አይቮሪኮስታዊው የወልቂጤ ከተማ ግብ ጠባቂ ሲልቭያን ግቦሆ ሀገሩ ላለባት የ2022 የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በስብስቡ ውሰጥ ተካቶ በነበረበት ጊዜ በተወሰደ ናሙና ትራይሜታዚዲን የተባለ እና በአለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ ( WADA ) የተከለከለ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ በመገኘት በጊዜያዊነት ከማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች ታግዶ መቆየቱ ይታወሳል ።
ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የአለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ( FIFA ) ዲሲፕሊን ኮሚቴ ተጫዋቹ ንጥረ ነገሩን መጠቀሙ በምርመራ ከተረጋገጠበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ18 ወራት እገዳን አስተላልፎበታል ። በዚህም መሰረት እስከ ሰኔ 16 2015 ዓ.ም ድረስ በየትኛውም የፊፋ እውቅና ባላቸው የእግርኳስ ውድድሮች ላይ መሳተፍ አይችልም ።
ግብ ጠባቂው የውድድር ዓመቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ለሰራተኞቹ በመፈረም በተከታታይ 8 የመጀመሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 5 ግቦችን አስተናግዷል ።
በተጨማሪም በአይቮሪኮስት ብሄራዊ ቡድንም ለተከታታይ አመታት በቋሚ ግብ ጠባቂነት የተጫወተ ሲሆን በ2015 የአፍሪካ ዋንጫን ያሸነፈው የዝሆኖቹ ስብስብ አባልም ነበር ።