(በታምሩ ዓለሙ)
መንደርደሪያ….
አካሏ በሰለጠነው አለም በበለፀገ ሀገር በዘመናዊ ከተማ በምቾት አርፏል። የበጋውን ፀሀይ ይሞቃል፤ የስዊዘርላንዷን ኤግል መንደር ንፁህ አየር ይምጋል
መንፈሷ ግን በሺዎች ኪሎሜትር ርቆ የትውልድ ቀዬዋ ውስጥ ከትሟል። የእናቷን ድምፅ መስማት ትናፍቃለች፤ ወንድምና እህቶቿን ለማግኘት ትጓጓለች፤ አይኗ የምትኖርበትን የኤግል ከተማ ጥንታዊ ግምብ ቢያይም አሻግሮ የሚመለከተው ግን እትብቷ በተቀበረበት ቦታ የሚገኘውን የአክሱም ሀውልትን ነው። ጆሮዋ ያለችበትን ስፍራ ልዩ መለያ የሴንት ማውሪስ ቤተክርስቲያንን ደውል ድምፅ ቢሰማም ውቂያኖስ አቋርጦ የሚያዳምጠው ግን ያደገችበትን የጥንታዊቷን አክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያንን ወረብና ፅናፅል ነው። እግሯ ከሜስዡር ማዕከል ተነስቶ አውሮፓን አካሎ የብስክሌት ፔዳል ቢዘውርም የትዝታዋ ኮቴ የአክሱምና የመቀሌ መንገዶች ላይ እንደቀረ ነው
- ማሰታውቂያ -
ይህቺ ወጣት በብዙ ፈተና ውስጥ አልፋለች፤ ልጅነቷ ታዳጊነቷና
ወጣትነቷ በችግር የታጀበ ነበር፤ ተስፋ ግን አትቆርጥም፤ አንዱ በር ሲዘጋ ሌላውን እያንኳኳች ከህይወት ጋር ግብግብ ትገጥማለች፤ ትንሽ ተሸንፋ ብዙውን ድል ነስታለች፤ ከአክሱም እስከ ስዊዘርላንድ የተመዘዘው የማትበገረዋን ጋላቢ የሰላም አምሀን የህይወት ሰበዝ በጥቂቱ እነሆ፦
ሩቅ አላሚዋ ታዳጊ….
የአቶ አምሀ ገረፍኤልና የወይዘሮ በላይነሽ አባይ ቤተሰብ በሶስት ሴቶችና በሁለት ወንድ ልጆች በአራት ፍሬዎች ተባርኳል። መስከረም 29/1991 ይህቺን አለም የተቀላቀለችው ሰላም አምሀ የቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ነች፤ ትውልድና እድገቷ ደግሞ አክሱም ከተማ ልዩ ስሙ ቀበሌ 02 ውስጥ ነው፤ ሰላም የልጅነት ህይወቷን ታስታውሳለች፦
“አባቴ በተወለድኩ በሶስት አመቴ ህይወቱ ስላለፈ አላውቀውም፤ እናቴ ነች ያሳደገችን፤ ፈተናው ከዚህ ይጀምራል፤ እናቴ ለእኛ ለልጆቿ ብላ ብዙ መስዕዋትነት ከፍላለች፤ ኑሮን ለማሸነፍ ታግላለች፤ ይህንን እያየሁ በማደጌ እሷን አሳርፌ ጫናዋን አቅልዬ ኑሯችን ከችግር እንዲላቀቅ ማድረግ የሁልጊዜ ህልሜ ነበር፤ ትምህርት እየተማርኩ ጎን ለጎን ስራ እሰራለሁ፤ የቀን ስራ የሚሰሩ ሰዎችን አግዛቸው ነበር”
አክሱም የሚገኘው አብርሃ ወ አፅባህ የመጀመሪያ ደረጃ
ትምህርት ቤት የሰላም አምሀ ቀዳሚ የእውቀት ቤቷ ነበር፤ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በዚህ ት/ቤት ተምራለች። ቀለም ገብ ሆና ከባዱን ህይወት ለማሸነፍ ብትታገልም መክሊቷ ግን ለስፖርት በተለይ ለእግርኳስና ለብስክሌት አደላ። ከትምህርት መልስ ውሏዋ ሜዳ ሆነ፤ እግሮቿ ኳስ ማንከባለልና ብስክሌት መጋለብ አዘወተሩ
“ኳስ በጣም እወዳለሁ፤ ቤት ሳልገባ ደብተሬን ሳላስቀምጥ ሮጩ ወደ ሰፈራችን ሜዳ እሄዳለሁ፤ ስጫወት አመሻለሁ፤ የግራ መስመር አጥቂ ነበርኩ። ኳስ ስጨርስ ደግሞ ብስክሌት እነዳና ወደ ቤት እመለሳለሁ፤ የኳስ ፍቅሬ ግን ይበልጣል። ችሎታዬም ጥሩ ስለነበር ለከተማዬ ምርጥ ተመርጩ አክሱም ከተማን ወክዬ ለመጫወት ችያለሁ፤ ጥሩ ቦታ ደርሼ የቤተሰቤን ህይወት የመለውጥ ምኞቴ በኳሱ እንደሚሳካ እምነት ነበረኝ” ትላለች
ሰላም እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ችሎታውም ነበራት፤ ከተማዋን ወክላ ድንቅ እንቅስቃሴ አሳይታለች፤ ይህንን ተከትሎም ገና በ14 አመቷ ትግራይ ክልልን የመወከል እድል መጣላት፤ ደስ አላት፤ ሆኖም ሌላ እንቅፋት ከፊቷ ተደቀነ
“አዳማ ላይ የሚካሄድ ከ17 አመት በታች የክልል የሴቶች እግርኳስ ውድድር ነበር፤ አንዱ ተሳታፊ ትግራይ ክልል ስለሆነ
የተጫዋቾች ምልመላ ተደረገ፤ እንደምመረጥ እኔም ሌሎች የሚያውቁኝ በሙሉ ተስፋ ነበረን። ነገር ግን እድሜሽ ትንሽ ነው ተብዬ ሳልመረጥ ቀረሁ፤ እኔን ጨምሮ ሶስት ልጆች በእድሜ ምክንያት ከስብስቡ ተቀነስን፤ ተስፋ አድርጌ ስለነበር በጣም አዘንኩ፤ የቡድኑ አባላትም አፅናኑኝ”
የ14 አመቷ ታዳጊ በወቅቱ ቢከፋትም ከእግርኳሱ ለመራቅ አልወሰነችም፤ የተሻለ ቀን ይመጣል ብላ በፅናቷ ቀጠለች። ለመፅናኛም ብስክሌት ትጋልባለች። ድንገት ያላሰበችው ጥሪ ከአሰልጣኝ ሙሴ መንግስቱ ደረሳት
“ከኳሱ እንደተቀነስኩ ብስክሌት የመወዳደር እድል አገኘሁ። አክሱም ከተማ ላይ ቅ/ማርያም፣ ከተማ አክሱምና ማይ ግልጋሎት የሚባሉ ሶስት ክለቦች ነበሩ። በእነሱ መካከል በሚደረግ ውድድር ላይ ማይ ግልጋሎት ክለብን ወክዬ እንድሳተፍ የክለቡ አሰልጣኝ ሙሴ መንግስቱ መረጠኝ። እኔ ብስክሌትን እንደመዝናኛ እንጂ እንደ ስፖርት አይቼው አላውቅም። ለእሁድ ውድድር ሀሙስ ማውንቴን ብስክሌትና ትጥቅ ሰጡኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፌ 2ኛ ወጣሁ፤ በጊዜው ትልቅ የሚባለውን 200 ብር ተሸለምኩ(ሳቅ) ውድድሩ በከተማው ሬዲዮ ተላልፎ ስለነበር ዜናው ተሰማ፤ ቤተሰቦቼ በተለይ እናቴ ተደሰተች፤ ስሜም በሬዲዮ ተጠራ”
መንታ መንገድ….
ሰላም በሁለት ስፖርቶች መካከል ቆመች። ብስክሌትና እግርኳስ በምርጫዋ መሀል ተፋተጉ፤ አሁንም ግን ወደ ኳሱ አደላች። በከተማው በእግርኳስ ቀድማ ስለተመዘገበች ወደሌላ ስፖርት መሄድ እንደማትችል አንዱን እንድትመርጥ ምርጫ ቀረበላት፤ ኳሱን መርጣ በአሰልጣኝ ዛብሎን ዘካሪያስ የሚመራውን ቡድን መረጠች። የብስክሌቱ አሰልጣኝ ሙሴ ደግሞ ራሱም እየሄደ ሰውም እየላከ ምርጫዋ ብስክሌት እንዲሆን ብዙ ለፋ፤ እሷ ግን እግርኳስ ህይወቴ ብላ ቀረች
“ኳሱን በመፈለጌ እሱ ላይ ትኩረት አድርጌ ጠንክሬ መስራቴን ቀጠልኩ። ሽሬ ላይ ውድድር አለ ተብለን ለአምስት ወር በደንብ ተዘጋጀን። መጨረሻ ግን ፌዴሬሽኑ ገንዘብ የለኝም ብሎ ሳንሄድ ቀረን። በወቅቱ ለወንዶች ብቻ ትኩረት መሰጠቱና የእኛ የሴቶቹ መሰረዙ ተስፋ አስቆረጠኝ። ኳሱን ብወደውም ቅድሚያ ለወንድ በመሆኑ ከፋኝ፤ ብስክሌት ጋር ለመሄድ ወሰንኩ”
ቀድሞውንም የሰላምን እምቅ ችሎታ የሚያውቀው የማይ ግልጋሎት ክለብ አሰልጣኝ ሙሴ በደስታ ተቀበላት።በኳሱ ሳትሄድ የቀረችበት ሽሬ ከተማ ላይ በብስክሌት ጋለበችበት። በ2007 ዓ.ም ክለቧን ወክላ ሽሬ ላይ በሶስት ዘርፎች ተወዳደረች፤ አመርቂ ውጤት አመጣች፤ ቀጠለች፦
“ከሽሬው ውድድር ከሁለት ሳምንት በኋላ አዲግራት ሄድን።
በከተማ ውድድር 10 ውስጥ ገባሁ፤ በበረሀ 4ኛ ወጣሁ፤ በግል ደግሞ በተመሳሳይ 4ኛ ሆኜ ጨረስኩ። ሌሎቹ ዘመናዊ የብስክሌት ጫማ አድርገው ሲጋልቡ እኔ ግን ኮንጎ ጫማ ነበር የምጫማው። የእኛ አሰልጣኝ ሙሴ ለትራንሱ አሰልጣኝ ስለእኔ ይነግረው ነበር። እኛ ጋር ጎበዝ ልጅ አለች ይለው ነበር። የትራንሱ አሰልጣኝ መሀሪ ዱሪ ከውድድሩ በኋላ ጁስ ጋብዞ 100 ብር ሸልሞኝ ጥያቄ አቀረበልኝ። ወደ መቀሌ ልውሰድሽና ለትራንስ ፈርሚ አለኝ። ቅድሚያ እምቢ አልኩ። በወቅቱ የ8ኛ ክፍል ተፈታኝ ስለሆንኩ አልሄድም አልኩት። ደጋግሞ ሲጠይቀኝ ቆይ ቤተሰቤን ላስፈቅድ ብዬው ተለያየን”
ከአዲግራት መልስ የቀረበላትን ጥያቄ ለእናቷ አማከረቻቸው። እናት ሰጉ። ከከተማዋ ውጪ ኖራ የማታውቀውና መቀሌ ከገባች በአመት ሁለት ጊዜ ብቻ ለእረፍት እንደምትመጣ የሰሙት ወ/ሮ በላይነሽ የልጃቸው ከአይናቸው መራቅ አስፈራቸው። ሰላም ግን ለተሻለ ህይወት ለህልሟ እውን መሆን መንገዱ ይህ መሆኑን አሳመነቻቸው፤ የጎረቤት ምክክርና ይሁንታም ተጨምሮ የ15 አመቷ ታዳጊ ሰላም አምሀ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ወስዳ ቀጣዩን መቀሌ ለመቀጠል ተስማምታ ትጥቅና ስንቋን ይዛ ወደ ክልሉ ርዕሰ መዲና ሄደች
ስኬትን ፍለጋ…..
2007 ዓ.ም ክረምት ላይ በሀገራችን የብስክሌት ስፖርት ታሪክ
ትልቅ ስም ያለውን ትራንስ ኢትዮጵያ ክለብን ተቀላቀለች፤ ትምህርቷንም በሀውሊቲ መቀሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9ኛ ክፍል ቀጠለች
” ከቤተሰብ ርቄ ኖሬ አላውቅም፤ ከእናቴ ጋር ተማከርንና ወሰንኩ፤ ነሀሴ 2007ዓ.ም አክሱምን ለቅቄ መቀሌ ገባሁ፤ ለትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ፈረምኩ፤ የመጀመሪያ ደሞዜ 900 ብር ነበር፤ ለእኔ ምንም ሳላስቀር ሁሉም ለእናቴ ላኩላት። እኔ ካምፕ ውስጥ ነበር የምኖረው ምግብም መኝታም ከክለቡ ነው። ገንዘቡ ከእኔ ይልቅ ለእናቴ ስለሚያስፈልጋት ላኩላት፤ ደስ አላት” ትላለች ሰላም
አዲስ ቦታ አዳዲስ ጓደኞችና አዲስ ድባብ ውስጥ የገባችው ሰላም አምሀ የነገዋን ብሩህ ተስፋ እያለመች ጉዞዋን ቀጠለች
“በትራንስ ክለብ የመጀመሪያ አመት ቆይታዬ በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ አዲግራት ላይ በኮርስ 7ኛ ወጣሁ። በሌሎች ደግሞ 12ኛ፣ 8ኛና 3ኛ ጨረስኩ። በመሀል ልምምድ ላይ እያለሁ ጉድጓድ ውስጥ ገብቼ ከባድ ጉዳት አጋጠመኝ። ለሁለት ቀን ራሴን አላውቅም ነበር። ለአንድ ወር ሆስፒታል ተኛሁ። ቤተሰቦቼ እንዳይጨነቁ አልነገርኳቸውም በኋላ አገግሜ አላማጣ ላይ ተወዳደርኩ። ትግራይን ወክለን ሀዋሳ ላይ ደግሞ በቡድን አንደኛ ሆነን ጨረስን። በዛው 2008 መጨረሻ ላይ ደግሞ መቀሌ በተካሄደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በግል 6ኛ
ወጣሁ፤ በበረሀ ውድድር ደግሞ 1ኛ ገብቼ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሆንኩ፤በዚህ ምክንያት ከሀገር ውጪ የስልጠና እድል አገኘሁ”
ተስፈኛዋ ወጣት….
የሰላም አምሀ የስኬት መንገድ ቀጥሏል። ተስፈኛዋ ወጣት በክለቡና በስፖርት ቤተሰቡ ተስፋ ተጥሎባታል። የመጀመሪያ ወር ብቻ 900 ብር ደሞዝ ተቀብላ ቀጣዮቹ ወደ 2400 ብር አድጎላታል። ደም ወዟ የእናቷ የባንክ አካውንት ውስጥ ነው የሚገባው፤ ምክንያት አላት፦
“እናቴ ከብድርና ቁጠባ ተቋም 5ሺ ብር ተበድራ ነበር። በየወሩ 44 ብር መክፈል ነበረባት። ግን እሱንም ለማግኘት ትቸገር ነበር። ደሞዝ ስቀበል ወዲያው እልክላታለሁ፤ ብድሩን በፍጥነት ከፍላ ጨረሰች፤ የልጅነት ህልሜን በመጠኑ በማሳካቴ ቤተሰቤን በማገዜ ደስታ ይሰማኝ ነበር። ነሀሴ 2008 ላይ ሩዋንዳ የመሄድ እድል መጣልኝ። በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ያሸነፍን ስድስት ሴቶች ተመርጠን ለስልጠና ሩዋንዳ ኪጋሊ ሄድን። እድሜዬ 17 ስለነበር ከፍ አድርጌ 19 አመት በሚል ፓስፖርት አወጣሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገር ወጣሁ፤ ለአንድ ወር በጣም ጠቃሚ ስልጠና ወስደን ተመለስን፤ ደቡብ አፍሪካም በተመሳሳይ ለስልጠና ተላክን፤ እኔ በግሌ ብዙ እውቀትና ልምድ አግኝቼባቸዋለሁ ”
በእድሜና በልምድ እየበሰለች የመጣችው ወጣቷ ሰላም አምሀ ከ2009 እስከ 2012 ስኬታማ የውድድር አመታትን አሳልፋለች። በተከታታይ አመታት የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሆናለች። አህጉራዊ ተሳትፎዋም አመርቂ ነበር። በ2009 በግብፅ የአፍሪካ ሻምፒዮና በጎዳና ውድድር 10ኛ፣ የቡድን ውድድር 2ኛ ደረጃን ይዛ ፈፅማለች። ሌላ በር ተከፈተላት፤ ከወደ አውሮፓ ስዊዘርላንድ ለሁለት ሴት ብስክሌተኞች የስልጠና እድል መጣ
” የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከስዊዝ የመጣውን ግብዣ ለክልላችን ላከልን፤ ክልሉ ደግሞ ለትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ላከ ። ከዛ እኔና እየሩስ ተስፋሁን ባለን ውጤት መሰረት ተመርጠን ስዊዝ ሄድን፤ ለሁለት ወራት ስልጠናና ውድድር አደረግን። ኢትዮጵያን ወክለን ኖርዌይ በተካሄደው የአለም ሻምፒዮና ተጋብዘን ሁለት ውድድር አደረግን። ውጤታማ ባንሆንም መሳተፋችን በራሱ ትልቅ ተሞክሮ ነበር። ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ተመለስን”
2010 ዓ.ም የሰላም ሌላኛው የስኬት አመት ነበር። ላቧን እያፈሰሰች ሜዳና ተራራውን በብስክሌቷ እያናገረች የአሸናፊነት ሜዳሊያ እያጠለቀች ቤተሰቦቿን እየደገፈች ቀጥላለች። የብስክሌቱ ፍቅር ስለበረታባት ትምህርቷን ግን ከ10ኛ ክፍል አቋርጣለች። በዚሁ አመት በሩዋንዳ የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ከሀያ ሶስት አመት በታች ውድድር 1ኛ ሆና
አጠናቀቀች፤ በተጨማሪ በግል ውድድር 2ኛ፣ በቡድን ደግሞ 1ኛ ሆና ፈፀመች
በ2011 ደግሞ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ሞሮኮ ላይ ብስክሌቷን ይዛ በግል 4ኛ፣ በቡድን 3ኛ እንዲሁም በጎዳና 8ኛ ሆና ገባች። በሀገራችን ባህርዳር ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና የብዙዎችን ቀልብ የሳበችበትን ድንቅ ብቃቷን ያሳየችበትን ውጤት አስመዘገበች። ከ23 አመት በታችና በግል በሁለቱም 1ኛ እንዲሁም በቡድን በተመሳሳይ 1ኛ ሆና የወርቅ ሜዳሊያ አጠለቀች። ይህንን ተከትሎ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ተመረጠች። ሆኖም ውሳኔው ተቀልብሶ የማጣሪያ ውድድር እንዲደረግ ተወሰነ
ሊነጋ ሲል ሲጨልም….
” ከተመረጥኩ በኋላ ድጋሚ ሌላ ውድድር አለ ሲባል ከፍቶኝ ነበር። ነገር ግን በእልህ የመቀሌው ማጣሪያ ላይ ገባሁ። ሁለት የበረሀና አንድ የከተማ ነበር ውድድሩ። የበረሀውን አንዱን ሁለተኛ ሌላውን አንደኛ ሆኜ ጨረስኩ። የከተማው ላይ እየተወዳደርኩ መውደቅ አጋጠመኝ፤ ብስክሌቴም ተበላሸ፤ ብስክሌት ቀይሬ ከወደኩበት ተነስቼ አንደኛ ወጣሁ፤ በጣም ልዩ ደስታ ነበር የተሰማኝ። በቀጥታ ለኦሊምፒኩ ተመረጥኩ። ጓደኛዬ ምህረት አስገላ እሷም ተመረጠች። በምድራችን ታላቁ የስፖርት መድረክ በኦሊምፒክ ሀገሬን ለመወከል ጓጓሁ፤ ግን
ሌላ ነገር ተከሰተ፤ ኮቪድ አለምን አመሰ፤ ኦሊምፒኩም ተራዘመ፤ እኛም ቤታችን ገባን”
ብዙ ፈተናዎችን በፅናት ያለፈችው ሰላም አምሀ አሁንም አልተበገረችም። በወረርሽኙ ከውድድርና ከስልጠና ብትርቅም በግሏ ከመዘጋጀት አልቦዘነችም፤ የክለቧ ትራንስ ኢትዮጵያ ካምፕ ሆና ዘመኑ በፈቀደው ቴክኖሎጂ አለም አቀፍ የስልጠና ዘዴዎችን እየቀሰመች ትተገብረው ነበር። በሽታው ጠፍቶ ድጋሚ ወደምትወደው ጎዳና እስከምትወጣ በተስፋ ስትጠብቅ ብትቆይም ሌላ ተጨማሪ እንቅፋት መጣባት
” ኮቪድ ጋብ እስከሚል ስጠብቅ የሰሜኑ ጦርነት ተጀመረ። የፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ግጭት ውስጥ ገቡ። ነገሮች በፍጥነት ከብርሀን ወደ ጨለማነት ተቀየሩ። መንገድ ተዘጋ፤ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ቆመ፤ የመብራት፣ የባንክ፣ የስልክ አገልግሎት ቆመ። እናቴ ጋር መሄድ አልቻልኩም፤ በስልክም እንዳላገኛት ግንኙነቱ ተቋርጧል። ግራ ተጋባሁ። በመሀል የስዊዘርላንዱ WCC TEAM ክለብ ለኦሊምፒክ መመረጤን ስላወቀ እነሱ ጋር እንድልማመድና የክለቡ አባል እንድሆን ግብዣ ልኮልኝ ነበር። ግን በምን እንደማገኛቸው እንዴት እንደምሄድ አላውቅም። ሁሉም ተቆላልፏል። መቀሌ ላይ አንዳንድ የውጪ ድርጅቶች ስልክና ኢንተርኔት ስለነበራቸው ክለቡ በዩኒሴፍ በኩል የግብዣ ወረቀቱንና ፎርሙን ላከልኝ፤ ሞልቼና ፈርሜ በዩኒሴፍ በኩል መለስኩኝ። በመሀል ለጥቂት
ጊዜ የአየር በረራ ሲጀመር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለሚመለከተው አካል ለቶኪዮው ውድድር መመረጤን አሳውቆ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ልክ እንደገባሁ እንደው ከሰራ ብዬ እናቴ ጋር ነበር የደወልኩት፤ ግን ኔትወርክ የለም። ለኦሊምፒኩ የተመረጥነው እኔና ምህረት አገላይ እንዲሁም አሰልጣኙ ተከስተ ጥላሁንና መካኒኩ ገብረጊዮርጊስ አድሀነ ኢትዮጵያ ሆቴል አረፍን። እኔ ፍላጎቴ ስዊዝ ሄጄ በደንብ ተዘጋጅቼ ለኦሊምፒኩ ለመመለስ ነበር። ሀገር ቤት ውድድርም ስልጠናም ስለሌለ ትግራይም ስለተዘጋ አውሮፓ ሄጄ ልዘጋጅ ብዬ ደጋግሜ ጠየኩ። ኦሊምፒክ ኮሚቴውና ብስክሌት ፌዴሬሽኑ ግን ከሄደች ትጠፋለች አትመለስም ብለው አልፈቀዱልኝም። እንደውም ጠሩኝና ከስዊዝና ከቶኪዮ አንዱን ምረጪ አሉኝ። ቅድሚያ ለሀገሬ ብዬ ትልቁን ኦሊምፒኩን መረጥኩ”
ቶኪዮን መናፈቅ….
ከግል ስኬቷ ይልቅ ሀገራዊ ግዴታዋን ያስቀደመችው ብስክሌተኛ ሰላም አምሀ ከቡድን አጋሮቿ ጋር ሆና ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅቷን ጀመረች። ከመጋቢት 2013 ጀምሮ ለሶስት ወራት በአርባምንጭ ከተማ ልምምዷን አደረገች። ደሞ ሌላ ፈተና ከፊቷ ተጋረጠ
” የአርባምንጩ ቆይታዬ ከባድ ነበር። ቤተሰቦቼ ያሉበትን ሁኔታ
አላውቅም፤ የእናቴን ድምፅ ከሰማሁ ወራቶች አለፉ፤ ውድድር ስለሌለ ልምምድ ብቻ ነበር የምናደርገው፤ አንድ ወር እንደቆየሁ ደግሞ ታመምኩ። ስታከም ወባ በሽታ ተባልኩና መድሀኒት ሰጡኝ፤ ከዛ በፊት አልነበረብኝም፤ ይህንን ሁሉ ተቋቁሜ በቻልኩት ያህል ተዘጋጅቼ ከሶስት ወራት በኋላ አዲስ አበባ ተመለስኩኝ፤ ከመጀመሪያው ልዑካን ጋር ወደ ቶኪዮ ሄድኩ”
ከልጅነቷ ጀምሮ ከሜዳና ተራራው ጋር በግልቢያ ቋንቋ የምትነጋገረው ፥ ለአመታት ላቧን አፍስሳ በመጨረሻ ለታላቁ መድረክ የበቃችው የ23 አመቷ ብስክሌተኛ ሰላም አምሀ ሀገሯን ወክላ ሰንደቋን አንግባ ቶኪዮ ገባች
ያልታሰበው ሲሆን….
በባህሪዋ ዝምተኛና መሸነፍን የማትወደው አንዴ ኮርቻው ላይ ከወጣች ግን ድል ማድረግን ብቻ የምታስበው ጠንካራዋ እንስት ሰላም ብዙ በደሎች ቢደርሱባትም ብዙ ፈተና ቢያጋጥማትም ሁሉን በሆዷ ችላ ሀገርን አስቀድማ ሳትበገር በጎዳና ብስክሌት ውድድር ላይ ቀረበች
እሁድ ሀምሌ 13/2013 ማለዳ ከ43 ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ከአፍሪካ ከአራቱ አንዱ ሆና በ137 ኪሎሜትር ለመወዳደር ኮርቻው ላይ ወጣች
“በጣም ጓጉቼ ነበር። ከአክሱም ትንሽ መንደር ተነስቼ ቶኪዮ ላይ በኦሊምፒክ ለመሳተፍ መብቃት ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው። ውድድሩ ላይ የተሻለ ውጤት አምጥቼ ለሀገሬና ለቤተሰቤ ኩራት ለመሆን ተዘጋጅቼ ነበር። ከዋዜማው ጀምሮ ግን ህመም አጋጠመኝ። ሰውነቴ በጣም ጋለ፤ መልኬ ጠቆረ፤ ራስ ምታትና ድካም አጋጠመኝ። ፀበል ይዤ ሄጄ ነበር፤ ጠጥቼና ራሴ ላይ አፍስሼ ወደ ውድድር ገባሁ፤ አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች የ2021 ሞዴል ብስክሌት ነበር የያዙት የእኔ ደግሞ ከክለቤ ያመጣሁት የ2015 ሞዴል ነበር። በተጨማሪ የእነሱ ልብስ ወንፊት ያለው ዘመናዊ ሲሆን የእኔ ግን ፕላስቲክ ስለነበር ሙቀት ይስባል፤ በዛ ላይ የህመም ስሜት አለኝ።አጀማመሬ ጥሩ ነበር፤ እስከ 47ኛው ኪ.ሜ ከመሪዎቹ መካከል አንዷ ሆኜ ተጓዝኩ፤ ከዛ በኋላ ግን አልቻልኩም፤ አስመለሰኝ፤ አቋረጥኩ፤ ሆቴል ተመለስኩ፤ ውድድሩን የጨረሰ ስፖርተኛ ወዲያው ወደ ሀገር ቤት ስለሚመለስ የእኛ የብስክሌት ልዑክም ሊመለስ ወደ ቶኪዮ ኤርፖርት ሄድን። መንገድ ላይ ግን በድጋሚ ታመምኩ። እንቀጠቀጣለሁ፤ ያዞረኛል፤ መናገር አቃተኝ፤ ኤርፖርት ውስጥ ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ሁሉም ደነገጡ፤ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደማልችል የህክምና ሰዎች ነገሩኝ። የበረራው ሰዓት ስለደረሰ ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ወደ ውስጥ ገቡ፤ ሻንጣዬ ሄዶ እኔ ብቻዬን ዊልቸር ላይ ላይ ቀረሁ። ኤርፖርት የሚሰራ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻዬን መሆኔን አይቶ ተባበረኝ። በኋላ አምቡላንስ መጣና ሆስፒታል ገባሁ”
የኢትዮጵያዊቷ ብስክሌት ጋላቢ ሰላም አምሀ የቶኪዮ ተሳትፎ ህልም በህመም ምክንያት ተጨናገፈ፤ ውድድሩን ከማቋረጧ ባለፈ ለሰባት ቀናት ሆስፒታል አሳለፈች
ለኦሊምፒክ ተሳታፊ ስፖርተኞች በተዘጋጀው ቶራንኦሞን ሆስፒታል ተኝታ ህክምናዋን ስትከታተል ቆየች፤ የህመሟ መንስኤ ወባ በሽታዋ ማገርሸቱ መሆኑንም ተነግሯታል። ብስክሌተኛዋ ከአንድ ሳምንት በኋላ ጤንነቷ መሻሻል በማሳየቱ ከሆስፒታል ወጥታ ኦሊምፒክ መንደር ገባች፤ የታዘዘላትን መድሀኒት እየወሰደች ቆየችና ኦሊምፒኩ ሲጠናቀቅ ከተመለሰው ልዑክ ጋር ነሀሴ 5/2013 ቶኪዮን ተሰናብታ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች
ሌላ ፈተና…..
ሀገር ቤት ስትገባ መንገዱ ሁሉ ምቹ ሆኖ አልጠበቃትም፤ ህመም፣ የመኖሪያ ችግርና የቤተሰብ ናፍቆት በወጣቷ መንገድ ላይ ጋሬጣ ሆነው ቆሙ
ከቶኪዮ መልስ ለ20 ቀናት በኢትዮጵያ ሆቴል ቆይታ ነበር። ሁሉም ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን እሷ ወደ ቤተሰቦቿ ጋር አክሱም ወይም ወደ ክለቧ መሄድ አልቻለችም። ከኦሊምፒኩ በፊት ኑሮዋ በክለቧ ትራንስ ኢትዮጵያ ካምፕ ውስጥ መቀሌ ነበር፤ አዲስ አበባ የምትሄድበት የምትጠጋበት ዘመድ ወገን የላትም
ለአምስት አመታት ክለቡ የሚከፍላትን ወርሀዊ ደሞዝ ለቤተሰቦቿ እየላከች ስትደግፍ ቆይታለች፤ የገንዘብ አቅም አጥሯታል። በጦርነቱ ምክንያት ከቤተሰቦቿ ከተለያየች አንድ አመት ሊሞላት ነው፤ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አልቻለችም፤ የእናቴን ድምፅ መስማት ናፍቆኛል የዘወትር ቃሏ ነው
ለተወሰኑ ቀናት በግሏ ሆቴል ካሳለፈች በኋላ ጎን ማሳረፊያ ትንሽ ቤት ተከራየች ።ጎን ለጎን ለህክምና ኮሪያ ሆስፒታል እየተመላለሰች በራሷ ወጪ ታከመች። በመጨረሻ ለእለት ጉርስና ለቤት ኪራይ እንዲሁም ለህክምና ወጪዎች አቅም አነሳት፤ ከህመሟም ሙሉ ለሙሉ አልዳነችም፤ የቆጠበችውን ገንዘብ ጨርሳ ባዷ እጇን ቀርታለች፤ ለችግሯ መፍትሄ ለማግኘት የስፖርት አካላትን ለማነጋገር ብትሞክርም ምላሽ የሚሰጣት አጣች። እናም ከወር በፊት ቶኪዮ ላይ ኢትዮጵያን የወከለችው ሰላም አምሀ አንድም በቤተሰብ ናፍቆት አንድም በህመም አንድም በገንዘብ እጥረት ተፈተነች። ቀጣይ እጣፋንታዬ ጎዳና መውደቅ እንዳይሆን ብላ ሰጋች፤ ለህዝቡና ለመንግስት ተማፅኖ አቀረበች
ይህቺ ወጣት አምባሳደር ይህቺ የሀገርና የሰንደቅ አላማ ወካይ ብስክሌተኛ ይህቺ ተስፋ ያላት ወጣት ስፖርተኛ ለኢትዮጵያ ያላትን በሙሉ ያለስስት ሰጥታለች። የውጪ እድሏ ተጨናግፏል፤ ከነህመሟ ተወዳድራለች፤ ቤተሰቧን ለአመት ያህል ሳታይ በሰቀቀንና በናፍቆት ኖራለች። አሁን ግን ከበዳት። የዚህ ፅሁፍ
አዘጋጅ ጉዳዩን በመገናኛ ብዙሀንና በማህበራዊ ሚዲያ ዘገባውን አስተላለፈ። በቀናት ውስጥ አስደሳች የምስራች ተሰሙ
የምስራች…
የስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተነጋግረው ሰላም በአካዳሚው መቆየት ትችላለች በማለት ማረፊያ አዘጋጁላትና ማዕከሉ ውስጥ ገባች፤ የቤት ችግሯ ለጊዜው ተቀረፈ። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ ለብስክሌት ልዑካኑ ለሰላም አምሀ፣ ለዋናው አሰልጣኝ ተከስተ ጥላሁን ለተጠባባቂዋ ምህረት አስገላ፣ ለመካኒኩ ገብረጊዮርጊስ አድሀነ በአጠቃላይ ለአራት የቶኪዮ ኦሊምፒክ የብስክሌት ልኡካን በየወሩ 5ሺህ ብር ደሞዝ ለመስጠት ወሰነና ክፍያው ተፈፀመ። ሰላም ነፃ የህክምና አገልግሎትም በዶክተር ጎይቶም ጊጋር አማካይነት አገኘች
“ከቶኪዮ መልስ ዙሪያው ጨልሞብኝ ነበር። ህመም፣ ማረፊያ ማጣት፣ የቤተሰብ ናፍቆት በአንዴ ተደራረቡብኝ። በአጭር ጊዜ ግን በሰዎችና በእግዚአብሔር ዕርዳታ ግን ከቤተሰቤ ናፍቆት ውጪ ሌላው ተስተካከለልኝ።ፈጥኖ ደራሽ ወገን ስላለኝ ደስ ብሎኛል፤ ያገዙኝን በሙሉ ከልቤ አመሰግናለሁ። ጤንነቴ ተስተካክሎ ወደምወደው ስፖርት በድጋሚ ተመልሼ በድል ውለታ ለመመለስም ይበልጥ ጓጓሁ፤ የቀረኝ ቤተሰቦቼ ያሉበትን
ሁኔታ ማወቅ እና የእናቴን ድምፅ መስማት ብቻ ነበር፤ ለእሱ ደግሞ ሁሌ ፀሎት አደርጋለሁ”
ችግር ያላቆማት ሰላም….
ዝምተኛዋ ጋላቢ ሰላም አምሀ ከህመሟ ካገገመች በኋላ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተቀምጣ ህዳር 2014 ላይ ወደ ልምምድ ተመለሰች። ለመወዳደር አማራጮችን ማየት ጀመረች።
World Cycling Center ወይም WWC team መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ኤግል ከተማ ያደረገና በአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ2018 የተቋቋመ የሴት ብስክሌተኞች ክለብ ነው። ከቶኪዮ በፊት ይህ ክለብ ሰላምን ለኦሊምፒኩ ሊያዘጋጃት ብሎም ሊያስፈርማት ከጫፍ ደርሶ የመሄድ ፈቃድ ስላላገኘች እድሏ ተጨናግፎ ነበር፤ እሷም ቅድሚያ ለሀገር ብላ ለኦሊምፒኩ ስትዘጋጅ ቆየች፤ ድጋሚ ይህንን እድል ለመሞከር ከክለቡ ጋር ተፃፃፈች፤ ቀድሞም ይፈልጋት የነበረው የስዊዘርላንዱ ክለብ ነይልኝ አላት። ታህሳስና ጥር 2014 ሁለቱን ወራት በጉዞ ቅድመ ዝግጅት አሳለፈች። የካቲት ላይ ቪዛ ተሰጣት፤ በዚሁ ወር ወደ ጄኔቭ በረረች፤ ክለቡን በይፋ ተቀላቀለች
አሁን ተስፈኛዋ ብስክሌት ጋላቢ ሰላም አምሀ ስዊዘርላንድ ከከተመች ስድስት ወራት አልፏታል።
“በስዊዝ ያለው ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነው። ስልጠናና ውድድር እያደረግን ነው። በአጠቃላይ ስምንት ነን። ኢትዮጵያዊ ደግሞ እኔ ብቻ ነኝ። በፈረንሳይና ስፔን በተካሄዱ ውድድሮች ላይም ክለቤን ወክዬ ተሳትፌያለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነኝ። የቤተሰብ ናፍቆት ብቻ ነው የሚረብሸኝ። አክሱም ያሉትን ቤተሰቦቼንና የእናቴን ድምፅ መስማት ናፍቆኛል፤ ያሉበትን ሁኔታ ሳላውቅ ሁለት አመት ሊሞላኝ ነው፤ ያለኝ አማራጭ ሀገር ሰላም እንዲሆን እናቴን የማገኝበትን ቀን እንዲፈጥን ዘወትር መፀለይ ብቻ ነው”
ሰላም በችግሯ ወቅት ለደረሱላት ለደገፏት ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና ታቀርባለች “ከባዱን ጊዜ እንዳልፍ የረዳችሁኝን በሙሉ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፤በተለይ እንደ እናት ከጎኔ ላልተለየችው የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አሰልጣኝ ዝይን አሰፋ ምስጋናዬ ይድረስሽ፤ ሁላችሁንም ከዚህ ይበልጥ ስኬታማ ሆኜ አኮራችኋለሁ” ብላለች ወጣቷ ብስክሌተኛ ሰላም አምሀ ከስዊዝ
ተስፈኛዋ፣ የማትበገረውና የፅናት ተምሳሌቷ ወጣት ሰላም አምሀ ስዊዘርላድ ኤግል ከተማ ተቀምጣ መንፈሷ ግን ባህር አቋርጦ ተሰዷል። እሷ ጓዳ ሁሉ ሙሉ ነው፤ ሆኖም በጦርነት ምክንያት የመብራት፣ የስልክ፣ የባንክና የትራንስፖርት አገልግሎት ለሁለት አመት የሚጠጋ ጊዜ የተቋረጠበትን ያደገችበትን ቦታ ታስባለች፤ እንዴት እየሆኑ ይሆን ብላ
ትጨነቃለች፤ የእናቷን ድምፅና ምክር መስማት ትጓጓለች፤ ወንድምና እህቶቿን ትናፍቃለች፤ ምን ገጥሟቸው ይሆን ብላ ትሰጋለች፤ ጨለማው የጦርነት አየር ተገፎ ብሩህ ቀን እንዲመጣ ትፀልያለች፤ እስከዛው ግን አካሏ አውሮፓ መንፈሷ እናቷ ጓዳ ነው፤ የማትበገረዋ ጋላቢ ነገ ጥሩ ይሆናል ትላለች
Photo credit – Geety Images
በታምሩ አለሙ