በመሸሻ ወልዴ
ሀትሪክ፡- ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ
ሰበታ ከተማን በአንተ ሁለት ጎሎችና በካርሎስ
ዳምጠው አንድ የፍጹም ቅጣት ምት ጎል 3ለ1
ሊያሸንፍ ችሏል፤ ጨዋታው ምን ይመስል
ነበር? የነበራችሁስ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምን
ነበር?
ሰመረ፡- ሰበታ ከተማን ያሸነፍንበት
የእሁድ ዕለቱ ጨዋታ ለእኛ ግጥሚያውን
ከሜዳችን ውጪ እንደማድረጋችን እና
ጨዋታውም የመጀመሪያችን እንደመሆኑ
ከባድ ሆኖብን ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ከእነሱ
በተሻለ እኛ ጥሩ ስለነበርን ልናሸንፋቸው
ችለናል፡፡
በጨዋታው ቡድናችን የነበረው ጠንካራ
ጎን የያዘውን የመሪነት ውጤት አስጠብቆ
ከሜዳ ሊወጣ መቻሉ ሲሆን ክለቡ የነበረበት
ክፍተት ደግሞ ክፍተት ሊኖር ይችላል ግን
ቡድናችን በማሸነፉ ሊደበቅለት ችሏልና
በእዚያ ላይ ግን የምንሰራው ነገር ይኖራል፡፡
ሀትሪክ፡- ለወልዋሎ አዲግራት በፕሪምየር
ሊጉ የጅማሬ ጨዋታ ላይ ሁለት ወሳኝ የድል
ጎሎችን በሰበታ ከተማ ላይ ያስቆጠርክ እና
በሊጉም ላይ እየታየህ ያለህ አዲስ ፊት
ተጨዋች ሆንሃል፤ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕም
ላይ ለቡድኑ ስትጫወት ተመልክተንሃል፤
አጀማመርህም የአማረ ሆኗል፤ በእዚሁ
ትቀጥላለህ? ወይንስ…?
ሰመረ፡- የወልዋሎ አዲግራት
ዩንቨርስቲ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ
በአሁን ሰዓት ላይ እየተጫወትኩ
የምገኘው በአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ
አማካኝነት ከወጣት ቡድኑ የተሰጠኝን
የማደግ እድል በአግባቡ በመጠቀም
እና ተቀይሬም በመግባት ለቡድኔ ጎል
ማስቆጠር የጀመርኩ ሲሆን፤ ይህን ጎል
ማስቆጠሬንም ወደፊትም ቢሆን ለፕሪምየር
ሊጉ የኮከብ ግብ አግቢነት መፎካከር
ስለምፈልግና ቡድኔንም ውጤታማም
ለማድረግ ስለተዘጋጀው ወደፊትም ሌሎች
ጎሎች ማስቆጠሬ አይቀሬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በሰበታ ከተማ ላይ የመጀመሪያ
ጎልህን እንዳገባህ በቀጥታ ደስታህን ሄደህ
የገለጽከው ለአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ያለህን
ክብር በሚገልጽ መልኩ እጅ በመንሳት ነበር፤
እስኪ ስለዛ ትንሽ ብናወራ….?
ሰመረ፡- አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ለእኔ
በጣም ጥሩ እና ምርጥም የሆነ አሰልጣኝ
ነው፤ ብዙ ነገሮችንም አስተምሮኛል፤ በተለይ
ከኳስ ውጪ ስለ ህይወትም ያሳወቀኝ ሁኔታ
ራሴን በምን መልኩ መምራት እንዳለብኝ
ስለነገረኝ፤ ግንዛቤም ስለሰጠኝ በሰበታ ከተማ
ላይ ጎሉን ካገባው በኋላ ደስታዬን ወደ እሱ
በመሄድ የገለጽኩት ለእኔ ወደዋናው ቡድንእንዳድግ እና ለቡድኑም ተሰልፌ እንድጫወት
ካደረገልኝ ከፍተኛ ውለታ አንጻር ነውና
በእዚሁ አጋጣሚ ላመሰግነው እፈልጋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በሰበታ ከተማ ላይ በእዚህ
የወጣትነት ዕድሜህ ሁለቱን የድል ጎሎች
ተቀይረህ በመግባት ስታስቆጥር የነበረህ
የደስታ ስሜት የቱን ያህል ነበር?
ሰመረ፡- የድል ጎሎቹን ካስቆጠርኩ በኋላ
ለማመን በሚያቅተኝና ራሴን በማላውቅበት
መልኩ በጣም ነበር የተደሰትኩት፤
ከዛም ለወጣት ተጨዋቾች እንዲህ ያሉ
በቂ የመሰለፍ ዕድሎች ከተሰጡ ጎሎችን
ከማስቆጠር ወደኋላ እንደማይሉም ያሳየኝ
ግጥሚያም ነውና ጨዋታውን በጣም ነበር
የወደድኩት፡፡
ሀትሪክ፡- ወልዋሎ አዲግራት በዘንድሮ
የሊጉ ተሳትፎው ምን ውጤትን ያመጣል?
ሰመረ፡- ወልዋሎ አዲግራት የእዚህ
ዓመት ፕሪምየር ሊግን የሚወዳደረው
ዋንጫውን ለማንሳት ነው፤ ያ ካልተቻለ
ደግሞ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘን
ለማጠናቀቅ ተዘጋጅተናል፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን መጫወት ስትጀምር የአንተ ተምሳሌት ተጨዋቾች እነማን
ናቸው?
ሰመረ፡- ከሀገር ውስጥ ጌታነህ ከበደ
ሲሆን ከባህር ማዶ ደግሞ ክርስቲያኖ
ሮናልዶ ነው፤ ለሁለቱም ተጨዋቾች ልዩ
ፍቅርና አድናቆትም ነው ያለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የወደፊት የኳስ ምኞትህ
ምንድን ነው?
ሰመረ፡- የመጀመሪያው ለሀገሬ
ብሔራዊ ቡድን ተመርጬ መጫወትና እሷን
ለውጤትም ማብቃት ሲሆን ሌላው ደግሞ
ክለቤንም ለጥሩ ደረጃ ማብቃት ዋንኞቹ
እቅዶቼ ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ….?
ሰመረ፡- በእግር ኳሱ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት
ደረጃ ቤተሰቦቼ በተለይ ደግሞ ወላጅ እናቴ
ያደረገችልኝ ነገር ሁሌም ቢሆን የማይረሳ
እና ከምንም ነገርም በላይ ነው፤ ለእሷ
ፈጣሪ እድሜ ይስጣት፤ አመሰግናታለው፤
ከዛ ውጪም የወልዋሎ ደጋፊዎች ክለባችንን
በየቦታው በመምጣት እያበረታቱን ይገኛልና
ለእነሱም ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡