ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርሲቲ 1-0 ሽረ እንዳስላሴ
8:15 ላይ የጀመረው የሁለቱም ቡድኖች ጨዋታ ደጋፊን ቁጭ ብድግ ሚያደርግ ጨዋታ ሳይታይበት በወልዋሎ 1ለ0 ኣሸናፊነት ተጠናቋል።ደደቢትን ከገጠመው ቡድን ዳንኤል አድሓኖምን በ እንየው ካሳሁን፣ ኤፍሬም አሻሞን በአብዱራሕማን ሙባሪክ ቀይረው የገቡት ወልዋሎዎች ቡድኑ ቅንጅት ላይ ብዙ መስራት እንዳለበት የጠቆመ ጨዋታን አሳይቶዋል ።በተለይ በመሃል ሜዳ ላይ የተሰለፋት አስራት መገርሳ፣አማኑኤል ጎበና እና ዋለልኝ ገብሬ አለመቀናጀታቸው ቡድኑ በማጥቃት ላይ ሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ያልተሳኩና የተቆራረጡ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል።በአንጻራዊነት ወልዋሎ ተሽለው በታዩበት የመጀመርያ አጋማሽ ከቀኝ መስመር በእንየው ካሳሁን ሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የሽሬን ተከላካይ ክፍል ሲፈትን ነበር።የዚህ ማጥቃት እንቅስቃሴ ውጤትም በ 22ኛው ደቂቃ ከ ሪችሞንድ ኦዶንጎ የተላከለትን ኳስ እንየው መቶት ወደ ውጪ የወጣውና በ30ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር እንየው ያሻማውን ኳስ ፕሪንስ ሰርቪንሆ ቢመታውም ከግቡ አናት ላይ የሰደዳት ፣ ሽሬዎች ኳስን ከኃላ ለመጀመር ሚያደርጉት ሙከራ በቅርፅ ደረጃ የተሳካ ቢሆንም ከመሃል ሜዳ አልፎ ወደ አጥቂዎች ሚደርስ ኣልነበረም።
በሁለተኛው ኣጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ሽሬዎች በግራ መስመር በሚነሱ ኳሶች የወልዋሎን ተከላካይ ክፍልን ሲፈትኑ ነበር፤ወልዋሎዎችም በአማኑኤል ጎበና በኩል ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።በ64ኛው ደቂቃ ደቂቃ ራችሞንድ ኦዶንጎ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ራችሞንድ ኦዶንጎ ኣስቆጥሮ ወልዋሎ መሪነቱን መያዝ ችሏል።ከግቡ መቆጠር በኃላ ሽሬዎች ሄኖክ ብርሃኑን በዘላለም በረከት በመቀየር ከኃላ ሦስት ተከላካዮችን በማቆም በ3-4-3 ኣሰላለፍ ለማጥቃት ቢሞክሩም የወልዋሎ መረብን ሳይደፍሩ ጨዋታው በወልዋሎ አሸናፊነት ተጠናቋል።
- ማሰታውቂያ -
መቐለ ከተማ 3-1 አክሱም ከተማ
10:20 ሲል የጀመረው የመቐለ ና አክሱም ጨዋታ በመቐለ ከተማ የበላይነት ተጠናቋል።ድሬዳዋን ካሸነፈው ቡድን የ10 ተጨዋቾች ቅያሬ አድርጎ ወደ ሜዳ የገባው መቐለ፤በ4-4-2 አሰላለፍ ፊት ላይ የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ ያለውን ጋናዊውን ኦሰይ ማውሊን ከ አርዓዶም ገ/ሂወት ጋር ሲጣመሩ በአንፃሩ በአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ሚመሩት አክሱሞች በ4-2-3-1 አሰላለፍ መስመሩን ታከው በሚጫወቱ የመስመር አማካዮች ለመጫወት ችለዋል። ጨዋታው በተጀመረ በ10ኛ ደቂቃ ላይ በዮናስ ግርማይ አማካኝነት ሲያስቆጥሩ …ከግቡ መቆጠር በኃላ ማጥቃታቸውን የቀጠሉት መቐለዎች በዮናስ ገረመው በኩል ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር።የመቐለ ተከላካይ ክፍል ወደ መሃል ሜዳ ተጠግቶ መከላከልን የተመለከቱት አክሱሞች ከመሃል እና ከተከላካይ ክፍላቸው በቀጥታ በረዥሙ በሚላኩ ኳሶች ጥቃት ሲሰነዝሩ ነበር።በ25ኛው ደቂቃ ከመሃል ሜዳ የተላከችውን ኳስ በግራ መስመር የተሰለፈው ልዑልሰገድ አስፋው በቀጥታ መትቶት ሶፋንያስ ወደ ውጭ አውጥቶት የተገኘውን ማአዘን ምት አክሱሞች በመሃል ሜዳ ተጫዋቻቸው ስለሺ ዘሪሁን ኣማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረው አቻ መሆን ችለዋል።
በሁለተኛው ኣጋማሽ መቐለ 8 ቅያሬዎችን በማድረግ የጨዋታውን ፍጥነት መጨመር ችለዋል።በተለይም ተቀይረው የገቡት ሻይቡ ጅብሪል፣ ሃይደር ሸረፋ፣ያሬድ ከበደ ና ሳሙኤል ሳሊሶ ጨዋታውን በማፍጠን ረገድ ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ አበርክተዋል።የዚህም ውጤት ሃይደር ሸረፋ ከሳሙኤል ሳሊሶ ጋር በጥሩ ቅብብል አልፈው ሳሙኤል ሳሊሶ አክርሮ በመምታት የመቐለ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።ወደ መሃል ሜዳ ተጠግተው መከላከልን የቀጠሉበት መቐለዎች ከአክሱም ተከላካይ ክፍል የሚላኩ ረጃጅም ኳሶች መቋቋም ቸግርዋቸው ታይቷል፤ ከመሃል ሜዳ በረዥሙ ተልከው ልዑልሰገድ አስፋው መትቶት ሶፋንያስ ያዳነበት እንዲሁም መዋዕል ተቀይረው ከገቡት ኣሚን ነስሩና ቢያድግልኝ ኤልያስ መሃል ሾልኮ በማለፍ ያስቆጠረው ግብ ከጨዋታ ውጭ በሚል የተሻረበት ተጠቃሽ ናቸው።ጨዋታ ሊጠናቀቅ የሦስት ደቂቃ እድሜ ሲቀረው ከመሃል ሜዳ ጂብሪል ያሻማውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ በጭንቅላቱ ለያሬድ ከበደ ሲያቀብለው ያሬድ በጥሩ አጨራረስ የመቐለን መሪነት ወደ 3ለ1 ከፍ አድርጎታል፤ጨዋታውም በመቐለ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ትግራይ ዋንጫ ረቡዕ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል።
08:00 | ደደቢት ከ ሽረ እንዳስላሴ
10:00 | ድሬዳዋ ከተማ ከ አክሱም ከተማ