በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘውና በሊጉ 5 ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ዘጠኝ ተጨዋቾች የአምናው የፊርማ ክፍያ አልተከፈለንም በሚል ልምምድ ማቆማቸው ተነገረ።
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ እስራኤል፣ አቡበከር፣ ያሬድ፣ ሀብታሙ፣ሙሉጌታ፣ ዳግም፣ ተስፋዬ፣አህመድና በሀይሉ በ2013 ሲፈርሙ በ50 ሺህ ብር ሲሆን በወቅቱ ቃል የተገባላቸው ክፍያ ባለመፈጸሙ ከሰኞ ጀምሮ ልምምድ ማቆማቸው ታውቋል።
በጌታነህ ከበደ ግብ ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 ከረቱበት ጨዋታ አስቀድሞ ላለመጫወት ወስነው የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው ባደረገው የማግባባት ስራ መጫወታቸው ታውቋል።
ቅዳሜ በ6ኛው ሳምንት መርሃ ግብር አርባምንጭ ከተማን በሚገጥሙበት ጨዋታም ተጨዋቾቹ እንደማይኖሩ መታወቁ በክለቡ ውጤታማ ጉዞ ላይ ሌላ መሰናክል እንዳይሆን ተሰግቷል። ዘጠኙ ተጨዋቾች ከ400 ሺህ ብር እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ ከክለቡ የሚፈልጉ መሆናቸው ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
በጉዳዩ ዙሪያ የክለቡን ምላሽ ለማወቅ ወደ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ታምራት ታዬ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ብንደውልም ዝግ በመሆኑ የክለቡን ምላሽ ማወቅ አልቻልንም።