➢የይግባኝ ውሳኔን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ማየቱ
ያልተለመደ መሆኑ ጥያቄ ተነስቶበታል
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የወልቂጤ ከተማው አጥቂ ጌታነህ ከበደን የሶስት ጨዋታ ቅጣት ማንሳቱ የህጋዊነት ጥያቄ ተነስቶበታል።
የሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ 1 ለ1 በተጠናቀቀው የወልቂጤ ከተማና የሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ኮሚሽነር “ተጨዋቹ ዘለፋ ፈጽሟል” በሚል ያቀረበውን ሪፖርት ተመልክቶ የሶስት ጨዋታ ቅጣት ማስተላፉ ይታወሳል የዚህ ኮሚቴ አባላት ከዲሲፕሊንና ከዳኞች ኮሚቴ እንዲሁም ከሊግ ኩባንያ የተውጣጡ መሆናቸው ታውቋል።
ተጨዋቹ ግን ውሳኔውን በመቃወም ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ በማለት በሰባት ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጠው ግንቦት 19/2014 ደብዳቤ ያስገባል። ደብዳቤው የደረሰው የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ጉዳዩን ወደ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ቢመራውም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ አልቀረበልኝምና አላየውም በማለት ጉዳዩን ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ መርቶት ዲሲፕሊን ኮሚቴው ቅጣቱን መሻሩ አነጋጋሪ ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
ዲሲፕሊን ኮሚቴ በፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ማህተምና ፊርማ በሊግ ኩባንያ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ውስጥ አቶ አበራ ሀብቴን በመወከል ስራውን እየሰሩ ባለበት ሂደት ተወካዩ ያሉበት ኮሚቴን ውሳኔ መሻሩ በወከላቸው ባለሙያ አለማመኑን ወይም ከስልጣን ድርሻው ውጪ እየሄደ መሆኑን ያሳየበት ነው ተብሏል።
ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም ቢሆን በ24ቱ ሳምንት ባልታየ ፍጥነት ውሳኔውን አላየውም የማለቱ ጉዳይ የህግ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል። የጅማ አባጅፋሩ ዳዊት እስጢፋኖስ የሰባት ጨዋታ ቅጣት አላይም ብሎ ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ያልመራው ኮሚቴው ተጨዋቹም ከሰባቱ ጨዋታ አምስቱ ካመለጠው በኋላ ጉዳዩን አይቶ ውሳኔውን ያሳወቀበትን ሂደት ያስተወሱ ወገኖች የኮሚቴው ፍትህ አስፋኝነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል።
ዳዊትም ሆነ ጌታነህን እንደምሳሌ የሚያነሱ ወገኖች ሁለቱም አጠፉ የተባለው ተመሳሳይ ዳኞችን ዘልፈዋል ሆኖ የዳዊት ይግባኝን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ቃለጉባኤ ሳይጠይቅ ውሳኔ ሲሰጥ የጌታነህን ግን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ የለም ብሎ ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ መምራቱ በአንድ ጉዳይ የተለያየ አቋም መያዙም እየተተቸበት ነው።
“የፍትህ አካላቱ ህጎችና ብይናቸውን ሁሉን ባለድርሻ አካላት እኩል የማያደርጉ ከሆነ ለአንዱ ልጅ ለሌላው የእንጀራ ልጅ ሆኖ ከታየ ውድድሩ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ከባድ በመሆኑ የፍትህ አካላቱ ተአማኒነት ላይ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም” በማለት የሚናገሩ ወገኖች በርክተዋል።
ሊግ ኩባንያው በበኩሉ ውሳኔውን ከሚዲያ ከመስማት ውጪ የደረሰው ደብዳቤ እንደሌለ ገልጾ ውሳኔው ሲደርሰው ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል