን ለማለፍ በቂ ዝግጅት አድርገናል ። ”
በመቀጠል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል ።
ለዝግጅቱ እንቅፋት ከሆኑ ነገሮች ጋር በተያያዘ
” ቀኖቹ በጣም አጭር ናቸው ። ውድድሩ ያለቀበት ጊዜ ለልጆቹ የሰጠነው ዕረፍት ሲደመር ከፊታችን ደግሞ በቀጣዩ ጨዋታችን መሀል በጣም አጭር ጊዜ ነው ያለው ። ስለዚህ ልጆቹን ከውድድር ወደ ውድድር መልሰህ መክተት አንዱ ፈታኝ ነገር ነው ። ሁለተኛው ነገር አዕምሮአቸው ያልተረጋጋ ልጆች ከፊርማ ጋር ተያይዞ ወደ እዛም ወደ እዚም ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉበት ሊግ ላይ ስለሆነ ያለነው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልጆቹን እንዳይወጡ እና እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ የብሔራዊ ቡድኑ ስራ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረግ በፍፁም ሊሞከር የማይችል ነገር ነው ። ልጆቹን በአካል ልንይዛቸው እንችላለን ግን በተለያየ መንገድ ለኛ የሚሰጡትን ትከሩት ሊቀንሱት ይችላሉ ። ስለዚህ በተቻለ መጠን ያ እንዳይሆን አንዳንዶቹ ከልምምድ ሰዓታችን ውጪ በሆነ ሰዓት በተለይ እዚህ አዲስ አበባ በነበርንበት ጊዜ ንግግራቸውን እዛው ሆቴል አካባቢ ማድረግ እንዲችሉ ሌሎችም የተጠናቀቀ ነገር ያላቸውን ለፊርማ ደርሰው እንዲመጡ በመፍቀድ ሁለቱን ነገሮች እያቻቻልን ለመሄድ ነው የሞከርነው ። በመጨረሻ ግን የተወሰኑ ዝውውሮችን አዳማ እኛ ያለንበት ድረስ ከፌዴሬሽኑ የተወከሉ ሰዎች መጥተው የልጆቹ ዝውውር እንዲያልቅና ተረጋግተው እንዲቆዩ ለማድረግ ነው የሞከርነው ። ”
አዲስ ተጫዋቾችን ከማካተት ጋር በተያያዘ
” እንደ እውነቱ ከሆነ አሁን ካሉት ተጫዋቾች ውጪ ሌሎች ተጫዋቾችን ማካተት አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል ። እነዚሁኑ ልጆች በዚህ ውድድር ባናካትታቸው እና እረፍት ሰጥተናቸው ቢሆን መስከረም ላይ ለሚጠብቀን የጊና ጨዋታ እንደገና እንደአዲስ ነው ለቅድመ ዝግጅት የምናመጣቸው ። እነዚህ ጨዋታዎች ማግኘቱ ራሱ ለነሱም ተጨማሪ ጥቅም ነው ። ከዛ አኳያ የነበረውን ቡድን ይዞ መቀጠሉ እና የተወሰኑ ተጫዋቾችን መጨመር እንደ አንድ አማራጭ ነው የወሰድነው ። ”
ተጫዋቾች ከአድካሚ የውድድር ጊዜ ወደ ሌላ ውድድር ስለመምጣታቸው
” ከውድድር ወደ ሌላ ውድድር መሄዱ አድካሚ ነው ። የኛ ልጆች ደግሞ እንደዚህ አይነቱን ድካም የመቋቋማቸው ነገርም አስቸጋሪ ነው ። በምንችለው መጠን ግን ይሄ ሌላ ምዕራፍ ነው ። ቻን ለሀገራችንም ለተጫዋቾችም ለእግር ኳስ ቤተሰቡም ሌላ ዕድል ነው ። አፍሪካ ዋንጫ መግባት ችለናል በዛ ውድድር ላይ የጀመርነው መንገድ አለ አሁን ደግሞ በቻን ውድድር ቢያንስ ለአልጄሪያው ውድድር ለማለፍ ደግሞ ሌላ ዝግጁነት እንዲኖራቸው ዕቅድ ከማስቀመጥ አንፃር በዛ ሀሳብ ውስጥ እዲጠመዱ በማድረግ እያነሳሳን ነው ያለነው ። እንግዲህ ከባድ ነው ምክንያቱም የውድድር ዓመት ሙሉ ተጫውቶ ሳያገግሙ ወደ ሌላ ጨዋታ መሄድ በሞራል ደረጃ የሚያመጣው ነገር አለ ያንንም ቢሆን ግን በተቻለ መጠን ለመጠበቅ እየሞከርን ነው ። ”
ተጋጣሚን ካለማወቅ ጋር በተያያዘ
” ተጋጣሚን አለማወቅ ይጎዳናል ። ይጎዳናል ስንል ቢያንስ ዝግጅታችንን በተወሰነ መንገድ ጎዶሎ ሊያደርገው ይችላል ። ግን የሚመስለውን ነገር ግን መገመት ይቻላል ። ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ያለችበትን ደረጃ ለማየት ሞክረናል ። ከሞሪታንያ ከማሊ ያደረገቻቸውን ጨዋታዎቿን አይተናል ግን ያ ቡድን አይደለም እዚህ የቻን ውድድር ላይ የሚመጣው ምናልባት በግማሽ ደረጃ የሚደርሱ አዲስ ልጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ እንገምታለን ። ስለዚህ በይበልጥ ያተኮርነው በራሳችንን ቡድን የጀመርነውን ነገር አጠናክሮ የመቀጠል ላይ እና ተጋጣሚያችን ሊመጣ ይችላል ብለን በምናስበው ነገር ላይ ለመዘጋጀት ሙከራ አድርገናል ። ሌላ አማራጭ ግን የለም ። ለምሳሌ እነሱ እኛን የሚያዩበት ዕድል ይኖራል ምክንያቱም አፍሪካ ዋንጫ የምናሳትፈው ቡድን ያ ነው የነረበው አሁንም 90% አካባቢ ያው ነው ። የነሱ ግን ከኛ ትንሽ ይለያል ።
እሰራኤል ፤ አውስትራሊያ ፤ ኡጋንዳ ፤ ኬንያ የሚጫወቱ ልጆች አሏቸው ስለዚህ እነዛ ልጆች እዚህ ውድድር ላይ አይካፈሉም ። ቢያንስ ቢያንስ ግን ምን አይነት ጨዋታ ሊጫወቱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል ብዬ ነው የማስበው ። ”
ከኮንትራት ጋር በተያያዘ
” ኮንትራቴ የሚያበቃው መስከረም መጀመሪያ ላይ ነው ። እንዳለመታደል ሆኖ በኛ ሀገር እንደዚህ አይነት ነገር አልተለመደም ኮንትራት የሚጠናቀቅበት ቀኗን ነው እንጂ ያየነው ቀጣይ ኮንትራት ግን በክለብም ይሁን በተጫዋቾችም ይሁን በአሰልጣኞች የመጨረሻዋ ቀን ነው የምትጠበቀው ። በተጫዋቾች ላይ ካየህ ነፃ የሚሆኑትተ ጊዜ አለ ከዛ አንድ አመት አስቀድመው ነጃ የሚሆኑበት ጊዝ አለ ። ከአሰልጣኝ ጋር ተያይዞ እንደዚህ አይነት ነገሮች መጀመር ያለባቸው ወይንም ማወቅ ያለብህ ቢያንስ 3 ወር ወይም 6 ወር ሲቀረው ንግግር ቢኖር የሚመጡ አለመረጋጋቶችን ይቀንሳል ።
” ከፌዴሬሽኑ ጋር ንግግር ጀምረናል ። በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነገር አለ ። ዝርዝር በሆኑ ነገሮች ላይ ግን ማውራት ይጠበቃል ። ከዛ በኋላ ያለውን ሂደቱ ነው የሚወስነው ። እቆያለሁ ወይም አልቆይም የሚለውን ነገር ፈጣሪ ነው የሚያውቀው ግን በበጎ መልኩ በኔም በኩል የጀመርኩትን ነገር ለመጨረስ የሚሆን ፍላጎት አለ ። በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በኩልም የተጀመረው ነገር እንዲቀጥል ፍላጎቱ አለ ። ግን ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተነጋገርን መስማማት ይጠበቅብናል ። ይሄም በቅርቡ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ። ”
አሰልጣኝ ውበቱ በመጨረሻም ኦሪገን ላይ እየተደረገ ባለው የ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ላይ እየተመዘገበ ባለው ውጤት በግላቸው በጣም መደሰታቸውን ገልፀው በስፍራው የሚገኙትን የልዑክ ቡድኑ አባላት እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያዊያንን በብሄራዊ ቡድኑ አባላት እና በፌዴሬሽኑ ስም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።