ለተከበራችሁ የሀትሪክ ቤተሰቦች ዛሬ ለንባብ በወጣችው ሀትሪክ ጋዜጣ ላይ ከአስቻለው ታመነ ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ ቅሬታ መፍጠሩን ተረድተናል።
የቅሬታው ምንጭ ደግሞ አስቻለው ታመነ “የደጋፊው ቁጣ ተጨዋች እስከመደብደብ መድረስ የለበትም” በሚል ለጋዜጣችን በተለይ የሰጠውን ቃለምልልስ ከኔ አንደበት የወጣ አይደለም በማለት ሀትሪክን የሀሰትና የፈጠራ ዘገባ እንደምትዘግብ እንደሚያስመስል ሀሳብ በግል የማህበራዊ ገጹ ላይ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ነገር ግን ሀትሪክ ሃላፊነት የሚሰማትና ለእውነትና ለእውነት ብቻ የወገነች ነፃ ጋዜጣ ናት አሁንም ሀላፊነት እንደሚሰማው የሚዲያ ተቋም ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ያለበትን ሃገራዊ ሃላፊነት ከግምት በማስገባት የቡድኑን፣የደጋፊውን፣የተጫዋቾችንና የስፖርት ቤተሰቡን ስሜት ላለመበረዝና ትኩረታቸውን ላለማሳጣት በሚል አስቻለው ታመነ ለዝግጅት ክፍላችን የሰጠውን ቃለምልልስ በድምፅ ቅጂ(ኦዲዮ) ለግዜው ከመልቀቅ ተቆጥበናል። ያም ቢሆን ግን አስቻለው ከሰራው ስህተት እንዲታረም የድምፅ ቅጂውን(ኦዲዮ) በቫይበር በቴሌግራምና በፌስቡክ ኢንቦክስ የላክልነት በመሆኑ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ያደረገውን የተሳሳተ መረጃ እንዲያስተካክል እድል ሰጥተነዋል።
መረጃውን ሳታዳምጡ ስሜታዊ ሆናችሁ ቁጣችሁን የገለፃችሁልንና እንዲሁም በሰከነ መንፈስ ነገሩ ምንድነው ብላችሁ ስልክ በመደወል በጨዋነት ሀሳባችሁን ለገለፃችሁልን አንባቢዎቻችን ከልብ እናመሰግናለን።የተሳሳተ መረጃ ያቀበለው ሀትሪክ ወይስ አስቻለው ታመነ ለሚለው ከነገ ጨዋታ በኃላ ጠብቁን። በመጨረሻም ድል ሀገርን ወክሎ ለሚጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ!!
የሀትሪክ ኤዲቶሪያል ቦርድ