የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጨዋችነት
ቆይታው ላይ በአማካይ የአጥቂ ስፍራና
አልፎ አልፎም በአጥቂ ስፍራ ለሐዋሳ
ከተማ፣ በውሰት ደግሞ ለአንተርናሽናል
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታ ለወላይታ ቱሳ፣ ለአዳማ ከተማ፣
ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ለብሔራዊ
ቡድናችን ተመርጦ በመጫወት ድንቅ
ብቃቱን አሳይቷል፤ ሀገራችን ካፈራቻቸው
ምርጥ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች
መካከልም በስፖርት አፍቃሪው ሊደነቅ
የቻለም የቀድሞ ተጨዋች ሆኗል፤
ተጨዋቹ በሀላባ ከተማ ተወልዶ በማደግ
ወደ እግር ኳሱ ብቅ ያለ ሲሆን የአሁን
ሰዓት ላይ ደግሞ ቤተሰብን መስርቶና
በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶም ኑሮውን
እየመራም ይገኛል፡፡
የሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ከእዚሁ የቀድሞ
እግር ኳስ ተጨዋች ጋር በየሳምንቱ
ይዛው በምትቀርበው የኦልዲስ በት ጉዲስ
አምዷ ላይ የዛሬው እንግዳ አድርጋ
ያቀረበችው ሲሆን ተጨዋቹም ምላሹን
እንደሚከተለው ሰጥቷል፡፡ ተከታተሉት፡፡
-የእግር ኳስ ጨዋታ ጅማሬውና ስለክለብ
የእግር ኳስ ሕይወቱ፡-
‘‘የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት
ተወልጄ ባደግኩባት የሀላባ ከተማ ነው፤
እዚያም ነው ልጅ ሆኜ አንድነት ለሚባል
የሰፈር ቡድን በመጀመሪያ የተጫወትኩት፤
ትንሽ አደግ ካልኩ በኋላም በሀላባ ከተማ
አንድ ቪድዮ ቤት ላይ ተቀጥሬ ስሰራና ወደ
ሻሸመኔ ከተማም በመሄድ የቪዲዮ ካሴቶችን
በማምጣት እመላለስ በነበረበት አንድ
አጋጣሚ ላይ ያገኘኝ የጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ
ወንድም የሆነው አለማየሁ መኩሪያ ሀላባ
ስመጣ ችሎታዬን ያውቅ ስለነበር የእግር
ኳስን ለምን አትጫወትም ብሎ ሲጠይቀኝ
እኔ ደግሞ ኳስን በጣም ከመውደዴ አንፃር
እጫወታለሁ ምን ችግር አለ ብዬ ስመልስለት
የሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ተቋቁሞ የነበረውን
የሻሸመኔው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ያሰለጥን
ስለነበር በእሱ አማካኝነት ወደ ክለቡ
በመግባት የእግር ኳስ ጨዋታን በክለብ
ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንድ ዓመት ያህል
መጫወት ጀመርኩ፤ በክለብ ደረጃ ከእዚያ
ቡድን ቆይታዬ በኋላም የተጫወትኩት ለሀላባ
ከተማ፣ ለሐዋሳ ከተማ፣ በውሰት ለወላይታ
ቱሳ፣ ለአዳማ ከተማና ለኢትዮጵያ ንግድ
ባንክ ክለቦች ነው፤ በአጠቃላይ በእነዚህ
ክለቦች ቆይታዬ ለ6 ዓመታት ያህል በጥሩ
ብቃት ላይ ሆኜ ኳስን ተጫውቼ በማለፌና
በስፖርት አፍቃሪውም ከፍተኛ አድናቆት
አግኝቼ በማለፌ በያስደስተኝም የእግር
ኳሱን በጉዳት ምክንያት ግን ገና ጠግቤው
ሳልጫወት ለማቆም በመቻሌ ግን በጣም ነው
የሚቆጨኝ”፡፡
–ስለትውልድ ቦታህና እድገትህ ምን
ትላለህ፡-
‘‘የእኔ የትውልድ ስፍራና ቦታ የደቡብ
ክልል ላይ በምትገኘው ሀላባ ቁሊቶ በምትባለው
ከተማ ላይ ነው፤ እዚያም ነው ተወልጄ
ያደግኩት፤ ትንሽ ከፍ ካልኩ በኋላም ኳስን
ልጅ ሆኜ በመጫወትና ኑሮንም ለማሸነፍ
የተለያዩ ስራዎችንም በመስራት አሳልፍም
ነበር በኋላ ላይ ጠልቄ ወደ ኳሱ በመግባት
ከክለብ አንስቶ እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ
የመመረጥና ለአንድ ጊዜም ቢሆን የመጫወት
እድልን አግኝቼ እድገቴን ያሳለፍኩበት
ወቅት የሚጠቀስ ነው፤ የትውልድ ሀገሬን
ሀላባን በተመለከተ እኔ ለማለት የምፈልገው
ከምነግርህ በላይ ነው፤ ሀላባ ለማንም የፍቅር
አገርና ከተማ ነች፡፡ ብዙ ኳስ የሚችሉ
ተጨዋቾችንም ያፈራችና አሁንም እያፈራች
ያለች ሀገርም ነች፡፡ በስፋት ደረጃ ከተማዋ
አሁን ላይ ያላት መሻሻል በጣም ጥሩና
የሚያስገርም ነው፡፡ በፊት የመኪና መሄጃ
አስፓልት አልነበረም፤ አሁን ግን መንገዶቹ
ሁሉ አስፓልት ሆነዋል፤ ከእዚያ ውጪ
ሌሎች የሚያማምሩ ገፅታም ይታይባታልና
እኔን ለእዚህ ደረጃ ቀደም ሲል በነበሩት
ጊዜያቶች ያፈራችኝ የትውልድ ከተማዬን
በሚመለከት አሁን ላይ በእዚህ ደረጃ ላይ
መገኘት መቻሏ እኔን በጣም እያስደሰተኝ
ይገኛል”፡፡
-‘‘ሰቦ” በሚል የተቀፅላ ስም ስለመጠራቱ፡
-“የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ላይ
ከዋናው ስሜ ሰብስቤ በተጨማሪ ስሜን
በማቆላመጥ ‘‘ሰቦ” በሚል የሚጠሩኝ ብዙዎች
ነበሩ፤ አሁንም በእዚሁ ስም የሚጠሩኝም
በርካቶች አሉና የምጠራበት ስያሜዬን
በጣም እወደዋለሁኝ፡፡ እንደውም በክለብ
ደረጃ የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኔን ለአንዴና
ለመጨረሻ ጊዜም ካቆምኩኝና ወደግል ስራዬም
ከተሰማራሁ በኋላ የአሁን ሰአት ላይ በሐዋሳ
ከተማ ውስጥ በምጠራበት የቅፅል ስሜ ‘‘ሰቦ
ሞባይልና ኤሌክትሮኒክስ ማከፋፈያ በሚል
የንግድ ሱቅን ከፍቼ ስራንም እየሰራሁ
ያለሁበት ሁኔታ ስላለ ያለኝን መጠሪያዬን
በጣምም ነው የምወደው”፡፡
–በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር
ተሳትፎው ለመጀመሪያ ክለቡ ሐዋሳ ከተማ
እንዴት እንደገባና በሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ
ዓመት ተሳትፎው ስለነበረው ቆይታ፡-
“ሐዋሳ ከተማ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለእኔ
መጀመሪያ የተጫወትኩበት ክለቤ ቢሆንም
ወደ ቡድኑ ታጭቼ ለመጀመሪያ ገዜ የገባሁት
ግን ገና ሊጉን ሳይቀላቀሉ በፊት ነው፤
ከእነሱ ጋር በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታም
ላይ ነው ታይቼ ለክለቡ ልፈርም የቻልኩት፤
የሐዋሳ ከተማ ውስጥ ወደ ፕሪምየር ሊግ
ለመግባት በተደረገው የክለቦች ውድድር ያኔ
ተሳታፊ የነበርነው፤ እኛ ሀላባ ከተማዎች፣
ሐዋሳ ከተማ፣ ሐዋሳ ዱቄት፣ ሐዋሳ ጨርቃ
ጨርቅ፣ ዲላ ከተማና የመሳሰሉት ቡድኖችም
ነበሩ በእዚያ ፍልሚያ ላይ ሊወዳደሩም ቻሉ
በእዚያ የውድድር ተሳትፎአችን ላይ ታዲያ
እኔ ለሀላባ ስጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረጌ
ባሸገር የውድድሩ ኮከብ ተጨዋችና ኮከብ ግብ
አግቢ ተብዬ መሸለሜም ለቡድኑ ለመግባቴ
ምክንያትም ሆኖኛል፤ ያኔ ከእነሱ ውጪ
ሐዋሳ ዱቄቶችም ሊያስፈርሙኝ ከጫፍ
ደርሰው ነበር በኋላ ለሐዋሳ ስፍርም ጋሽ
አዳነ የሐዋሳ ዱቄት አሰልጣኝ ነበሩና በአቶ
ብርሃኑ ጌታቸው አማካኝነት ለሐዋሳ ከተማ
ስፈርም ተበሳጭተውብኝ ነበር፤ በጊዜው
ለሐዋሳ ስፍርምም ለሪያል ማድሪድ የፈረምኩ
ያህል ነው በወቅቱ የተሰማኝ፤ ለሀዋሳ
ከፈርምኩ በኋላም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ ድሬዳዋ
ላይ በተካሄደው የክልል ክለቦች ሻምፒዮናም
እኛ ሻምፒዮና ሆነን ነበር፤ በተለይ አሰልጣኝ
ገብረመድህን ሀይሌ ከያዘው ትግራይ ከነማ
ጋር ስንጫወትና 3-1 ስናሸንፍ በመርፌ ገብቼ
የተጫወትኩበትና አሸናፊ የሆንበትን ጨዋታ
አልረሳውም”፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ በጣም
ስለተደሰተበት ቀን፡-
‘‘የመጀመሪያው የ1991 የውድድር ዘመን
ላይ የሐዋሳ ከተማ ተጨዋች እያለሁ በማስተር
ቴክኒሺያን ሐጎስ ደስታ ከሚሰለጥነው
የኤሌክትሪክ ክለብ ጋር ተጫውተን ጥሩ
ብቃቴን ያሳየሁበትና ምርጥ የድል ግብም
ያስቆጠርኩበት ከእዚያም ባሻገር ጨዋታውን
እስከ እረፍት በእነሱ 2-0 ተመርተን ከእረፍት
መልስ 3-2 ያሸነፍንበት ግጥሚያ ለእኔ ልዩ
የደስታ ቀን ነበር፤ ሌላው የደስታዬ ቀን ብዬ
የምገልፀው ደግሞ አሁንም የዚሁ ዓመት ላይ
ከቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋር በኮሌጅ ሜዳ ላይ
ያደረግነውን ጨዋታ 2-1 ስናሸንፍ የድሉን
ግብ እኔ አግብቼ ነበርና የክለባችን ደጋፊዎች
አቅፈውኝና አዝለውኝ የጨፈሩበት ቀን
የሚረሳኝ አይደለምና እነዚህን ደስታዎቼን
በልዩ መልኩ የማስታውሳቸው ናቸው”፡፡
–በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመንህ የእኔ
የምንጊዜውም ምርጥ ጨዋታና ጣፋጭስ ግቤ
የምትለው የቷን ነው፤ ግቧን ካስቆጠርክ
በኋላስ ስለነበርህ ደስታ ታስታውሳለህ፡-
‘‘አዎን፤ በጣም ነው የማስታውሰው፤
ምርጡ ጨዋታ የምለው ከላይም
ገልጬዋለሁ፤ ሐዋሳ ከተማ በነበርኩበት
ሰዓት ከኤሌክትሪክ ጋር እየተጫወትን ከ2-0
መመራት አንሰራርተን በሁለተኛው አጋማሽ
የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ግቦች አስቆጥረን
ያሸነፍንበትን ግጥሚያ ነው፤ ያ ጨዋታ
ፈፅሞም አይረሳም፤ ምርጥና ጣፋጭ ግቤ
ብዬ የምጠቅሳትም በእዚሁ ጨዋታ ላይ እኔ
ያስቆጠርኳትን የማሸነፊያ ግብ ነው፤ ግቧን
ያስቆጠርኩት የእነሱን አራት ተጨዋቾች
አብዶ ሰርቼ ካለፍኩኝ በኋላ ግብ ጠባቂው
በለጠ ወዳጆ ፈፅሞ ሳይመለከታትና ምንም
አይነት እንቅስቃሴም ሳያደርግ እንደቆመ
ያስቆጠርኳት ስለነበረች ማራኪነቷ በእኔ፣
በብዙ የስፖርት አፍቃሪዎችና በሐዋሳ ከተማ
ደጋፊዎችም አህምሮ ውስጥ አሁንም ድረስ
አብራ ያለች ነችና ሁሌም የምትታወስም
ነች፤ ያኔ ምርጥ ግቧን ካገባው በኋላም
ደስታዬን የገለፅኩበት መንገድ አሁንም ድረስ
ይገርመኛል፤ ደስታዬን መቆጣጠር አቅቶኝ
ሁሉ ወደየት እንደምሄድም አላቅምም ነበር”፡፡
–በጨዋታ ዘመንህ ልብህ የተሰበረበትና
በጣም የተበሳጨህበት ቀን፡-
‘‘የእግር ኳስ ተጨዋች ሆኜ ልቤ በሀዘን
የተሰበረበትና በጣም ያዘንኩበት ቀን
ብዬ በቅድሚያ የምገልፀው ያኔ ከፈጣሪ
በታች የእኔ የምለው ሰውም አልነበረኝምና
በጣም የምወዳትን የማከብራትን ለእኔ ሁሉ
ነገሬ የነበረችውን ወላጅ እናቴን በ1993ቱ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን
ላይ እኔ ለአዳማ ከተማ ስጫወት ከቅዱስ
ጊዮርጊስ ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት የአዲስ አበባ
ስታዲየም ላይ ከነበረው ጨዋታ በርካታ
ሰዓታቶች በፊት እናቴ ለካ ሞታ ነበርና እኔ
ጨዋታውን ያን እለት ለማድረግ ብችልም
የእናቴን መሞት ከግጥሚያው ማለቂያ
ሰአታቶች በኋላ የሰማው ቀን የተፈጠረብኝን
ከፍተኛ ሀዘን ፈፅሞ አልረሳውም፤ በጊዜው
የእናቴን መሞት አስቀድመው የቡድናችን
ተጨዋቾችና አሰልጣኞች ያውቁ ነበር፤
ያን እለት እኔ ያለወትሮዬ ጨዋታችን 12
ሰዓት ላይ ስለነበር ከ9 ሰአት ጀምሮ ትጥቅ
አድርጌ የቡድናችንን ተጨዋቾች ምንድነው
የምትተኙት ተነሱ እንጂ እላቸውም ነበርና
አንድ ነገር መፈጠሩን ያወቅኩት ግን በኋላ
ላይ ነው፤ በጨዋታው ያን እለት እኔ ለ45
ደቂቃ ያህል ተጫወትኩና በመጎዳቴ ተቀይሬ
ወጥቼ ነበር በኋላ ላይ ቡድኑ አዲስ አበባ
ሲያድር እኔ በመጎዳቴ ከግብ ጠባቂያችን
መሰረት ወልደማሪያምና ከዓለሙ ዘርጋው
ጋር ወደ አዳማ መጥተን ነበር ከጨዋታው
መጠናቀቂያ በኋላ አዳማ ስንደርስም የመሰረት
አባት ናቸው ለሊት ላይ የእናቴን መሞት
ያረዱኝ እነ መሰረትም የማዘጋጃ መኪና
እንዲመጣ አድረጉና ሀዘኑንም ከወቅኩ በኋላ
ነው ወደ ሀላባ የተጓዝኩት ወደ ሀላባ ያኔ ስጓዝ
በሜዳ ላይ ጉልበቴን ተጎድቼ ስለነበር ህመም
እየተሰማኝ እንቅልፍ ሁሉ አልወሰደኝም
ነበርና በእናቴ ሞት በጣም ነው ላዝን
የቻልኩት፡፡ የእግር ኳስ ህይወቴ ላይ ሌላው
ያዘንኩበት ቀን የሐዋሳ ከተማ ክለብ ውስጥ
እያለሁ የሩዋንዳውን ቡድን ጥለን ካለፍን
በኋላ ከናይጄሪያ ክለብ ናሽናል ኢዋንዩ ክለብ
ጋር እዚህ 1-1 ተለያይተን በመልሱ ራሳችን
ላይ ባስቆጠርነው ግብ 2-1 የተሸነፍንበት
ጨዋታን በርካታ የጎል እድሎችን አግኝተን
ሳንጠቀምበት የቀረንበት ጨዋታ ስለነበር
ያም ፍልሚያ በጣም ያበሳጨኛል”፡፡
-ከባህር ማዶ በውጤታማነቱና በድንቅ
አሰልጣኝነቱ የምታደንቀውና የተለየ ቦታ
የምትሰጠው አሰልጣኝ፡-‘‘ስፔናዊው የማንቸስተር ሲቲው አለቃ
ጆሴፍ ፔፕ ጋርድዮላን ነው የማደንቀው፤
የእሱ የአሰለጣጠን ብቃቱና የጨዋታ
ታክቲኩም ይመቸኛልና ለችሎታው የቅድሚያ
ደረጃንም ለእሱ እሰጠዋለሁ”፡፡
–ከውጪ ክለቦች ያለስስት ድጋፍህን
የምትሰጠው ቡድን፡-
‘‘ለሪያል ማድሪድ ነዋ! የእኔ ድጋፍ
የተጀመረውም ዛሬ ላይ ሳይሆን ክለቡ
የአለማችንን ምርጥ የሚባሉ ተጨዋቾችን
ለምሳሌ እንደ ብራዚላዊው ሮናልዶ ሉዊሰ
ናዛሪዮ ዴሊማ እና ፈረንሳዊው ዚነዲን
ዚዳን ከነበሩበት ጊዜም አንስቶ ነው እነሱ
በአጨዋወታቸውም ይስቡኝ ስለነበሩ የእነሱ
ደጋፊ ልሆን የቻልኩት”፡፡
–ከባህር ማዶ ተጨዋቾች በድንቅ
ችሎታው ስለሚያደንቀውና እንደ እሱ ብሆን
ብሎ ስለሚመኘው ተጨዋች፡-
‘‘አርጀንቲናዊው ዲያጎ አርማንዶ
ማራዶና በችሎታው ልዩ ክህሎት ያለው
ተጨዋችና ዋንኛም ሰው ስለሆነ በቅድሚያ
እሱን ነው የማደንቀው፤ ከእሱ በኋላ ደግሞ
የሮናልዲኒሆ ጎቾ፣ ሊዮኔል ሜሲና ኔይማርም
አድናቂ ልሆን ችያለሁና የእንደዚህ አይነት
ጥበበኛ ተጨዋቾች እንቅስቃሴን መመልከት
ደስታዬን ስለሚጨምሩልኝም የሁልጊዜ
ምኞቴ፣ ህልሜና ፍላጎቴም እነሱ ናቸው”፡፡
–ከባህር ማዶ የሚደግፈው ብሄራዊ
ቡድን፡-
‘‘የአርጀንቲና ደጋፊ ነኝ፤ እነሱ እንዳላቸው
ብቃት በውጤት እስከዛሬ የፈሰሰውን እምባዬን
ባያብሱልኝም አሁንም ድጋፌን ያለስስት
እሰጣቸዋለው፤ የአሁን ሰአት ላይ ባለው
ብቃት ሜሲን በጣም ስለምወደውም ዘንድሮ
ምንአልባት እሱ በድልም ያስደስተን ይሆናል
ያንን ስኬት እየጠበቅኩትም ይገኛል፡፡
–በህይወት አጋጣሚ የእግር ኳሱ ላይ
ባለው እውቅና ለአንድ ደቂቃ ባወራውና
ባናግረው ብለህ የምትመኘው ተጨዋች ማንን
ነው? ስታገኘውስ ምን ታወራዋለህ?
‘‘በዓለም ላይ ከሚገኙ ተጨዋቾች መካከል
ከአንድ ጉዳይ ተነስቼ ላወራው የምፈልገው
ተጨዋች ቢኖር ዚነዲን ዚዳንን ነው በጣም
የሚገርምህ እንዲህ ያለ ጥያቄም በሚዲያ
ደረጃ ከእኔም ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ስላለና
መጠየቅንም እፈልግ ስለነበር ይህንን ጥያቄ
ስላነሳችሁልኝ በጣምም ነው ደስ ያለኝ፤
ለእዚሁም ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
የእግር ኳሱ ላይ ዚዳንን መጠየቅ የምፈልገው
በ2006ቱ የአለም ዋንጫ ፈረንሳይና ጣሊያን
ሲጫወቱ እሱ የጣልያኑን ማቴራዚ ለምን
ብሎ በቴስታ እንደመታው ትክክለኛውን
ነገር ጠይቄ ምላሽን ከእሱ አንደበት ማግኘት
እፈልጋለሁ፡፡ በጊዜው ልክ እሱ እንደጥላሁን
ገሰሰ ነፍሱን ይማረውና ሆድ ይፍጀው
እንዳለው ነው ሃሰቡን የሰጠውና ይህን ለእሱ
መጠየቅ እፈልጋለሁ፤ ከእኔ ጋር በተያያዘ
ጉዳይ ላነሳ የምፈልገው የአዳማ ከተማ
ተጨዋች እያለሁ አንድ ጊዜ 1993 ዓ.ም
ላይ ከቡና ጋር ስንጫወት እዚያ ጨዋታ
ላይ ጥሩ ስለተንቀሳቀስኩ የድሉን ጎልም
አገባሁኝ እንደዚያ በሆነበት ጊዜ ግን የቡናው
አሸናፊ ግርማ እንደፈለግከው ብትፈነጭ ለቡና
አትገባም ሲለኝ እሱን በቦክስ መትቼው በቀይ
ካርድ የወጣሁበትና ለ12 ደቂቃ ያህልም
ጨዋታው የተቋረጠበት ጊዜ አይረሳኝም ያኔ
ከጨዋታው በኋላ እኔ እያለቀስኩ የወጣሁበት
ሁኔታም ነበር ተመልካቹ አንድ ነገር አሸናፊ
ሳይናገርው አይማታም በማለት ደጋፊዎቻችን
እኔን ሊያፃናኑኝ የሞከሩበትን ሁኔታ
የማልረሳው ነውና ዚዳንም በእዚሁ አጋጣሚ
ማታሬዚን ምን ብሎት እንደሆነ ብጠይቀውና
ቢነግረኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፡፡
–የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ኳስን
ስትጫወት በደጋፊዎች ከተሰጠህ አድናቆቶችና
ሙገሳዎች ፈፅሞ የማትረሳው፡-
‘‘የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ኳስን
ስጫወት ለእኔ በደጋፊ ደረጃ ከተመለከትኳቸው
ደጋፊዎች መካከል ፈፅሞ አቻ የማላገኛቸው
ደጋፊዎች ቢኖሩ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎችን
ነው፤ ያኔ ለቡድኑ ስጫወት የሚሰጡን ድጋፍና
እኛን የሚያበረታቱበትም ዜማ በጣምም
ይደንቃል፤ ለክለቡ ስጫወት ለእኔ የነበራቸው
አድናቆት ሁሌም የማልረሳው ነው በተለይ
አንዴ ከድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ጋር በድሬዳዋ
የነበረን ጨዋታ ላይ ግጥሚያው በአልቢትር
ኪነጥበቡ እየተመራ 3ለ2 ያሸነፍንበት ጨዋታ
ላይ ሁለት ድንቅ የድል ግቦችን ባስቆጠርኩበት
ጊዜ ጨዋታውን ለመከታተል በ4 መኪና
ሙሉ ታጅበው የመጡት ደጋፊዎቻችን በእኔ
ብቃት ተደንቀው በቃ ከአሁን በኋላ ዜግነት
ቀይር ከአሁን በኋላም የናዝሬት ልጅ ነህ
እያሉ የአድናቆትና የሙገሳ ቃላት የሰጡኝን
ጊዜ አልረሳውም፡፡ የሐዋሳ ከተማ ክለብ
እያለሁም የቡድኑ ደጋፊዎች ያኔ እኛ በ80
ብር ተከራይተን ከምንኖርበት ቤት ድረስ
በፈረስ ጋሪ እየመጣን ስንጫወት ተከትለውን
ለእኛ ክብር በመስጠት ይደግፉንም ነበር፤
የሀላባ ደጋፊዎችም እኔን ለማበረታታት
በ13 ብር ከከተማዋ በመምጣትም ያበረታቱኝ
ነበርና ሁሉንም ላመሰግናቸው እፈልጋለው”፡፡
–የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች
ተመራጭ ስለመሆኑና በተደጋጋሚ ጊዜም
ለቡድኑ እየተጠራ ስለመመለሱ፡-
‘‘የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ
በአሰልጣኝ ስዩም አባተ አማካይነት ተመርጬ
ከሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ጋር የአዲስ አበባ
ስቴድየም ላይ ከተጫወትኩኝ በኋላ ብዙ ጊዜ
አሰልጣኞች በችሎታዬ ይጠሩኝና ይመልሱኛል
እኔን በችሎታዬ አምነውብኝ የሚመልሱበት
መንግድ ሁኔታ ግን ከእግር ኳሱ መርህ
ጋር አብሮ የማይሄድ ነው ለአገር መጥቀም
የምትችልበት ጥሩ ብቃት እያለህ እነሱ
ያንን ወደ ጎን አድርገው አንዳንዶቹ ደግሞ
የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ ለምሳሌ
ስለአንዱ አሰልጣኝ ልንገርህ በእሱ የሃላፊነት
ዘመን ላይ እያለ ለሚያሰለጥነው ቡድኑ
እንድፈርምለት ጠየቀኝ እኔም ጥያቄውን
ሳልቀበል ቀርቼ ቀልድ በሆነ መልኩ ምላሽን
ሰጠሁት በእዚሁ ሳይመርጠኝ ቀረና ለብሄራዊ
ቡድን ልትመረጥ የምትችልበትና ተመርጠህ
የምትመለስበት ሁኔታም በጊዜው አንዳንዴ
ተገቢ አልነበረምና ይሄ አሰራር ሁሉም ነው
የሚያበሳጨኝና ሊታረም ይገባል፡፡
–አብሮት ሲጫወት ቶሎ ስለሚረዳውና
በእንቅስቃሴ ስለሚመቸውና ተግባብቶ
ስለሚጫወተው ተጨዋች፡-
‘‘በእዚህ በኩል የተለያዩ ተጨዋቾች
መጥቀስ እችላለሁ፡፡ የክለቡ ደረጃ ላይ
አብረውኝ ከተጫወቱት ተጨዋቾች መካከል
ያሬድ አበጀን የቅድሚያ ደረጃ ላይ ማስቀመጥ
እፈልጋለሁ፡፡ በእሱ ውጪ ከእኔ ጋር
በእንቅስቃሴ ተግባብተው ይጫወቱ የነበሩት
ተጨዋቾች የሐዋሳው ከተማ ክለብ ውስጥ
ሳለሁ አብረውኝ የነበሩት አለሙ ዘርጋ እና
በፈቃዱ ዘሪሁን ናቸው ልዩ ብቃት የነበራቸው
ተጨዋቾች ነበሩ፡፡
–በጨዋታ ዘመኑ አላንቀሳቅስ ብሎ
ያስቸግረው ስለነበረው ተጨዋች፡-
‘‘የእግር ኳስን ለ6 አመታት ያሀል የእኔ
ተቃራኒ ሆነው ነው ሲጫወቱ ከተፋለሙኝ
ውስጥ እኔን ፈፅሞ እንዳልንቀሳቀስ ያደረጉኝ
ተጨዋቾችም ብዙም ባይኖሩም ሳሙኤል
ደምሴ ኩኩሻ እና አንዋር ሲራጅ አንድአንዴ
ያስቸግሩኝ ነበር፡፡
–የጨዋታ ዘመንህ ምርጥ አሰልጣኝ
የምትለው፡-
ስዩም አባተ እሱ ምርጥ ነው
–የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ተጨዋች
ማነው
‘ዮርዳኖስ አባይ ነው እሱን በፍቅርም
ነው የምወደው ለእኔ የቅድሚያ ደረጃ ላይ
የማስቀምጠውም ነው ሌሎች የማደንቃቸው
ተጨዋቾች በትንሹ ቢሆንም የተጫወትኩበት
ገዜ ላይ ደርሼበታለው ነብሱ ይማረውና
አሰግድ ተስፋዬን በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ
ተጨዋችነት ዘመኑ አንስቶ የማውቀው
ሙሉ አለም ረጋሳን አሸናፊ ግርማን ብርሃኑ
ቃሲምን፣ ገረሱ ሸመናን ዘውዱ በቀለንና
አፈወርቅ ዮሃንስንና ዓለሙ ዘርጋውን
አደንቃቸዋለሁ፡፡
–የእግር ኳስን ስለማቆሙና ጫማውን
ስለሰቀለበት ምክንያት፡-
‘‘የእግር ኳስን ሳልጫወት በአጭር
አመታት ጊዜ ውስጥ ለማቆም የቻልኩት
በጉልበቴ ላይ በደረሰበኝ ግጭት በቁርጭምሚቴ
ላይ ጠንከር ያለ ጉዳት ሊያጋጥመኝ በመቻሉ
ነው ያኔ ጉዳቱ ሲደርስብኝ እግሬ ላይ
የሚገኘው ስፍራ ላይ አራት ጥርስ ጥርስ
የሚያህል አጥንት ስጋዬ ላይ ተለጥፎብኝ ነበር
ከአደጋው ለመዳን ብዙ ጥረት አድርጌያለው
ብዙ ሆስፒታል ሄጃለው፤ ቅዱስ ገብርሄል ና
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ ብዙ ቦታ
ሄጄ ልታከም ብችልም መዳን ሳልችል ቀረው
በኋላ ላይ ጉዳቱ ሲበረታብኝ ጊዜ ጣሊያኖች
አርሲ ነገሌ ላይ በከፈቱት ጂጌሳ በሚባል
ሆስፒታል ብራዚላዊውን ሮናልዶ ያከመ
አንድ ዶክተር ወደ አገራችን መጥቶ ነበርና
በእሱ አማካኝነት ታክሜ ለመዳን ብችልም
ኳሱን ግን በጊዜው ሊያጫውተኝ የሚችል ነገር
ቢኖርም በእዚያው የእኔ ጉዳትንና ያለሁበት
ሁኔታን ብዙዎችም በአግባቡ የሚያውቁም
ስላልነበር በጊዜው ልጫወት ወደምፈልግበት
የኢትዮጵያ ቡናም ፈርሜ በኋላ ላይ ሳልገባ
ቀርቻለሁ፡፡
–የእግር ኳሱን በጉዳት ምክንያት
መጫወት እንደደማትችል ስታውቅ ምን
ተሰማህ፡-
‘‘በጣም ያማል ባለጎዳ ኖሮ ለረጅም
አመታት የሚያጫውተኝ ብቃትና ክህሎት
ነበረኝ በተለይ ደግሞ ኳሱን የሐዋሳ ከተማ
ውሰጥ አሁን የሊጉ ላይ ከሚጫወቱት
ተጨዋቾች ጋር በጉዳትና በቀይ ካርድ
አልፎ አልፎ ለየቡድኖቻቸው ሳይሰለፍ
ከሚቀመጡ ልጆች ጋር አብሬያቸው ስጫወት
ደስ ይለኛል፤ ለክለብ ለመጫወት ባልችልም
ከኳስን መለየት አልፈልግምና አሁንም
ለጤንነት እየተጫወትኩኝ ነው፡፡
-የኢትዮጵያ ፕሪምየር ላይ በተቃራኒነት
ስትፋለማቸው ሁሌም የሚያስደስቱክ ክለቦች፡
-‘‘ ሁለት ናቸው፤ እነሱም ኢትዮጵያ ቡናና ቅ/
ጊዮርጊስ ከእነሱ ጋር ሁሌም የሌሎች ክለቦች
ማለትም የሐዋሳ ከተማ፣ የአዳማ ከተማና
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ተጨዋች
ሆኜ ስፋለማቸውና ስናሸንፋቸው በጣም ደስ
ይለኛል፤ እነሱን ካላሸነፍናቸው በምንም
ነገር ደስ አልሰኝም ነበር፤ በተለይ ደግሞ
ከቡና ጋር ስንጫወት በጣም የምደሰተው
በአጨዋወታቸው ስለምደነቅና በእዚያም
ማራኪ እንቅስቃሴያቸው ሁሌም ስለምረካና
የእነሱም ደጋፊዎች አጨፋፈርም ይስበኝም
ስለነበር ለሌላ ቡድን እየተጫወትኩም
የእነሱም ደጋፊም ስለነበርኩ ነው ደስታዬም
ልዩ ሊሆንልኝ የቻለው”፡፡
–ስለትዳር ህይወትህ ምን ትለናለህ፤
ባለቤትህንስ እንዴት ትገልፃታለህ?፡-
‘‘የትዳርሕይወቴን የሐዋሳ ልጅ ከሆነችውና የጅማ
ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከነበረችው ባለቤቴ ለምለም
መርጊያ ጋር ለሁለት ዓመት በፍቅር ከቆየን
በኋላ ከጥቅምት 25 2005 ዓ/ም ጀምሮ
በነበረን ትውውቅ ከአራት ዓመት በፊት
ትዳርን መስርቻለው፤ ከእሷም ታማኝ /
ያፌት/ ሰብስቤና ሳሌም ሰብስቤ የተባሉ
የሶስት ዓመትና የአንድ ዓመት ከሁለት ወር
ልጆችንም አፍርቻለው፤ ለመጀመሪያ ልጄ
ታማኝ ብዬ ያወጣሁለት ለአርቲስት ታማኝ
ባለኝ ጥልቅ ፍቅር ነው፤ ባላቤቴን በተመለከተ
እኔ የምገልፃት በጣም ጥሩና መልካም
የሆነች ልጅ መሆናን ነው፤ ለእኔ እሷ የእናት
ያህልም ብዙም ነገሬም ናትና ቤተሰባችንን
የምትንከባከብበት መንገድ ሊያስደንቃትና
ሊያስመሰግናትም የሚገባ ነውና በእሷ በጣም
ደስተኛ ነኝ”፡፡
–ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፈልጎና
ፈርሞ ለሁለት ጊዜያት ያህል ሳይሳካለት
ስለመቅረቱ፡-
‘‘ወደ ኢትዮጵያ ቡና ገብቶ
ለመጫወት ከአንዴም ሁለት ጊዜ እድሉ
የነበረኝ ቢሆንም በተለይ አንዱ ላይ ሊሳካልኝ
ባለመቻሉ በጣም ነው የሚቆጨኝ፤ ለቡና
ደጋፊው ስለሆንኩና በጊዜው የነበሩት
ተጨዋቾችም ምርጥ ስለነበሩም ነው
ለመጫወት ፈልጌ የነበረው ያኔ እልሜ ተሳክቶ
ቢሆን ኖሮ በጣምም ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖም
ግን ለቡና ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐዋሳ ከተማ
በአሰልጣኝ ስዩም አባተ አማካኝነት ለብሔራዊ
ቡድን ተመርጬ መጥቼና ከፈረምኩ በኋላ
ከቡድኑ ጋር በገንዘብ ክፍያ ሳልስማማ
ስለቀረሁ ወደ ቡድኑ ሳልገባ ቀርቻለው፤
ከቡናዎች ጋር ያኔ ያልተስማማሁት
መጀመሪያ ስንነጋገር ለፊርማ 15ሺ ብር
እንሰጥሃለን ብለውኝ በኋላ ላይ ደግሞ
ክፍያውን በሁለት ጊዜ ክፍያ እንስጥህ የሚል
ሀሳብን ይዘው በመምጣታቸው ነው፤ እኔ
ደግሞ በጊዜው ለክለቡ የመጫወት ፍላጎቴና
ጉጉቴ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም የሀላባ ከተማ
ውስጥ የተወለድኩና የደሃ ልጅ ስለነበርኩም
ብሩ ቤተሰቤን ለመርዳት ያስፈልገኝም
ስለነበር ካልሰጣችሁኝ ብዬአቸውና ሐዋሳ
ከተማም መልቀቂያ ከለከሉኝም ብዬ ወደ
ቡና ሳልገባ ቀረው፤ ወደ ቡና ልገባ የነበረበት
ሌላው አጋጣሚ ደግሞ በ1996 ነበር ለክለቡ
ለመፈረምም ከጫፍ ደርሼም ነበር ሆኖም
ግን ለእዚህ ለምወደው ክለብና ደጋፊ ከእነ
ጉዳቴ መጫወት መቻል ራስ ወዳድነት ነው
በሚል ምክንያት ራሴን ወደዚያ ከማምራት
በመቆጠብ ወደ ቡድኑ ሳልመጣ ቀርቻለው፤
እኔ ለቡና ሙሉ ጤነኛ ሆኜ ነበር መጫወትን
የምፈለገውና ያ በወቅቱ ሳይሳካ ሊቀር
ችሏል”፡፡
በመጨረሻ…‘‘የእግር ኳስ ህይወቴ
ላይ በተጨዋችነት ዘመኔ ኳስን ስጫወት
ለእኔ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱልኝን ሁሉ
አመሰግናችኋለሁ፡፡ በመጀመሪያ ፈጣሪዬን
በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን አስቀድማለሁ
ከእነሱ በኋላ ወደ ክለብ ደረጃ ገብቼ
እንድጫወት በማሰልጠንና በመምከርከር ከጎኔ
የነበሩት የጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ወንድም
አሰልጣኝ አለማየሁ መኩሪያ፣ በአላባ ከተማ
ያሰለጠኑኝን ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ
በኃይሉ ደስታ፣ በአዳማ ከተማ ያሰለጠነኝ
ብርኃኔ ገ/እግዚያብሔር፣ በአዋሳ ያሰለጠኑኝ
ጋሽ ከማል፣ እንደዚሁም ደግሞ ወደ
ኢትዮጵያ ቡና ገብቼ ባልጫወትም ወደ ክለቡ
እንድመጣ ትልቅ ግፊት ያደርጉ የነበሩት
ነብሱን ይማረውና አሰግድ ተስፋዬንና ሌላው
ወደ ቡና እንድመጣ ጥረት ያደርጉ የነበሩት
የአላባ ነዋሪ የሆኑት ሀጂ ሉሉ ሰይድ
መኪዬና ሳመሰግን ሌሎቹ የምጠቅሳቸው
ደግሞ የሀላባ ነዋሪ የሆኑትን አቶ አቡዱል
ሰመድ መሐመድንና የአላባ ህዝብን ማመስገን
እፈልጋለው”፡፡