ወላይታ ድቻዎች በጨዋታ ላይ የተጎዳው የአስናቀ ሞገስ የህክምና ወጪ አሁንም አለመሸፈናቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ተጨዋቹ ከሀትሪክ ጋር በነበረው ቆይታ “ባህር ዳር ላይ እየተጫወትኩ እያለሁ በመጎዳቴ ህክምና እንዳደርግ በክለቡ ሃኪም ተወስኖ አዲስ አበባ መጥቼ ህክምናዬን በራሴ ወጪ አደረኩ ጥቃቅኑ ወጪ ሳይቆጠር ከ5ዐ ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጌያለሁ ይህን የሚገልፅ ደረሰኝም ወደ ክለቡ ፋይናንስ ክፍል ልኬያለሁ ነገር ግን ምንም አልተደረገልኝም ምላሽ ካጣሁ ወራቶች ተቆጥረዋል ምን ማድረግ እንዳለብኝም ከመወሰኔ በፊት የመጨረሻ ሙከራ እያደረኩ ነው አሁንማ የፋይናንስ ክፍሎቹ ምላሽ አልሰጡኝም ገንዘብ የለም እያሉም ነው ክለቡ የኔን ወጪ የመሸፈን ግዴታውን እንዲወጣ እጠይቃለሁ” በማለት ሁኔታውን አስረድቷል፡፡
“በጉዳዩ ዙሪያ የፋናይንስ ኃላፊዎችና አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በደንብ ያውቃሉ አዲሱ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሳሙኤል መረጃውን ካላገኙ በወቅቱ ስላልነበሩ ላያውቁ ይችላሉም” ሲል አስናቀ ለሀትሪክ ገልጿል፡፡ ይህን ተከትሎ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከሀትሪክ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “የተጨዋቹ ጥያቄ ትክክለኛ ነው ጨዋታ ላይ እያለ ነው የተጎዳው በወቅቱ ጉዳቱ የደረሰበት ጅማ ላይ እያለ ሲሆን የክለቡ ሀኪም ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ እንዲታከም ሪፈር በመፃፉ ሄዶ ታክሟል ክለቡ ወጪውን የመሸፈን ግዴታ አለበት ለዚህም እኔ ምስክር ነኝ” በማለት የተጨዋቹ ጥያቄ እውነትና ተገቢ መሆኑን መስክረዋል፡፡
ከክለቡ የፋይናንስ ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ኢያሱ ጉዳዩ ከእኔ ይልቅ የሚያውቀው አቶ ያሬድ ስለሆነ ለእሱ ብትደውል ይሻላል ብለው ወደ አቶ ያሬድ ብደውልም ቴክስት ብልክም ምንም ምላሽ አላገኘንም የክለቡን ትክክለኛ አቋም ለማወቅ በቅርቡ ስራአስኪያጅ ሆነው ወደ ተሾሙት አቶ ወንድሙ ሳሙኤል ጋር ቴክስት ብንልክም ስልክ ብንደውልም ሊያነሱልንና ምላሹን ሊገልፁልን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ክለቡ የግንቦት ወር ደመወዝ 40 ቀን ሞልቶትም አለመክፈሉ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ደመወዝ እየከፈሉ አይደለም ከሚባሉ ጥቂት ክለቦች መሀል አንዱ ወላይታ ድቻ ነው፤ ማንኛውንም ሠራተኛ 30 ቀን ሰርቶ የሚከፈለው በ30 ቢሆንም እኛ ክለብ ግን የሚከፈለው 30 ቀን ሰርተን በ50ኛው ቀን ነው በቅርቡ ነው በ47 ቀን የከፈሉን በማለት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የተናገሩትን የሚያስታውስ ሆኗል፡፡ የግንቦት ወር ሳይከፈል ዛሬ 41ኛ ቀን መሆኑን የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡
በሌላ በኩል ተጨዋቾች እስከ ሰኔ 30 ቀን ኮንትራት ስላላቸው የተሟሉ የውል ስምምነቶች ክለብ ከክለብ የቀየሩ፣ ውላቸውን ያደሱ ተጨዋቾች ይፋ ባይደረግም የመረጃ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ በተለይ ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ በኩል በከፍተኛ ሁኔታ መጠመዳቸው እየተነገረ ነው የሚያዘዋውሯቸው ተጨዋቾች ከሀምሌ1/2013 ጀምሮ ይፋ እንደሚደረጉ የታወቀ ሲሆን አስቻለው ታመነ፣ ሙላለም መስፍን (ዴኮ)፣ ጋዲሳ መብራቴ፣ ሳላሀዲን ባርጌቾ፣ ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ)፣ ተክለማርያም ሻንቆ /ጎሜዝ/ እንዲሁም አስራት ቱንጆን ጨምሮ በርካቶች ክለቦቻቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ በሚል በስፋት እየተነገረ ሲሆን ከሀምሌ ጀምሮ የዝውውር መስኮቱ ማድመቂያ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡