“በቀጣዩ ጨዋታ ጌታነህን እናሰልፈዋለን”
አቶ ብርሃኑ በጋሻው /የተጨዋቹ ጠበቃ/
ወልቂጤ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ጌታነህ ከበደ እንዲሰለፍ መመርያ የተሰጣቸው የቡድን መሪው አወል ከድር ሃላፊነታቸውም አልተወጡም በሚል መታገዳቸው ተሰማ።
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ጌታነህ ከበደ ቅጣቱ ተነስቶለት እንዲጫወት ቢወስንም የሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ አልቀበልም በማለቱ ጌታነህ ከበደ በዛሬው ጨዋታ ሳይሰለፍ የቀረ መሆኑ ይታወቃል።
በጉዳዩ ዙሪያ የተገኘውን መረጃ ያረጋገጡት የጌታነህ ከበደ ጠበቃ የህግ ባለሙያው ብርሃኑ በጋሻው ግን በጨዋታው ጌታነህ እንዲሰለፍ ክለቡ ወስኖ ለሊግ ኩባንያው ገልጾ እያለ ቡድን መሪው አወል ከድር የተወሰነውን ውሳኔ በመተግበር ጌታነህ ከበደን እንዲገባ አላደረጉም በሚል ከደመወዝና ከስራ መታገዳቸውን አስረድተዋል።
- ማሰታውቂያ -
ጠበቃው አክለው እንደገለጹት አሁንም የሊግ ኩባንያው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ውሳኔን እንደማይቀበሉትና የፊታችን ሀሙስ ሰኔ 16/2014 ከቀኑ 7 ሰዓት ከሲዳማ ቡና ጋር በሚደረገው ጨዋታ ጌታነህ ከበደ እንደሚሰለፍ ተናግረዋል።